Wednesday, June 12, 2024

የሶማሊያ አዲሱ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝትና የሁለት አገሮች የወደፊት ተስፋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት አዲሱ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና የአገሪቱን የጦር ኃይል ለማጠናከር ስምምነት አድርገዋል፡፡

ረቡዕ ሚያዝያ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተሰጠው የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሁለቱም መሪዎች በጋራ እንደገለጹት በሁለት ዓመት ውስጥ አልሻባብን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያውያን ሶማሊያውያን የፀና መንግሥት እንዲመሠርቱና ደኅንነታቸው እንዲረጋገጥ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሶማሊላንድን በተመለከተ ከሶማሊያ ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የምታደርገው ግንኙነት ቀጥተኛ እንዳልሆነና ቅድሚያ የፌዴራል መንግሥቱን በማሳወቅና በማስፈቀድ የሚከናወን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በገዛ ራሷ ነፃነቷን ካወጀች 25 ዓመታት የሞሉዋት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ በቅርቡ ለተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበትንና ኢንቨስት እያደረገች ያለበትን የበርበራ ወደብ በከፊል ማከራየቷ አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሶማሊላንድን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሶማሊያውያን ከማገዝ ውጪ ሌላ ድብቅ አጀንዳ የላትም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንዲት ሶማሊያን›› ብቻ እንደምታውቅም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሁለቱ አገሮች ጥያቄዎች የሚመለሱት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ሲቋቋም ነው የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶችን ለመተግበር ውይይትም ተደርጓል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም፣ የፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገሮች አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ቀደም ሲል በደርግ ዘመን በተጀመረው የእርስ በርስ ግጭት ቀጥሎ፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ በጎረቤት አገር ሶማሊያ በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት የዛይድ ባሬ መንግሥት ሊበተን ችሏል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሶማሊያ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆኖ ቆይታለች፡፡

በዚህም ምክንያት የሽብርተኛ ድርጅቶችና የአክራሪ ኃይሎች መናኸርያ በመሆን፣ የሶማሊያ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አጥቶ በመላ ዓለም ሲበተንና በስደት ሲማቅቅ ቆይቷል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ጎረቤት አገሮች በሶማሊያ ለራሳው የሚመች መንግሥት ለማቋቋም የተለያዩ የሰላም ሒደቶችና የእርቅ መድረኮች ሲያዘጋጁ ታይተዋል፡፡ በተለይ ኬንያ፣ ጂቡቲና ኢትዮጵያ በአካባቢው የተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህም በመነሳት የተለያዩ መሰል የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ ነበር፡፡

በአገሪቱ የቆየው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወደ አንድ ጫፍ የተገፋው ግን እ.ኤ.አ በ2006 በተለይ በደቡባዊ ሶማሊያ ተቋቁሞ መላ አገሪቱን በቁጥጥር ሥር በማዋል ላይ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የተባለ ስብስብ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን (አልቃይዳ) ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው ተብሎ ይታማ ነበር፡፡

ስብስቡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር የፖለቲካ ሹክቻ ያላቸው በርከት ያሉ የዓረብ አገሮች ከኋላ ይደግፉታል ተብሎም ይነገር ነበር፡፡ በድንበር ሳቢያ ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረው ፍጥጫ ያልበረደለት የኤርትራ መንግሥት ደግሞ፣ የዚሁ ድጋፍና ትብብር ዋና አስተባባሪ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አጣሪ ኮሚቴ በሪፖርቱ በተደጋጋሚ አረጋግጧል፡፡

ኅብረቱን ለመበተን ኢትዮጵያ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዷ የሚታወስ ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር የውክልና ጦርነት ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥታት ድጋፍ የተቋቋመው በወቅቱ የነበረው የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ጣልቃ እንድትገባ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ በወቅቱ ስብስቡን በወታደራዊ ኃይል መበተን ተችሎ ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ ስብስብ የቀረው የወጣቶች ክንፍ አልሻባብ የተባለው አክራሪ ቡድን መልሶ በማንሰራራት ተደጋጋሚ የሽብር ተግባራት ሲፈጽም መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

በአንፃሩ ደካማው የሽግግር መንግሥት ራሱን መከላከል በማይችልበት ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ጥበቃ በቅርቡ እስከተካሄደው ምርጫ ድረስ እየተንገዳገደ ቆይቷል፡፡

እምብዛም የኢትዮጵያ ድጋፍ ያልተቸራቸው ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩት አዲሱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ምርጫውን ማሸነፍ ከመቻላቸውም በላይ፣ በጎረቤት አገሮችና በአንዳንድ አገሮች ጉብኝት ሲያካሂዱ ሰንብተዋል፡፡

አዲሱ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እምብዛም መልካም ግንኙነት አልነበራቸውም ቢባሉም፣ በኢትዮጵያ ይፋዊ የመጀመሪያ ጉብኝት ከማድረጋቸው በፊት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ እንደሚሉት፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት የላቸውም የሚለው ግምገማና ድምዳሜ ከጥርጣሬ ያለፈ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ለመግባት ምንም ፍላጎት እንደሌላትና በሶማሊያ ሕዝብ ከተመረጠው አካል ጋር ተባብሮ መሥራት የኢትዮጵያ መርህ እንደሆነ ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

ሁለቱም መሪዎች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ ፕሬዚዳንት ፎርማጆ ሶማሊያ ወሳኝ የተባለውን የፖለቲካ ሽግግር እንድታደርግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ደግሞ ለአፍሪካ ኅብረትና ለኢጋድ አባል አገሮች ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ለአሚሶም ወታደራዊ አስተዋጽኦ ላደረጉ አገሮች፣ እንዲሁም ደግሞ ኬንያና ኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳው ውለታ እንደዋሉላቸው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀውና የሶማሊያ ቀጣይ ዕድል ላይ የሚመክረው የለንደኑ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2020  የተረጋጋች ሶማሊያ ለመፍጠር የቀረበው ንድፈ ሐሳብ ላይ ይመክራል ተብሎ በሚጠበቀው በለንደኑ ጉባዔ፣ የኢጋድና የኢትዮጵያ አቋም ወሳኝ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጠንካራና የተቀናጀ ሐሳብ ይዘው እንደሚቀርቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ቀደም ሲል በናይሮቢ የሶማሊያ ስደተኞችን በተመለከተ ኢጋድ አንድ ጉባዔ ያካሄደ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበዓለ ሲመቱ ቀጥሎ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው የመከሩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ የሶማሊያ ስደተኞች ጉዳይ፣ የሶማሊያን የጦር ኃይል ማጠናከር፣ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ድርቅና ረሃብ ለማስቀረት ከኢትዮጵያ የመፍትሔ ሐሳብ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት ከአፍሪካ ቀንድም ሰፋ ያለ ኢጋድ መር የሆነ የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ኅብረት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ከሱዳን፣ ከኬንያና ከጂቡቲ ጋር የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች  ስትራቴጂካዊ ትስስሩን ያፋጥናሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

በመግለጫው ባይገለጽም ሪፖርተር ከታማኝ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት በዚህ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው የሁለቱ አገሮች ድንበር እንዲካለል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ቀረበ የተባለው አቋም ድንበርን ማካለል ብቻ ሳይሆን፣ ድንበር የለሽ ንግድና የሰዎች ዝውውር ዞን ለመፍጠር መንቀሳቀስ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም እስከ ዛሬ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት፣ ይህንን የሚከታተል ከፍተኛ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን እንዲቋቋም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ‹‹የበፊቷ ኢትዮጵያና አዲሲቱን ኢትዮጵያ መለየት ያቃታቸው›› ያሏቸው ሰዎች፣ ኢትዮጵያን እንደ ወራሪ አገር የመመልከት አባዜ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት 25 ዓመታት በገዛ ፈቃዷ ነፃነቷን ካወጀችው የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ጋር ይፋዊ ሊሰኝ የሚችል ግንኙነት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ በስፋት ቢነገርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን አስተባብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የምታውቀው አንዲት የሶማሊያ ሪፐብሊክ ብቻ ነው፡፡ ለሌላ ግዛት ዕውቅና የመስጠት ፍላጎት የላትም ብለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ ዛሬ ከሶማሊላንድ ጋር ሲያደርገው የቆየው የውጭ ግንኙነት ሞቃዲሾ የሚገኘውን ፌደራል መንግሥት በማስፈቀድና በማሳወቅ ነበር፡፡

‹‹የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ጉዳዮች የሶማሊያ የፌዴራል መንግሥቱ ብቸኛ ኃላፊነት እንደሆኑ እናምናለን፡፡ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ አቋም ግልጽና መርህን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሶማሊያዊያን ከማገዝ ውጪ ሌላ ፍላጎት የለንም፤›› ብለዋል፡፡

በሶማሊላንድ ግዛት በተለይ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን እንድትጠቀም የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ሶማሊላንድ የወደብ አገልግሎቱን ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለ30 ዓመታት ማከራየቷና በአካባቢው ወታደራዊ የጦር ሠፈር እንዲመሠረት መፍቀዷ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ በበጎ ዓይን የሚታይ አይደለም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡

 የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በየመን ላይ የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ያለው 28 አገሮችን ያቀፈው የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ቡድን ዋና አባል ስትሆን፣ የአሰብን ወደብ በተመሳሳይ ለ30 ዓመታት በመከራየት ለኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ መስጠቷ በተለያዩ ዘገባዎች ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊላንድ ጉዳይ ላይ እንዲህ ዓይነት የከረረ አቋም ሲያንፀባርቅ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ሲገመት የነበረው ጉዳይ ውኃ የተቸለሰበት ይመስላል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽና የአካባቢያዊ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት መልካም አጋጣሚ ሊፈጥርላት ይችላል እየተባለ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -