Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓ የተወጠነበት የሐበሻው ደብረ እስጢፋኖስ

የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓ የተወጠነበት የሐበሻው ደብረ እስጢፋኖስ

ቀን:

ኢትዮጵያውያን ቅዱሳት ሥፍራዎችን ለመሳለም (ለንግደት) እጅግ ከራቀው የጥንት ዘመን ጀምሮ በየዓረፍተ ዘመኑ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ እንደነበር ይወሳል፡፡ እንደዚሁም ተሳላሚዎች ወደ ሮም መምጣት የጀመሩት እ.ኤ.አ. በ1351 መሆኑን ስለ ሰብአ ሰገል በሚናገረው መጽሐፍ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህ መጽሐፍ የመንግሥት መልዕክተኞች ከኢትዮጵያ ወደ ሮም እንደመጡ ሲተርክ፣ ‹‹ትውልዳቸው ከሰብአ ሰገል መሆናቸውን ራሳቸው ተናገሩ›› ይላል፡፡

በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በ1441 በፍሎረንስ ከተካሄደውና ኢትዮጵያዊም ከተሳተፉበት ጉባዔ በኋላ ኢትዮጵያውያን በሮም የሚገኙ የቅዱስ ጴጥሮስ መቃብርና ሌሎች ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም በብዛት ይመጡ እንደነበሩ በቫቲካን የሚገኘው የታሪክ መዝገብ ያመለክታል፡፡ ጆቫኒ አፍሪካኖ (ዮሐንስ አፍሪካዊ) የሚባል አንድ ጸሐፊ በ1526 ዓ.ም. ‹‹ከኢትዮጵያ የመጡ መነኮሳት በፊታቸው እንደ መስቀል ሆኖ የእሳት ምልክት ያላቸው በአውሮፓ ሁሉ ይልቁንም በሮም ይታያሉ፤›› ብሎ ጽፏል፡፡ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን በመልካቸው ምክንያት ፈረንጆቹ ‹‹ህንዳውያን›› ይሏቸው ነበር፡፡

በቫቲካን ከተማ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን በኩል የሚያልፍ ምዕመንም ሆነ ቱሪስት ልዩ አሠራር ያላትን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይመለከታል፡፡ ሥነ ሕንፃው ቀልብን ይይዛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የሐበሻ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተብላ ትጠራለች፡፡ ይህም ከሕንፃው ራስጌ በጣሊያንኛ ‹‹La chiesa di S. Stefano degli Abissini›› ተጽፎ ይታያል፡፡ መንበረ ጴጥሮስ አጠገብ የምትገኘው የሐበሻ ቅዱስ እስጢፋኖስ ከመባሏ በፊት የትልቁ ቅዱስ እስጢፋኖስ  ወይም ካታጋላ ፓትሪቻ ቤተ ክርስቲያን በሚል ስም ትጠራ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የገዳሙ አለቃ የሆኑትና ገዳሙንና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩን ካስጎበኙን አባ አማኑኤል ያገኘነው ‹‹ደብረ ቅ. እስጢፋኖስ የኢትዮጵያዊ ኮሌጅ›› በተሰኘ ታሪካዊ ኅትመት እንደተገለጸው፣ ቤተ ክርስቲያኗ በትልቁ ፓፓ ልዮን በ5ኛው ክፍለ ዘመን (440-461) የተሠራች ናት፡፡ በትልቁ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኙ ታላላቅ ቤተ ክርስቲያኖች አንዷ ነበረች፡፡ ቁጥሯም ባዚሊክ ተብለው ከሚጠሩት ታላላቅ ቤተ ክርስቲያኖች ስለነበር ታላቅ ክብር እንደነበራት ይተረካል፡፡ ብዙ ዘመናት ስላለፋት በየጊዜው መሠራቷና መታደሷ አላቋረጠም፡፡ ይልቁንም ላዲስላኦ የተባለ ጨካኝ የናፖሊ ንጉሥ ከፓፓ ጎርጎርዮስ 12ኛ ጋር ተዋግቶ ስላፈረሳት እንደገና ከመሠረቷ ከታደሰች በኋላ የሮማ ፓፓዎች የእንግዳ ቤቱን ጨምሮ ለኢትዮጵያውያን ነጋድያን (ተሳላሚዎች) መገልገያ እንዲሆኑ ማበርከታቸውና ሮም ለመሳለም የሚመጡ ኢትዮጵያውያንም ከ15ኛው እስከ 18ኛው አጋማሽ ድረስ እንደተቀመጡበት ይወሳል፡፡

የትልቁ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንን ለኢትዮጵያውያን ለመጀመርያ ጊዜ የሰጡ ፓፓ ማን መሆናቸውን የታሪክ ጸሐፍት አይስማሙበትም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ የእንግዳ መቀበያ ቤትና ቤተ ክርስቲያን የሰጧቸው ፓፓ ቀሌምንጦስ 7ኛ (1523-1534) እንደሆኑ ቢናገሩም፣ ከመነኮሳቱ አንዱ የነበረውና ኢየሱሳውያን በኢትዮጵያ በነበሩበት በ17ኛው ምዕት ዓመት እንደጻፈው፣ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከነእንግዳ ቤቱ የሰጡዋቸው ፓፓ ሲክስቶስ 4ኛ (1471-1484) እንጂ ቀሌምንጦስ 7ኛ አይደሉም፡፡የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓ የተወጠነበት የሐበሻው ደብረ እስጢፋኖስ

ደብረ እስጢፋኖስ – በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት የተጀመረበት

በደብረ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያዊ ኮሌጅ ወርቃዊ ኢዮቤል አጋጣሚ አባ አድኃኖም ሥእሉ ‹‹ከ፲፭ኛው ዘመን ኢትዮጵያውያን ነጋድያን በቫቲካን ውስጥ›› (Pellegrini Etiopici in Vaticano dal sec, XV) በሚል ርዕስ እንደጻፉት፣ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ከኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙዎቹ ከፍ ያለ ዕውቀት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ በአውሮፓ ከነበሩት ብዙዎች ሊቃውንት በራሳቸው ፍላጎት ሆነ በመንግሥታቸው መልዕክተኝነት ወደነርሱ እየመጡ ስለኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ ሰፊ ጥናት ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በጊዜው የነበሩት ፓፓዎችና ነገሥታት መሳፍንትና መኳንንት እየጠሯቸው ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ከፍ ያለ ዕውቀት ይቀስሙ ነበር፡፡ ስለዚህ ስለኢትዮጵያ ጥናት በመላው አውሮፓ ሊዘረጋ የቻለው በዚሁ ገዳም አማካይነት መሆኑን ባለ ታሪኮች ይመሰክራሉ፡፡

ስለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ ዕውቀት ያላቸው ካርዲናል ቲሠራን የኢትዮጵያ ኮሌጅ የተቋቋመበት የ25ኛውን ዓመት ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹የአውሮፓ ሊቃውንት ስለኢትዮጵያ ዕውቀት መገብየት የቻሉት ከቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋ ጥናት በአውሮፓ በደብረ እስጢፋኖስ እንደተጀመረ ከሁሉ በፊት የገለጸ ዮሐንስ ፖትከን የተባለ ጀርመናዊ ነው፡፡ እርሱ ‹‹ከለዳዊት›› ብሎ የሚጠራት የኢትዮጵያ ቋንቋ በሮም ከኢትዮጵያውያን እንደተማረም ይናገራል፡፡ ሰኔ 30 ቀን 1513 በግዕዝ ፊደልን ቀርፆ ለመጀመርያ ጊዜ መጻሕፍትን ያሳተመ ዮሐንስ ፖትከን ነው፡፡ ሲያሳትም የረዱት አባ ቶማስ የሚባሉ መነኩሴ ናቸው፡፡ መነኩሴው በመጽሐፉ መቅድም ‹‹ዮሐንስ ፖትከን ጀርመናዊ የቅዱስ ጊየርጊስ ቤተ ክርስቲያን ቆሞስ፣ በኮሎን የዳዊት መጽሐፍ ሲያሳትም እኔ ቶማስ ወልደ ሳሙኤል የኢየሩሳሌም ነጋዴ (ተሳላሚ) በሐምሌ 4 ቀን 1513 ዓ.ም. የኢየሱስ ዓመት ከርሱ ጋር እፈርማለሁ፤›› ብለው ጽፈዋል፡፡ ፖትከን በሥራው ውጤታማ በመሆኑ በቋንቋ ጥናትና መጻሕፍትን በማሳተም ለብዙዎች መልካም አርዓያ ሆነ፡፡

እንደ አባ አድኃኖም አገላለጽ፣ በደብረ እስጢፋኖስ ከነበሩት ከሁሉ ይበልጥ እንደ አባ ተስፋጽዮን መልኅዞ ስለኢትዮጵያ ትምህርት የደከመና ያስፋፋ የለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1548-49 በግዕዝ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የሐዋርያት አኰቴተ ቁርባንና ሥርዓተ ክርስትና በላቲን ተርጉመው አጠናቀው አሳትመዋል፡፡ በፈረንጅ ‹‹ጴጥሮስ ህንዳዊ›› ተብለው ይጠሩ የነበሩት አባ ተስፋጽዮን እንደተመሰከረላቸው፣ በትምህርታቸውና ትህትና በተሞላበት ፍቅራቸው ካገኟቸው የፈረንጅ ሊቃውንት መጻሕፍትን ከግዕዝ ወደ ላቲን ሲተረጉሙ ጴጥሮስ ጓልትየሪ ሲረዳቸው፣ በርሳቸው ምርኩዝነትም ማርዮ ቪቶርዮ የኢትዮጵያ ነገሥታት ስም በተርታ የያዘ መጽሐፍና ትንሽ የግዕዝ ሰዋስው ለመጀመርያ ጊዜ አሳተመ፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ባሳተሙት መጻሕፍት መሠረትነት ነው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት መጀመሩ የሚገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በ1983 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሲካሄድ ጥናታቸውን ያቀረቡት አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት (ዶ/ር)፣ ‹‹በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት አባት መባል ያለባቸው አባ ተስፋጽዮን መልኅዞ እንጂ ኢዮብ ሉዶልፍ አይደለም፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ 

የደብረ እስጢፋኖስ ምክትል አለቃ የነበሩት አባ አድኃኖም ሥእሉ በድርሳናቸው እንዳወሱት፣ በገዳሙ ከተማሩት ፈረንጆች አንዱ ያዕቆብ ወመርስ የተባለው ዶሚኒካዊ የግዕዝና የላቲን መዝገበ ቃላት ለመጀመርያ ጊዜ ጽፎ አሳትሟል፡፡ ዴንማርካዊው ቴድሮስ ጴጥሮስ በበኩሉም ብዙ የኢትዮጵያ መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ እየመጡ ከተማሩት ሁሉ የተማረውን ይበልጥ ከሙያ ያዋለው ጀርመናዊው ኢዮብ ሉዶልፍ ነው፡፡ ሉዶልፍ ከኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ኢየሱስ ተምሮ የኢትዮጵያ ታሪክ ከነትርጉሙና የግዕዝ ግስ ጽፎ አሳትሟል፡፡ የአባ ጎርጎርዮስ በአስተርጓሚነት የረዳው እናቱ ሐበሻ አባቱ ፖርቱጌዝ የሆነው አንጦንዮስ ዳንድራንደ ነበር፡፡

አባ አንጦንዮስ በ1668 ዓ.ም. በሮም ጵጵስና ተሹሞ ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩ፣ እንዲሁም በፕሮፓጋንድ ኮሌጅ የተማሩት በደብረ እስጢፋኖስም ቆይታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊው አባ ጦቢያ ገብረ እግዚአብሔር በ1788 ዓ.ም. የአዶሊስ ጳጳስ ተብለው ወደ ኢትዮጵያ ተልከዋል፡፡ የመጀመርያው በ18ኛው ምዕት ዓመት የተሾሙ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ የሚባሉት አቡነ ጦቢያ፣ የካርዲናል በላርሚኖ ትምህርተ ክርስቶስ ከላቲን ወደ ግዕዝ ተርጉመው አሳትመዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ሰበካ ሁኔታ ለስፍሐተ ሃይማኖት ማኅበር በጻፉት ረዥም ደብዳቤያቸውም በታሪክ ታውቀዋል፡፡

በመጨረሻ ዘመን መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም 11 ዓመታት ተቀምጠው ፈረንጆቹን ሁሉ ያስተምሩ ነበር፡፡ ከርሳቸው የተማሩ እኛስዮ ጉዲና ፍራንቸስኮ ጋሊና ሌሎች ጥቂትቶችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ስለኢትዮጵያ የሚናገሩ ልዩ ልዩ መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ መምህሩ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው እዚያ አሥር ዓመት ከተቀመጡ በኋላ አረፉ፡፡

 የግዕዝ ሥነ ጽሑፍን በጥልቀት በመመርመር የሚታወቁት ኅሩይ አብዱ (ዶ/ር)፣ ‹‹መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (1817 እስከ 1900)›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደሚገልጹት፣ 1948 .ም. በአዲስ አበባ የታተመው ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የግእዝ አማርኛ ሰዋስውና መዝገበ ቃላት የሦስት ትውልድ ሊቃውንት የምርምርና የትጋት ውጤት፣ የሆነው እፁብ መዝገበ ቃላት ሥራ ወጣኝ የነበሩት መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡.

‹‹ግንቦት 14 ቀን 1817 .ም. በአንኮበር ተወለዱት መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከአርባ ቀንም በኋላ በሰኔ 23 ስለተጠመቁ ሰማዕቱ ጊዮርጊስን ለመዘከር ስማቸው ‹‹ክፍለ ጊዮርጊስ›› ተባለ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ሮም እንደደረሱ ቫቲካን (Vatican) ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ግዕዝ ማስተማር ጀመሩ። በዚህም ወቅት ምጽዋና ከረን ሳሉ የጀመሩትን የሮማይስጥ (Latin) ቋንቋ ጥናት በማጠናከር ቀጠሉ። በቆይታቸውም ዘመን ከጣሊያኑ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ሊቅ ጒዲ (Ignazio Guidi) ጋር ይተዋወቃሉ።

‹‹መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ኪዳነ ወልድ እንደተናገሩት፣ ‹‹ሮሜ ሄጄ ከፈረንጅ ሊቃውንት ሁሉ በዕውቀት የሚበልጥ፣ የጽርዕ (Greek) እና እብራይስጥ (Hebrew) እንዲሁም ሱርስት (Syriac) እና ዓረብ አዋቂ ሰው አገኘሁ። ይህም ሰው፣ኢትዮጵያዊ ሊቅ ሆይ! ግዕዝና አማርኛ አስተምረኝ፣ እኔም የፈለግከውን አስተምርሃለሁአለኝ።››

‹‹ይህም ትውውቅ ሁለቱ ሊቃውንት እርስ በርስ እንዲማማሩና ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ምሁራን ይከብድ የነበረውን የአማርኛ ጽሑፎችን ጥናት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ዕርዳታ ጒዲ ሊካንበት አስችሏል። ጒዲ በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እገዛ ካሳተማቸው ሥራዎቹ የመጀመሪያው ‹‹የኢትዮጵያ ምሳሌዎች፣ ግጥሞችና ተረቶች›› የተሰኘው ነው። ሌሎች በእሳቸው እገዛ ከወጡት ሥራዎች መካከል፣ ‹‹የነገሥታት ግጥም›› ‹‹መርሐ ዕዉር›› ‹‹የኢትዮጵያ ቅኔዎች›› ‹‹ፍትሐ ነገሥት›› እና እንደዋና ሥራው የሚቆጠረውን ‹‹የአማርኛጣሊያንኛ መዝገበ ቃላት›› መጥቀስ ይቻላል።

ከ49 ዓመታት በፊት የገዳሙ ምክትል አለቃ አባ አድኃኖም ሥዕሉ እንዲህ ጻፉ፡፡ ‹‹ደብረ እስጢፋኖስ ገዳም በአውሮፓ እውነተኛ የትምህርት መደብር ሆኖ ሳያቋርጥ በዚያ የተማሩ ብዙ ሊቃውንት ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ለመጭው ትውልድ አስረከቡ፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በዘረጉት ጽሑፍ ሌሎችም ተስበው ወደ ኢትዮጵያ እየሄዱ ጥናታቸውን አጣርተው ስላወቁ ሌሎችንም እንዲነሳሱና ብዙ የዕውቀት ስሜት እንዲኖራቸው አደረጉ፡፡ ይህ ስሜት ሲወርድ ሲዋረድ የኢትዮጵያ ኮሌጅ እስኪመሠረት ድረስ ቆየ፤ አሁንም በኮሌጁ በኩል ይቀጥላል፡፡››

መቶ ፈሪ (99 ዓመት) ያስቆጠረውና የኢትዮጵያና ኤርትራ ቤተ ክርስቲያናት የሚገለገሉበት የኢትዮጵያ ኮሌጅ (Pontificio Collegio Etiopico in Vaticano) ድልድዩን በመቀጠል የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እያደረገ ለኅትመት እያበቃ መሆኑ፣ በሁለቱ ቤተክርስቲያናት የጋራ ሥራም 17ቱ የግዕዝ ቅዳሴያት ለኅትመት ዝግጁ መሆናቸውም ይወሳል፡፡

በሔኖክ ያሬድ፣ ቫቲካን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...