Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ሆስፒታላችን በሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና የልቀት ማዕከል ነው ለማለት ይቻላል››

  ወ/ሮ አደይ አባተ፣ የኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች  ሆስፒታል ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር

  ወ/ሮ አደይ አባተ ኪዮር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል ኤክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተወለዱትና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ አቅንተው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽንና ፋይናንስ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ሲያትል በሚገኘው የቦይንግ አውሮፕላን ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው ያገለገሉ ሲሆን፣ በዋሽንግተን ዲሲ ለመከላከያ የሚውል ሚሳይል ማምረቻ ኩባንያ ውስጥም የፕሮግራም ማኔጀር ነበሩ፡፡ ለቡዝ አለን ሀሚልተን ሰብ ኮንትራክተርም አገልግለዋል፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በሆስፒታሉ እንቅስቃሴ ዙርያ አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች  ቢገልጹልን?

  ወ/ሮ አደይ፡- ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል በተፈጥሮ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናትና ልጆች ያለምንም ክፍያ በነፃ ዘመናዊና የተሟላ የቀዶ ሕክምና፣ ፊዚዮቴራፒና የመሰል ማስተካከያ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝና መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ነው፡፡ ሆስፒታሉ የተቋቋመው ሐምሌ 19 መናፈሻ አጠገብ ሲሆን፣ ከተገነባም ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ሥራውን ከጀመረ ግን ስምንት ዓመቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ  የልጆች፣ የአዋቂዎች የተሟላ የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒክ፣ ሙሉ የምርመራ ማዕከል፣ አራት የቀዶ ሕክምና ክፍሎች የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ክፍል፣ ፋርማሲና ላቦራቶሪ አለው፡፡ ሆስፒታሉን ያቋቋሙት በአሜሪካ የኪዮር ኢንተርናሽናል መሥራችና የአጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ስኮት ሐርሰን ናቸው፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የሆስፒታሉ ወጪ በማን ነው የሚሸፈነው?

  ወ/ሮ አደይ፡- የሆስፒታሉን ወጪ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየሸፈኑ ያሉት አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ የሚገኘው የሬስ ጆንስ ፋውንዴሽን መሥራችና ባለቤት ሚስተር ሬስ ጆንሰን ሲሆኑ፣ ሌሎች አሜሪካውያን ባለሀብቶችም የበኩላቸው አገዛ ያደርጉልናል፡፡ በተለይ ዩኤስአይዲ እና ሲቢኤም የተባሉት ተቋማት ለኤክስሬይና ለቀዶ ሕክምና የሚውሉ መሣሪያዎችን በመለገስ አግዘውናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉን ያቋቋሙት ባለሀብቱ ወጪውንም በቀጣይነት ለምን አይሸፍኑም?

  ወ/ሮ አደይ፡- ባለሀብቱ በወቅቱ ከራሳቸው ገቢ ቀንሰው ሆስፒታሉን መሥርተዋል፡፡ ለተወሰኑ ዓመታትም ወጪውን ሲሸፍኑ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የሕክምና ተቋሙ ከአንድ ግለሰብ በሚገኝ የገንዘብ ሽፋን ብቻ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለዚህ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት እየተጠናከረና የተጠቃሚውም ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ሌሎች በጎ አድራጊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን መሻት ግድ ሆነ፡፡

  ሪፖርተር፡- ለሕክምና ከሚመጡት መካከል አብዛኞቹ ምን ዓይነት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው?

  ወ/ሮ አደይ፡- ብዙዎቹ የአጥንት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክለብ ፉት (የተቆለመመ የእግር መጫሚያ) ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ እንዲሁም ጉልበትና ጉልበት የመጋጨት፣ የአከርካሪ ችግሮች ያሉባቸው፣ በመውደቅ የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው ሁሉ አሉ፡፡ በእሳት ቃጠሎ አደጋ የቆዳ መጨማደድ ችግር ያለባቸው ብዙ  ልጆች ነገር ግን በዚህ ጉዳት ለሚደርስባቸው ልጆች ያዘጋጀነው አልጋ አምስት ብቻ ነው፡፡ ሆስፒታሉ የሚቀበለው ደግሞ ባለው አልጋ ቁጥር ስለሆነ ለሕክምና በሚመጡት በዚሁ መጠን ቁጥራቸው አነስተኛ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉ በተሟላ የሕክምና መሣሪያ የተደራጀ ነው ወይስ ገና ይቀረዋል?

  ወ/ሮ አደይ፡- ትልቁ ጥቅማችን እጅግ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን መያዛችን ነው፡፡ ወይም በየትኛውም ያደጉ አገሮች ውስጥ ያለው ዓይነት መሣሪያ በኛም ሆስፒታል መኖሩን በእርግጠኝነት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ኪዮር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል በአገር ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ለየት የሚያደርገው ምንድንነው?

  ወ/ሮ አደይ፡- በልጆች አካል ጉዳት ላይ ከኪዩር ሆስፒታል በስተቀር በብዛት የሚሠራና ስፔሻላይዝ ያደረገ ሌላ ሆስፒታል የለም፡፡ ነገር ግን አንድ ታካሚ ጥቁር አንበሳ ወይም ሌላ ሆስፒታል ሂዶ ይኼን ዓይነቱን ሕክምና አያገኝም ማለት አይደለም፡፡ የልጆች አጥንት ሕክምና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረገ ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገን በልጆች አጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ ብቻ ሳይሆን ለአዋቂዎችም ጭምር ነው፡፡ በተረፈ ለአዋቂዎች የጉልበት መቀየሪያ (ኒል ሪፕለስመንት) በሆስፒታላችን ብቻ ይሰጣል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ከዚህም ሌላ ለየት የሚያደርገን ለልጆች ወይም ስኳር፣ ኩላሊትና ሌሎች በሽታዎች ላለባቸውና በዕድሜ ለገፉ አዋቂዎች ከቀዶ ሕክምና በፊት ሰመመን ወይም ማደንዘዣ (አኒስቴዢያ) አሰጣጥ ነው፡፡ በሆስፒታላችን ውስጥ ሰመመን የሚሰጡ ነርሶች ብቻ ሳይሆኑ ሁለት ዶክተሮችም አሉን፡፡ የሰመመን መርፌ ማለት ለተወሰነ ሰዓት በማስተንፈሻ መጠቀም ማለት ነው፡፡ በታካሚው ላይ አንድ ችግር ቢከሰት ሰመመን ሰጪው ባለሙያ በቀጣዩ ምን መሠራት እንዳለበት የሚያውቀው፡፡

  ሪፖርተር፡- በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉት ልዩ ልዩ የሕክምና ባለሙያዎች በቋሚነት የሚሠሩ ናቸው ወይስ ጥሪ ሲደረግላቸው እየመጡ የሚሠሩ?

  ወ/ሮ አደይ፡- ሁሉም ቋሚ ናቸው፡፡ በተረፈ ከአንገት በላይ፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን የሚያክሙት በዓመት ሁለቴ ወይም ሦስቴ እየመጡ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነሱም የሚመጡት በማስታወቂያ ጥሪ ሲያደርግ ነው፡፡ ካሉን የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ስድስቱ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ የቀሩት የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞቻችን ኬንያ በሚገኘው የማሰልጠኛ ማዕከላችን ገብተው በልጆች የአጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ ሰልጥነው የተመለሱ ናቸው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሐኪምም አለን፡፡

  ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በሕክምና ላይ ያሉት ሕፃናት ስንት ይሆናሉ?

  ወ/ሮ አደይ፡- በጠቅላላው 50 ሕፃናት ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ጋር ያላችሁን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

  ወ/ሮ አደይ፡- በጣም ቅርብ የሆነ ግንኙነት ያለን በተለይ ከአጥንት ቀዶ ሕክምና  ዲፖርትመንት ጋር ነው፡፡ አጥንት ሕክምና ላይ የሚማሩ ዶክተሮች ሆስፒታላችን ይመጡና ከኛ ዶክተሮች ጋር በሕፃናት የአጥንት ቀዶ ሕክምና አብረው እየሠሩ፣ እየሰለጠኑና ስፔሻላይዝድ እያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የአነስቴዢያ (የሰመመን) ተማሪዎች ናቸው፡፡ እዚህ እየመጡ በአንስቴዢያ አሰጣጥ ላይ ስልጠና ይከታተላሉ፡፡

  ሪፖርተር፡-  ኪዩር ኢንተርናሽናል የልጆች ሆስፒታልና የልቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኤክስለንስ) ነው ለማለት ይቻላል?

  ወ/ሮ አደይ፡- እንችላለን፡፡ ስም ብቻ እንዳይሆንም አጥብቀን እየሠራን ነው በተለይ የሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና እና አነስቴዢያ ላይ የልቀት ማዕከል ነን ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሲባል ሌሎች አገሮች ያመጡትና እኛም የተቀበልናቸው መስፈርቶች ስላሉ ማሟላት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡትን ስታንዳርዶች ለማሟላት የሚቀሩን አሉ፡፡

  ሪፖርተር፡-  ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ነው?

  ወ/ሮ አደይ፡- ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ከቢሮው ጋር በቅርበት እየተረዳዳን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ ሚኒስቴሩ ይቆጣጠረናል፡፡ የተሳሳተ ነገር ካለ ያርመናል፡፡ ከዚህ የበለጠ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በሕፃናት አጥንት ቀዶ ሕክምና ላይ በይበልጥ እኛ ስለምንሠራ የዕውቀት ሽግግሩ ላይ መተጋገዝ ወይም ማዳበር ይኖርብናል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆስፒታሉን የማስፋፋቱን ጉዳይ እንዴት ይዛችሁታል?

  ወ/ሮ አደይ፡- የማስፋፋት ሥራ ጀምረናል፡፡ አዲስ ያስገባነው የመልሶ የማስተካከያ (ሪሀብሊቴሽን) ሕክምና ዋርድ በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ከዚህም ሌላ የአከርካሪ አጥንት ላይ ችግር ያለባቸው ልጆች በብዛት ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ካሉን ሌላ ሁለት ተጨማሪ የቀዶ ሕክምና ክፍል ለማቋቋም አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ የሚቋቋመው ክፍል የአከርካሪ አጥንት ችግር ላለባቸው ልጆች አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡-  ለአዋቂዎች ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀምሯችሁ አቋርጣችኋል፡፡ ለምን?

  ወ/ሮ አደይ፡- 95 ከመቶ ያህሉ አገልግሎታችን ለሕፃናት ብቻ ነው፡፡ የተቀረው ግን እየተከፈለ የሚሰጥ ሕክምና ሲሆን፣ ለዚህም የሚሆን አራት አልጋዎች አሉ፡፡ የምንሰጠው አገልግሎት የታፋ መቀየር ነው፡፡ ይህም ከባድ ቀዶ ሕክምና የሚጠይቅ ነው፡፡ አንድ ታካሚ ውጭ አገር ሄዶ ከሚያገኘው ሕክምና የበለጠ ሕክምና እንሰጣለን፡፡  የአዋቂዎች ሕክምና ለተወሰነ ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆነን ለማድረግ ሲባል ነው የጀመርነው፡፡ ምክንያቱም ዕድሜ ልክ በዕርዳታውና በልመና መኖር የለብንም፡፡ 20 ከመቶ ያህል ገቢያችንን በራሳችን ማሰባሰብ አለብን በሚል መንፈስ የተጀመረ ነው፡፡ 95 ከመቶ በነፃ አገልግሎት ሰጥተን የቀረውን አምስት በመቶ ያህሉ እያስከፈልን አገልግሎት ብንሰጥ 20 በመቶ ያህል ገቢ ልናገኝ እንችላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ለጊዜው ተቋርጧል፡፡ ይህም የሆነው አገልግሎቱና አፈጻጸማችን ከአገሪቱ ሕግና ደንብ ጋር ስላልተጣጣሙ ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ በተቋረጠበት ጊዜ ሕክምና የጀመሩ የቀድሞ ታካሚዎችን እንድናክም ተፈቅዷል፡፡ በተረፈ መደበኛውን አገልግሎት ለመቀጠል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ውይይት እያደረግን ነው፡፡

   

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የማሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎትና የቤተሰብ ዕቅድ

  በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይም በገጠራማ ቦታዎች በቂ የሆነ ግንዛቤ ባለመኖሩ የተነሳ እናቶች በወሊድ ምክንያት እየሞቱ ይገኛል፡፡ የእናቶችን ሞት...

  ሴት የሕግ ባለሙያዎችን ለአገራዊ ችግሮች መፍትሔነት

  በ1980ዎቹ መጨረሻ የተመሠረተው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በሦስት አሠርታት ውስጥ በዋናነነት ለሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት፣ አድሏዊ ሕጎችና ተግባራት እንዲስተካከሉ በመታገል ለኅብረተሰቡ...

  ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነትና ንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሻገር የቆመችው ‹‹ትምራን››

  ‹‹ትምራን›› በሴት ስም የምትጠራ የሲቪል ማኅበር ስትሆን የተቋቋመችውም በመጋቢት 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ የተቋቋመችውም ኢትዮጵያውያን ሴቶች በፖለቲካና በሕዝብ አስተዳደር መስክ ፍትሐዊ ውክልናና ትርጉም ያለው ተሳትፎ...