Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የቀረበው ክስ የተቀነባበረ ሳይሆን በማስረጃ የተደገፈ...

ዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የቀረበው ክስ የተቀነባበረ ሳይሆን በማስረጃ የተደገፈ ነው አለ

ቀን:

ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ጠየቀ

  ዶ/ር መረራ ጉዲና የተመሠረተባቸው ክስ እሳቸው በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ሲደረግባቸው በሰጡት ቃል መሠረት ሳይሆን ተቆራርጦ የተቀነባበረ መሆኑን፣ በቅድመ ክስ መቃወሚያቸው በመግለጽ ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቃወመ፡፡ የቀረበባቸው ክስ የተቀነባበረ ሳይሆን በማስረጃ የተደገፈ መሆኑንም ለፍርድ ቤት ባቀረበው የመቃወሚያ መቃወሚያ ገልጿል፡፡

      ዶ/ር መረራ በ2008 ዓ.ም. ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን በቅድመ ክስ መቃወሚያቸው መግለጻቸውን ያስታወሰው ዓቃቤ ሕግ፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በሚመሩት የፖለቲካ ድርጅት (ኦፌኮ) ሽፋን ምን እንደተፈጸመና የሚያስከትልባቸው የወንጀል ኃላፊነት በክሱ ላይ በጊዜና በቦታ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ማቅረቡን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር መረራ መቼ፣ የትና እንዴት የወንጀል ድርጊት እንደተፈጸመ በክሱ ላይ እንዳልተገለጸ በመቃወሚያቸው የጠቀሱት አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ ያቀረበውን ማስረጃና የክስ ሁኔታ ለመመዘን ሥልጣን ለተሰጠው ለፍርድ ቤቱ እንደሚተውም አክሏል፡፡

      ዶ/ር መረራ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለን) እና 38ን በመተላለፍ በዋና የወንጀል ድርጊት ተካፋይ መሆናቸውን፣ አመራር መስጠታቸውን፣ የፖለቲካ ድርጅትን ሽፋን በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ፣ የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት እንዲያልፍ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ የሽብር ልሳን ለሆኑ ሚዲያዎች መግለጫ በመስጠት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ፣ አብረዋቸው ከተከሰሱት ግለሰቦችና ድርጀቶች ጋር በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ኃላፊነት እንዳለባቸው ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

ዶ/ር መረራ የቀረበባቸው በወንጀለኛ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112 በሚደነግገው መሠረት ግልጽ  አለመሆኑንና ክሱ ተጣሞ የቀረበ በመሆኑ፣ የሰጡት ቃል ሳይቆራረጥ እንዲቀርብ ያቀረቡትን ተቃውሞ በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግ እንደሚለው የተጣመመ ክስ የለም፡፡ በሰላማዊ መንገድ በሚል ሽፋን የተፈጸመ ሁከትና ብጥብጥ ነው፣ ብጥብጡ እንዲፈጸም አመራር የሰጠ ደግሞ በሕግ ተጠያቂ ነው ብሏል፡፡ ቄሮ ማለት የኦነግ ወጣት ክንፍ ሴል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ የኦነግ ሴል ስንት እንደሆነና በእነማን እንደሚመራ ዝርዝር የመጻፍ ግዴታ እንደሌለበት በመቃወሚያው አቅርቧል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27(2) መሠረት የሰጡት የእምነት ቃል በነፃ ፈቃዳቸው የሰጡትና የፈረሙበት እንጂ፣ እንደ ጠበቃቸው አባባል ተቆርጦና ተጣሞ የቀረበ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

ኦኤምኤን የኦነግ ልሳን ሳይሆን አሜሪካ በሕግ የተቋቋመ ለኦሮሞ ማኅበረሰብ ድጋፍ የሚሰጥ ሚዲያ መሆኑን በመግለጽ የዶ/ር መረራ ጠበቃ ጥብቅና ላልቆሙለት ተከሳሽ መቃወሚያ ማቅረባቸውን የጠቀሰው ዓቃቤ ሕግ፣ ጀዋር መሐመድ የተባሉት ተከሳሽ ሚዲያው የኦነግ ልሳን መሆኑን መናገራቸውንና ሁሉም ተከሳሾች በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር፣ ዜጎች እንዲሞቱና ንብረት እንዲወድም የአመራር ሚና የነበራቸው በመሆኑ ትስስራቸውንና ግንኙነታቸውን ለማሳየትና በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ገልጿል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትን በሚመለከት የዶ/ር መረራ ጠበቆች ጥብቅና ላልቆሙለት መልስ መስጠታቸው ተገቢ ያልሆነና የሕግና ሥነ ሥርዓት አካሄድ አለመሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ሆኖም ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት በመሆኑና አመራር አባላቱ በሕግ ተጠያቂ መሆናቸው አጠያያቂ እንደማይሆን አክሏል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 1/2009ን መተላለፋቸውንና የሕግ ተጠያቂ ስለመሆናቸው የተደነገገ መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል፡፡

ዶ/ር መረራ በ2006 ዓ.ም. የአልሸባብ ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ሊፈጽሙት የነበረውን የሽብር ተግባር ሊኮንኑት ሲገባ፣ ‹‹የመንግሥት ድራማ ነው፤›› ማለታቸው በሕግ ተጠያቂና የወንጀል ኃላፊነትን እንደሚያስከትልባቸው በመግለጽ ተቃውሟል፡፡ በአጠቃላይ ዶ/ር መረራ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁር 130 (1) መሠረት ያቀረቡት መቃወሚያ ከክሱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው መቃወሚያዎች መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ያቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ያቀረቡትን መቃወሚያ ከሕጉ አንፃር በመመርመር ብይን ለመስጠት ለግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...