Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከድርሰቱ ማማ

ከድርሰቱ ማማ

ቀን:

አንቺ መጣፍ ሂጂ ዕድል እንደመራሽ

እኔ ለንፋሱ ለአየሩ ሰጠሁሽ

ሰጠሁሽ ለንፋስ ሂጂ እንግዲህ በቃ

አላገኘሁም ሰው ለአደራ እሚበቃ

በጣም አትጠጊው ሸውሻዋ ነው እሱም

ገንጥሎ በትኖ እንዳይጥልሽ የትም

በይ እንግዲህ ሂጅ ዕድል በመራሽ

ጨርቅ ሆኖ መንገዱ ካሰብሽው ያድርስሽ

እኔ የማዝንልሽ እኔ የምፈራው

ከምሁራን ሠፈር እግር እንዳይጥልሽ ነው፡፡

ይህ ‹‹መልዕክት ለወዳጆቼ›› በሚል ተጽፎ ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. አንባቢ ከበቃው ከደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ የግጥም መድብል ‹‹ስንበት›› ከሚለው ግጥም ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

 በደብረ ማርቆስ እንዶዳም ኪዳነ ምሕረት አካባቢ በ1902 ዓ.ም. የተወለዱት ደራሲ ሐዲስ አለማየሁ በግጥም መድብል ብቅ ሲሉ ይሄ የመጀመሪያቸው ይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ በሚታወቁበት በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰታቸው የግጥም ችሎታ እንዳላቸው ማስተዋል ይቻላል፡፡

 ከረዥም ልብ ወለዶች በሚመደበው የፍቅር እስከ መቃብር ድርሰታቸው የአገዛዝ ሥርዓት አስከፊ ገጽታዎችና ማህበራዊ ትስስሮችን አሳይተዋል፡፡ ወንጀለኛው ዳኛ፣ የልም እዣት የተሰኙት ድርሰቶቻቸውም ከፍቅር እስከ መቃብር ቀጥሎ በማህበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ስራዎቻቸው ናቸው፡፡

ደራሲ ሐዲስ በባህላዊው የትምህርት ዘርፍ ጾመ ድጓ፣ ዜማና ቅኔን በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና ዲማ ጊዮርጊስ ተምረዋል፡፡ የትውልድ ቀያቸውን እንዶዳምን ለቀው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በስዊድን ሚሲዮንና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች የዘመናዊ ትምህርት ተምረዋል፡፡ ደራሲው ከስነ ፅሁፍ ባሻገር በልዩ ልዩ ስራዎችም የተሳካላቸው ነበሩ፡፡

 በ1966 ዓ.ም. ጡረታ እስኪወጡ በመምህርነት፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜም በአርበኝነት፣ በኢየሩሳሌም፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያም በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት ማዕረግ አገራቸውን አገልግለዋል፡፡

የልብ ወለድና የኢ-ልብወለድ ይዘት ያላቸው ስምንት ድርሰቶቻቸውን የደረሱትም ከሥራቸው ጎን ለጎን ነው፡፡ ለሥነ ጽሑፍ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው እኚህ ደራሲ በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰታቸው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት መሸለማቸውን፣ በ1991 ዓ.ም. ደግሞ በሥነ ጽሑፍና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ባደረጉት አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደሠጣቸው ከሕይወት ማህደራቸው ማወቅ ይቻላል፡፡

‹‹አቶ ሀዲስ የእንስሳት መብት ተከራካሪም ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት አንዲት ጦጣ ከጫካ  አምጥተን ግቢ ውስጥ አስረናት ነበር፡፡ እሳቸው ይኼንን ሲያዩ ‹በሉ መልሷት ከዘመዶቿ ነጥላችሁ ለእናንተ መጫወቻ እዚህ አመጣችኋት፤› በማለት ስለተቆጡ ጦጣዋ ወደ መኖሪያዋ እንድትመለስ አደረጉ›› በማለት የአቶ ሀዲስ ዓለማየሁ የእህት ልጅ ጽጌረዳ አበበ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ስለ ድርሰት ሲወራ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀስ ኢትዮጵያውያን ደራሲዎች መካከል  የሆኑት አቶ ሀዲስን ለመዘከር በትውልድ ከተማቸው ደብረ ማርቆስ የተለያዩ ነገሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም የሀዲስ ዓለማየሁ የባህልና ጥናት ተቋም ተቋቁሟል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ በባህል ማዕከሉ ወጪ የተገነባው ሐውልታቸው ተመርቋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከነሐስ የተሠራው ሐውልት 5.5 ሜትር ርዝማኔ አለው፡፡ ግንባታውም ከዓመት በላይ መፍጀቱን የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) ደራሲው ‹‹የላቀ ሰብእናና ትሁት ልቦና ነበራቸው፡፡ የእሳቸውን የሥነ ጽሑፍ ሥራም ያላነበበ አለ ለማለት አያስደፍርም›› በማለት ከስነፅሁፍ ባሻገር መልካም ባህሪ ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የልም እት፣ ፍቅር እስከ መቃብርና ወንጀለኛው ዳኛ የመሳሰሉት ሥራዎቻቸው ልብ ወለድ ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ፣ የባህል፣ የቋንቋና የመልክዓ ምድር ወዘተ ዕውቀቶች ለትውልድ ማስተማር የሚችሉ ናቸው፡፡ ‹‹ለምሳሌ በፍቅር እስከ መቃብር ታሪኩ ከተነሳበት ከማንኩሳ ጀምሮ እስከ ተቋጨበት ጎሐ ጽዮን የአርሶ አደሩን ኑሮ፣ የቤተክህነት ትምህርትና ሥርዓትን፣ ውጣ ወረዱና ድካሙን፣ በወቅቱ የነበሩትን የአካባቢ መሪዎች ባህሪ እስከነ መገለጫቸው፣ እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚያሳይ ዘመን የማይሽረው እውቀት ለትውልድ አስተላልፏል፤›› በማለት የደራሲውን ሥራዎች አሞካሽተዋል፡፡ በዘመኑ የነበረውን አገዛዝ በሥራዎቻቸው መገሰፅ የቻሉ መሆናቸውም ጀግና እንደሚያስብላቸውም ተናግረዋል፡፡ እንደ እሳቸው ያሉ ተተኪ የጥበብ ሰዎችን ለማፍራት ባለድርሻዎች ሁሉ በርትተው መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

በ1996 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለዩ በተለያየ ጊዜያት የጻፏቸው ግጥሞች ተሰባስበው መታተማቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ጽጌረዳ አቶ ሀዲስ ለሕክምና ወደ ባህር ማዶ በወጡበት ጊዜ ሁሉ የግጥም መጽሐፋቸውን የመጨረስ ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሥራቸውን ከዳር ሳያደርሱ ሞት ቀደማቸው፡፡

‹‹መሞታቸውን ሰምቼ ወደ ቤታቸው ስሄድ ያልተቋጨ ሥራቸውን ጠረጴዛ ላይ አገኘሁት፤›› በማለት አሳትሞ ለአንባቢ የማድረስ ኃላፊነቱ በእሳቸውና በወንድማቸው ትከሻ ላይ እንደወደቀ ይናገራሉ፡፡ የደራሲው ወራሽ የሆኑት ጽጌረዳ (ዶ/ር) ለደራሲው በተደረገው ዝክርና የግጥም መድበሉ ለህትመት በመብቃቱ ‹‹በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት በአንድ ወቅት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ መውጣቱን አስታውሰው፤ ስራው ፈር የለቀቀና የደራሲውን ሥራ የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በፈረንሣይኛ ቋንቋ በጥንቃቄ ተተርጉሞ በቅርቡ ገበያ ላይ እንደሚውል ይናገራሉ፡፡

  ባለፈው ቅዳሜ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው የግጥም መድበላቸው 38 ግጥሞችን አካቷል፡፡ ‹‹በወጣትነትና በሥራ ዘመናቸው ያጋጠሟዋቸውን ተግዳሮቶች ለመቁዋቋም የተከተሉትን ሥልት የሚያሳዩ እንዲሁም በጡረታ ዘመናቸው የዕድሜና የሕመም ጫና የፈጠረባቸው ምሬትን የሚገልጹ፤›› በማለት የግጥሞቹ ኢርታአ ዶ/ር ታዬ አሰፋ በመድበሉ መግቢያ ላይ የግጥሞቹን ይዘት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ታላቅ ነው አባትህ››፣ ‹‹ነህ አጉል ቅርንጫፍ››፤ ‹‹ነበረ አንድ መነኩሴ›› ፣ ‹‹ዳኝነት››  እና ሌሎችም በመድበሉ የተካተቱ  ግጥሞች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ስለነበረው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ስርዓት፣ የማህበረሰቡን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚሄሱ መሆናቸውን አርታኢው አስተያየት ሰተዋል፡፡ ከመድበሉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በባህል ተቋሙ ለታቀፉ ወጣቶች ድጋፍ የሚደረግበት መሆኑ ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...