Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለጎርፍ ሥጋት የተጋለጡ አካባቢዎች ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲነሱ ጥሪ ቀረበ

ለጎርፍ ሥጋት የተጋለጡ አካባቢዎች ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲነሱ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

– 1.5 ሚሊዮን ዜጎች አደጋ አንዣቦባቸዋል

የዝናብ ወቅትን በማስተጓጎል ለድርቅ መንስዔ ሆኗል የሚባልለትን ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ክስተት መዛባት ተቃራኒ ነው የተባለለት ላኒና የጎርፍ አደጋ በብዛት እያስከተለ ነው፡፡ ይህ ላኒና የተባለ ክስተት በሚያስከትለው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ምክንያት በአገሪቱ በመጪው ክረምት የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተዳፋትና በወንዞች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በፍጥነት ወደሌላ ሥፍራ እንዲዛወሩ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስቸኳይ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ የጎርፍ አደጋን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ስለተወሰደውና በቀጣይ ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎች በተመለከተ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ አስቸኳይ ሥራ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተለይ በመጪዎቹ ሐምሌና ነሐሴ ከአንድ ወር በፊት ቀድሞ ከተተነበየው በላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ከፍተኛ ዝናብና ያልተጠበቁ የወንዞች ሙላት ሊከሰት ስለሚችል፣ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋዎች ይጋለጣል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጎርፍ አደጋው በገጠርና በከተማ የሚከሰትበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ፣ በቅድመ ጎርፍ ወቅት የመከላከል ሥራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በጎርፍ ወቅትም ሆነ በድኅረ ጎርፍ ወቅት ሊኖር ይገባዋል ያሉትን ምላሽ የመስጠትና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን አቶ ካሳ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የበልግ ዝናብ እየተጠናከረ ከመጣበት ከመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ሳምንት አንስቶ ጎርፍ በ134 ሰዎች ላይ የሞት አደጋ አስከትሏል፡፡ ይህም በክልል ደረጃ ሲታይ ኦሮሚያ 23፣ ደቡብ የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ 59፣ አማራ 4፣ አፋር 5፣ ሐረሪ 4፣ ድሬዳዋ 5፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ 33 እና ትግራይ 1 እንደሆነ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

በእንስሳት ሀብት ረገድም በጠቅላላው 33,446 የተለያዩ የቤት እንስሳት በ48,884 ሔክታር ላይ የነበረ ሰብል መጎዳቱን፣ በ36,130 ሔክታር ላይ የነበረ ሰብል መውደሙን አስረድቷል፡፡

ጎርፍ በመኖሪያ ቤቶች፣ በተቋማትና በትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን፣ በአጠቃላይ 3,373 ቤቶች የመፍረስና የጣሪያ መገንጠል ደርሶባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ እስከ ግንቦት ወር የመጀመርያ ሳምንት ድረስ ከክልሎች በተሰበሰበው መረጃ መሠረት፣ 195,987 ሰዎች በጎርፍ አደጋው ምክንያት መፈናቀላቸውን የኮሚሽሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

‹‹የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያስከተለው ጉዳት የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ቀደም ሲል የተሠሩ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ፣ የመከላከልና የማቅለል ሥራዎች ባይኖሩ ኖሮ ጉዳቱ ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር፤›› ሲሉ አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቀጣይ የክረምት ወቅት ላኒና ተብሎ በሚጠራው የአየር ንብረት ክስተት ተፅዕኖ ሥር የሚወድቅ ከሆነ፣ ከሚዘንበው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ጋር ተያይዞ ቅፅበታዊ ጎርፍና የወንዞች ከመጠን በላይ ሞልቶ የመፍሰስ ዕድል ከፍተኛ ስለሚሆን በሰው፣ በሰብል፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት ያስከትላል፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ የከተማ አስተዳደሮችና ማዘጋጃ ቤቶች በቆሻሻ የተዘጉ ቱቦዎችን የመክፈት፣ አዳዲስ የሚሠሩና ነባር መንገዶች ተገቢው የጎርፍ ማፍሰሻ እንዲኖራቸው የማድረግ፣ የጎርፍ መቀልበሻ አውታሮች የመገንባትና የማጠናከር ሥራዎች ማከናወን እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ በሚጋለጡና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ከመሬት አቀማመጥና በአፈር ባህሪይ ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ ከእነዚህ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ጥናት ላይ በመመሥረት ለጎርፍና ለመሬት መንሸራተት በማይጋለጡ አካባቢዎች በዘላቂነት እንዲሰፍሩ ማድረግ ይገባል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት እየዘነበ ባለው ከባድ ዝናብ በተለይም በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የመሬት መሰንጠቅ እያደረሰ በመሆኑ፣ ለችግሩ ፈጣን ምላሽ መስጠት ካልተቻለ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በዩኒቨርሲቲዎች፣ በምርምር ተቋማትና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጥናት እንዲያካሂዱ በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ሊበጀትለት እንደሚገባም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

‹‹በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየከሰተ ያለው ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የመሬት መሰንጠቅ በአመዛኙ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ላይ መሆኑ የሚደርሰውን ጉዳት ከባድ ያደርገዋል፡፡ በቀጣይም በክረምት ወቅት ከሚጥለው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ጋር ተያይዞ የቅፅበታዊ አደጋዎች መከሰት ዕድል ሰፊ ስለሚሆን፣ እያንዳንዱ በየደረጃው የሚገኝ አስፈጻሚ አካል ያላሰለሰ፣ የተናበበና የተቀናጀ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

የኮሚሽነሩን ሪፖርት ያዳመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በዜጎች ላይ ያንዣበበውን አደጋ የሚመለከተው ሁሉ የቅድመ መከላከል አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት በጋራ እንዲቆም የኮሚሽኑን ጥሪ አስተጋብቷል፡፡

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ አስቴር አማረ በበኩላቸው፣ ‹‹ጎርፍ እንደ ድርቅ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ከቅድመ መከላከል ሥራችን መካከል ለሕዝቡ በተከታታይ ግንዛቤ ሊሰጠው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ በብሔራዊ ደረጃ ከተቋቋመው ኮሚቴ በተጨማሪ ምክር ቤቱም በጎርፍ ቀድመው በተጠቁትም ሆነ፣ በመጪው ክረምት ለአደጋው ሊጋለጡ ይችላሉ የሚባሉ ሥፍራዎችን ሄዶ የሚጎበኝ ቡድን ማቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

‹‹አደጋው ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳይ መቀነስ እንጂ ማስቀረት ስለማንችል፣ ሁላችንም በጋራ ልንቋቋም ይገባል፤›› ሲሉ አቶ አባዱላ የኮሚሽኑን ጥሪ አጠናክረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...