Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ያልወጣላቸው ምርቶች በሦስተኛ ወገን ማረጋገጫ እንዲገቡ ሊደረግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ያልወጣላቸው ምርቶች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ፣ የሦስተኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ሊደረግ ነው፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ሥርዓቱን ለመቆጣጠርና የሸማቾችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሦስተኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫ አስመጪዎች እንዲያቀርቡ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ድንገተኛ ግዢዎችን በማከናወን መቆጣጠር እንደሚጀምር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በንግድ ሚኒስቴር ላይ ባከናወነው የክንዋኔ ሒደት፣ ደኅንነታቸውና ጥራታቸው ያልተጠበቀ ምርቶች በገፍ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን የደረጃ መሥፈርት በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በላብራቶሪ ተመርምረው ደረጃቸውን የማያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጦ እንዲታገዱ ከተደረገ በኋላ፣ ሚኒስቴሩ በአዋጅ ከተደነገገው በተቃራኒ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲለቀቁ አድርጓል፤›› የሚል ሪፖርት በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በመቅረቡ ይኼ ለምን እንደሆነ ለሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ጥያቄ ቀርቧል፡፡

የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በቋሚ ኮሚቴው መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ መሆኑንና ለከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ተብለው እንደሚገቡ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ደረጃ የሚያሟሉ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ መግባት የሚችሉት የሦስተኛ ወገን የጥራት ማረጋገጫ ሲያቀርቡ ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ዘያድ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የተጣለባቸው ምርቶች 146 ናቸው፡፡

ከዚህ ወጪ ያሉ ምርቶች የጥራት ደረጃ የማቅረብ ግዴታ እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ አሠራር ሊቆም እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ አሰድ፣ ከዘንድሮ ጀምሮ የኢትዮጵያን አስገዳጅ የጥራት ደረጃ እንዲያሟሉ ግዴታ ያልተጣለባቸው ምርቶች ከሚኒስቴሩ ጋር ከሚዋዋሉ የሦስተኛ ወገን የጥራት ደረጃ አረጋጋጮች ሰርተፍኬት እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኮንትሮባንድና ናሙናዎችን አጭበርብረው ምርቶቻቸውን የሚያሳልፉ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ድንገተኛ ግዢ መፈጸም እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡ ይኼ ሥርዓትም ራስን በራስ መልሶ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች