Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ ታሪክ ትልቅ የተባለው 510 ሚሊዮን ዶላር ለትምባሆ ሞኖፖል ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በሥሩ የሚገኘውን የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት 40 በመቶ አክሲዮን ለመሸጥ ላወጣው ጨረታ ጃፓን ትምባሆ ኢንተርናሽናል፣ በኢትዮጵያ የልማት ድርጅቶች ሽያጭ ታሪክ ያልተለመደ ከፍተኛ መወዳደሪያ ገንዘብ አቀረበ፡፡ ጃፓን ትምባሆ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት 40 በመቶ ባለድርሻ ለመሆን 510 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል፡፡

ከዚህ ቀደም ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ሙሉ ለሙሉ የገዛው የእግሊዝ ኩባንያ ዲያጆ 225 ሚሊዮን ዶላር፣ ሚድሮክ ጎልድ ለገደንቢ ወርቅ ማውጫን ለመግዛት 172 ሚሊዮን ዶላር ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ የትምባሆ ድርጅትን 40 በመቶ አክሲዮን ለመግዛት ጃፓን ትምባሆ ያቀረበው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከጃፓን ትምባሆ ጋር ሌሎች አምስት ኩባንያዎች የተጫረቱ ሲሆን፣ ብረትሽ አሜሪካ ቶባኮ 230 ሚሊዮን ዶላር፣ ቻይና ሎጂስቲክስ ሊሚትድ 156 ሚሊዮን ዶላር፣ ፓን አፍሪካ 120 ሚሊዮን ዶላር ለ40 በመቶ አክሲዮን ሲያቀርቡ፣ ኢሮ አዶ ኒጀር ኢትዮጵያ ኩባንያ ለአሥር በመቶ አክሲዮን 35 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል፡፡

በዚህ ጨረታ ጃፓን ትምባሆ ያቀረበው መወዳደሪያ ገንዘብ ያልተጠበቀ በመሆኑ ተወዳዳሪዎችን ያስገረመ ክስተት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት 29 በመቶ ባለድርሻ የሆነው የየመኑ ሼባ ኢንቨስትመንት፣ ሁለት ደቂቃ ዘግይቶ በመምጣቱ ከጨረታ ውጪ መደረጉ አስገራሚ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር መጋቢት 2008 ዓ.ም. ባወጣው ጨረታ ለመሳተፍ፣ ከ40 በላይ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ ገዝተው ነበር፡፡ በቀጥታ ሽያጭ መርህ በቁጥር 002/2016 የወጣው የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ሽያጭ ለጨረታ የቀረበው አክሲዮን 40 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ባለአክሲዮኖች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር 71 በመቶ ሲኖረው፣ የየመኑ ሼባ ኢንቨስትመንት 29 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

የየመኑ ኩባንያ ባለድርሻ በመሆኑ በድርድር የሚገዛ በሆነ ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም፣ የመን ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ኩባንያው የሚጠበቅበትን ፋይናንስ ማቅረብ ባለመቻሉ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በዚህ መሠረት መንግሥት ካለው 71 በመቶ ድርሻ 40 በመቶው ለገበያ በማቅረቡ ሳቢያ፣ ሼባ ኢንቨስትመንት ቀደም ብሎ ያጣውን ዕድል ለመጠቀም፣ ከሌሎች የገንዘብ ምንጮች ፋይናንስ በማግኘት ለመወዳደር ቀርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሼባ ኢንቨስትመንት ሰዓቱን ጠብቆ ስላልቀረበና ኩባንያው መሳተፍ እንደሌለበት ከተወዳዳሪዎች ተቃውሞ በመቅረቡ፣ የአምስት ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ ሲከፈት የየመኑ ኩባንያ የጨረታ ሰነድ ግን ሳይከፈት ቀርቷል፡፡

ጃፓን  ትምባሆ ያቀረበው መወዳደሪያ ገንዘብ ከዚህ ቀደም ለሽያጭ  ከቀረቡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የበለጠ ብቻ ሳይሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ገንዘብ ካቀረበው ብሪትሽ አሜሪካ ትምባሆ ጋር ሲነፃፀር፣ ከግማሽ በላይ ብላጫ ያለው ነው፡፡

ብሪትሽ አሜሪካ ትምባሆ በሮዝማን፣ በፊሊፕ ሞሪስና በሌሎችም የሲጋራ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታወቃል፡፡ ጃፓን ትምባሆ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ስምንት የሲጋራ ምርቶች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ውስጥ ዊንስተን፣ ካሜል፣ ሚቪስ፣ ቤንሰንና ሄጂስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ጃፓን ትምባሆ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ 11 በመቶ ድርሻ እንዳለውና በዓለም ላይ ሦስተኛው ግዙፍ የትምባሆ ኩባንያ መሆኑን፣ ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች