የፌደራል ፍርድ ቤቶች በማይመለከታቸው የመሬት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ፣ በሥራው ላይ እንቅፋት እንደሆኑበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ከዚህ በኋላ ጣልቃ እንዳይገቡ ለማድረግ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተነጋገረ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሬት የማስተዳደር ሥልጣን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቶች የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እየተቀበሉ እያንዳንዱን ክርክር እየሰሙ በመሆናቸው፣ ቢሮው ሥራውን እንዳይሠራ እንቅፋት እየሆነ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ፍርድ ቤቶች ሊመለከቱ የሚችሉት የይዞታ ካሳ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን መጀመርያ የከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች ከተመለከቱት በኋላ በይግባኝ የሚሄድ ከሆነ ብቻ ነው፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ፍርድ ቤቶች ግን በመንግሥት ይዞታዎች መሬት በወረራ ለያዙ አካላት ጭምር ዕግድ እየሰጡ፣ በሥራ ላይ እንቅፋት እየሆኑ መጥተዋል፤›› በማለት ጉዳዩ አስተዳደሩን እንዳሳሰበው አስረድተዋል፡፡
ኅዳር 24 ቀን 2004 ዓ.ም. የወጣው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ አዋጅ የከተሞችን መሬት የማስተዳደር ሥልጣን የከተማ አስተዳደር አካላት እንደሆነ ይደነግጋል የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ነገር ግን ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ የዕግድ ውሳኔዎችን ከመቀበል ጀምሮ ክርክር እያዳመጡ በመሆናቸው፣ በርካታ ቦታዎች ለዓመታት ውሳኔ ሳይሰጥባቸው ቁጭ ብለው ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች በመሬት አስተዳደር ጉዳዮች በከፍተኛ ደረጃ ጣልቃ እየገቡ እንቅፋት መሆናቸውን አቶ ሰለሞን አመልክተው፣ መሬት መተዳደር ያለበት በአዋጁ፣ በከተማው ደንብና መመርያዎች መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ተስተጓጉለዋል ከተባሉት መካከል ከመልሶ ማልማት ቦታዎች መነሳት ያለባቸው ይዞታዎች፣ ለባለሀብት ከተወሰኑ ቦታዎች መነሳት ያለባቸው ይዞታዎች፣ ከመንገድ ግንባታ ቦታዎች መነሳት ያለባቸው ይዞታዎች፣ ለኢንዱስትሪ ከተመደቡ ቦታዎች መነሳት ያለባቸው ይዞታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያራመደ የሚገኘው ሐሳብ በሕግ ምሁራን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የሕግ ምሁራን ይህ ሐሳብ ተቀባይነት እንደማይኖረው ሕገ መንግሥቱን ጠቅሰው ይከራከራሉ፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37፣ ‹‹ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤›› ይላል፡፡
ይህን ሕግ ተፈጻሚ የማድረግ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራዎችን ለማቀላጠፍ የያዘው አዲስ ሐሳብ፣ በዚህ መንገድ ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል የሕግ ምሁራን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን አቶ ሰለሞን የፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት የሥራ መስተጓጎል እየፈጠረ በመሆኑና የከተማው አስተዳደርም የፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት መቆም እንዳለበት በማመኑ፣ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሄዷል ብለዋል፡፡
አስተዳደሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ እየመከረ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚወሰነው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡