– 100 ያህል ሆቴሎች ከደረጃ በታች ተብለዋል
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያን ከጎበኙ ከ700 ሺሕ በላይ የውጭ ዜጎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታወቀ፡፡ በአምስቱ ዓመት ዕቅድ መሠረት በየዓመቱ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ግን ስድስት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ቱሪስቶች ቁጥር 712,111 እንደሆነና ከእነዚህ ጎብኚዎችም 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊገኝ እንደቻለ፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት ወቅት፣ የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ተክሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ዋና ሪፖርት ገና ይፋ አለመውጣቱ ታውቋል፡፡
ምንም እንኳ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2.7 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱና የጎብኚዎች ቁጥር ከ700 ሺሕ በላይ መሆኑ ቢገለጽም፣ በሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት ዕቅድ መሠረት ይገኛል የተባለው ገቢ መጠን ስድስት ቢሊዮን ዶላር፣ የጎብኚዎች ቁጥርም ስድስት ሚሊዮን እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተመዘገበው አፈጻጸም ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ተቀራራቢ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ካቻምና አገሪቱን የጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር 724,000 ሲሆን፣ ተገኘ የተባለው ገቢም ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጋር በትብብር ሲከናወን የቆየው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ፣ 359 ሆቴሎችን በመመዘን የተጠናቀቀ መሆኑ ሲገለጽ ከእነዚህ ውስጥ እስከ 100 ያህል ሆቴሎች ከደረጃ በታች ሆነው መገኘታቸውን አቶ ሲሳይ ጠቁመዋል፡፡
በመላ አገሪቱ ከተመዘኑ 359 ሆቴሎች ውስጥ 139 ሆቴሎች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 75 እስካሁን ደረጃቸውን ያወቁ፣ 38 ደረጃ ቢያገኙም ሊያሟሉ ባልቻሏቸው አስገዳጅ ግዴታዎች ምክንያት ደረጃቸው ገና ያልተገለጸላቸው፣ 26 ሆቴሎች ግን ከደረጃ በታች ባለዜሮ ኮከብ ተብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ 70 ሆቴሎች ለኮከብ ደረጃ ተመዝነው 20ዎቹ ብቻ እስካሁን ደረጃቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ 32 የኮከብ ደረጃ ቢያገኙም ውጤታቸው ተይዟል፡፡ 18 ግን ከኮከብ ደረጃ በታች ዜሮ ሆነዋል፡፡ ከ359 የአገሪቱ ሆቴሎች ውስጥ እስካሁን የኮከብ ደረጃ ውጤታቸው ያልተጠቃለለው የድሬዳዋ ከተማና የሐረሪ ክልል 19 ሆቴሎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሆቴሎች ሲካተቱ ከደረጃ በታች ዜሮ ኮከብ የሚያገኙ ሆቴሎች ቁጥር 100 ሊደርስ እንደሚችል አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ ካሉ 600 ያህል ለደረጃ ብቁ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ ሆቴሎችን ለኮከብ ደረጃ ለመመዘን አቅዶ የነበረው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ዕቅዱን በመከለስ 400 ያህሉን ቢያካትምም በመጨረሻው ግን 359 ሆቴሎች ለደረጃ ብቁ ተብለው ተገምግመዋል፡፡