Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

  የብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ጉዳይ የመንግሥትን ጉልበት ከማፈርጠም፣ ከግዛት ማስፋፋት፣ አድራጊ ፈጣሪ ከመሆን፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከመቆጣጠር፣ የግለሰቦችን መብት ከማፈንና ከመሳሰሉት አሉታዊ ድርጊቶች አንፃር ከተቃኘ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ከአገር ዘለቄታ ህልውናና ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ሲመጋገብ ለምንነጋገርበት ርዕሰ ጉዳይ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ የበለፀጉ ወይም በወታደራዊ ጡንቻቸው የሚተማመኑ አገሮች ለጂኦ ፖለቲካዊ ዓላማዎቻቸው መሳካት ሲሉ በየትም ሥፍራ የኢነርጂ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ነዳጅ የሚገኙባቸውን ቦታዎች፣ ለኑክሌር ማብላያ የሚጠቅመውን ዩራኒየም፣ ማዕድናትን፣ ውድ ጌጣ ጌጦችና ዕንቁዎችን ለመቆጣጠር በርካታ ታዳጊ አገሮችን ወረዋል፡፡ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አማካይነት አስገዳጅ በሆኑ ስምምነቶችም ተፅዕኖአቸውን በየቦታው አሳርፈዋል፡፡ በብሔራዊ ጥቅም ስም አገሮች እየተወረሩ ሕዝቦቻቸው ለስቃይ ተዳርገዋል፡፡  ኢትዮጵያዊያንና አገራቸው ግን ይህንን እኩይ ተግባር ሲፋለሙ ስለኖሩ፣  

  በዚህ ግንዛቤ መሠረት ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን ስንቃኝ እነዚህን እኩይ ተግባራት እየራቅን መሆን አለበት፡፡

  ከብሔራዊ ደኅንነት ስንጀምር አገርን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች በመጀመር ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ማንም ዜጋ በገዛ አገሩ ላይ የሚፈጸሙ ደባዎችንና አደገኛ ድርጊቶችን ከማጋለጥ ጀምሮ፣ የመከላከልና ብሎም የመቀልበስ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የዜግነት ክብሩና ማዕረጉም ይኼው ነው፡፡ አገርን ለጥቃት የሚያጋልጡ ድርጊቶች ደግሞ ከአውዳሚ ግጭቶች ጀምሮ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶችን ዝርፊያ ያካትታሉ፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመለካከትና በመሳሰሉት በሕዝብ መካከል መጠራጠር መፍጠርና ለግጭት መዳረግ አደገኛ ተግባር ነው፡፡ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣን ማንኛውም ወረራ ሆነ አሻጥር ማበረታታትም ሆነ መፈጸም የክህደት ተግባር ነው፡፡ የአገርን ሚስጥር ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የከፋ ተግባር ነው፡፡ በየብስ፣ በምድርና በባህር የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚቃረኑ ማናቸውንም ተግባራት ብቻ ሳይሆን፣ በኤሌክትሮኒክ ግንኙነቶች ጭምር የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መተባበር ወይም እንዳላዩ መሆን አውዳሚ ተግባር ነው፡፡ እነዚህና መሰል ተግባራት በሕግ ያስጠይቃሉ፡፡ ቅጣታቸውም የከበደ ነው፡፡ አገሩን የሚወድ ዜጋ ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹን አስከፊ ድርጊቶች የመከላከል ትልቅ አገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ ብሔራዊ የመለያ ምልክትም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እያንኳሰሱ ጠባብነትን ማስተጋባት በራሱ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ 

  በሌላ በኩል በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ አገርን ከሚጎዱ ድርጊቶች ይታቀባል፡፡ የመጀመሪያው የሕግ የበላይነትን ማክበር ነው፡፡ ሕግ የሚያከብር ማንኛውም ዜጋ በተሰማራባቸው መስኮች ግዴታውን በሚገባ እየተወጣ መብቱን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ የሕዝቡን ማኅበራዊ እሴቶች ማክበር፣ የአገር ሀብትን አለማባከን፣ ሕዝብን ለችግር ከሚዳርጉ ድርጊቶች መቆጠብ፣ ሌብነትና ዘረፋ ውስጥ አለመገኘት፣ ሥልጣንን በሕጉ መሠረት ብቻ መጠቀም፣ ለወጣቱ ትውልድ አርዓያ መሆን፣ አጓጉል ድርጊቶችን መፀየፍ ብቻ ሳይሆን እንዲመክኑ ማድረግ፣ በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ የመንግሥት ሹማምንትን ማጋለጥ፣ አገር እየዘረፉ በአቋራጭ ለመክበር የሚሯሯጡትን ማስታገስና የመሳሰሉትን አኩሪ ተግባራት መፈጸም ጠቃሚ ነው፡፡ ብሔራዊ ደኅንነት የሚጠበቀው ከውጭ የሚቃጣ ጥቃትን በመከላከል ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ ብልሹ አሠራሮችንና ሕገወጥነቶችን ዋጋ ማሳጣት ሲቻል ጭምር ነው፡፡ በሕዝብ መካከል ኢፍትሐዊነትን የሚያነግሡና የሚያስቆጡትን አደብ ማስገዛት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

  የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ሲነሳ አገሪቱ ከጎረቤት አገሮች ጀምራ የተለያዩ አኅጉሮችን ስታቆራርጥ ዲፕሎማሲዋ በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተቃኘ መሆን አለበት፡፡ መንግሥታት በሚያደርጉዋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በርካታ ውጣ ውረዶች መኖራቸው ዕውን ቢሆንም፣ ማንም መንግሥት በአገሩ ሕዝብ ተጠያቂነት ስላለበት በተቻለ መጠን ብሔራዊ ጥቅም መጎዳት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዓለም በአፍሪካ ስመ ገናና ናት፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ በፊት ጀምሮ በዓለም ላይ ከብዙ አገሮች ጋር ግንኙነት የመሠረተች ታሪካዊ አገር ናት፡፡ በሰላም ማስከበርም ሆነ በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷም ትታወቃለች፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መመራት ያለበት በበሰሉ ዲፕሎማቶች ድጋፍ መሆን ይኖርበታል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ዲፕሎማቶችን ያፈራች አገር፣ እነዚህን ልምድ ያካበቱ ዜጎች መጠቀም ግድ ይላታል፡፡ ከአማካሪነት ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያግዛሉና፡፡ ይህ ሲሆን ዲፕሎማሲው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን ያጎለብታል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ይረዳል፡፡ በአገሪቱ ጥሪት ተምረው በርካታ ግዳጆችን የተወጡ ልምድ ያላቸው ዜጎችን ማንገዋለል ኪሳራ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ወጣት ዲፕሎማቶችን ኮትኩቶ ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ መነቃቃት ስሟ ሲነሳ ያኮራል፡፡ ይህንን ኩራት ግን ጎዶሎ የሚያደርጉ በርካታ እንቅፋቶች አሉ፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር መጣበብ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የዜጎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች መብዛት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ እንደ ሰደድ እሳት የተዛመተው ሙስና ማቆሚያ ማጣት፣ ወዘተ የዚህች ኩሩ አገር ሕዝብ እሮሮ ናቸው፡፡ አገሪቱ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ሆና አደባባይ ላይ ስትታይ የምታጣቸው በርካታ ጥቅሞች አሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን የምታስተናግድ አገር በርካታ ታዋቂ የሚዲያ ድርጅቶች ለምን ይሸሹዋታል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የአገር ገጽታን አስተካክሎ ራስን ለገበያ ማቅረብ ሲገባ መሸፋፈንን ምን አመጣው? ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስህቦቿ በአፍሪካ ተደናቂ ሆና ሳለ ለምን ጎብኚዎችን መሳብ አቃታት መባል የበለትም? ወይስ በዘልማዳዊ አሠራር ተተብትቦ ተዓምር መጠበቅ ይሻላል? ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን የሚያሳጡ አጉል ድርጊቶችን ማስወገድ? ወይስ በይነጋል ይመሻል ድብርት ውስጥ መመሸግ? የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በጣም ብዙ ነገሮች አሉበት፡፡ በመጥበብና በማነስ የሚገላገሉትም አይደለም፡፡

  ይህች አገር ከተሠራባት የተዓምር ምድር መሆን ትችላለች፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ያለባት፣ አብዛኛው ደግሞ ወጣት፣ በዓመት ከ100 ሺሕ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ወጣቶች ለሥራ የሚዘጋጁባትና በጨዋነቱና በጀግንነቱ ዓለምን ያስደመመ ሕዝብ ምድር ናት፡፡ ይህንን አይበገሬ ሕዝብ አንቀሳቅሶ ድህነትን ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የተጣባንን የፖለቲካ ነውር ማስወገድ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ መሠረቶችን መጣል፣ ዘረኛና ከፋፋይ ድርጊቶችን ማስወገድ፣ ጠንካራውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በማፅናት በኅብረት መቆም፣ ወጣቱን በትምህርትና በሥነ ምግባር ማጎልበት፣ ከስሜታዊነትና ከጀብደኝነት የፀዳ አስተዋይ ትውልድ ማነፅ፣ አሉባልታንና ሐሰተኛ ወሬዎችን በተግባር ሥፍራ ማሳጣት፣ ሌብነትና ዘረፋን ከመፀየፍ በላይ በተግባር ማንኮታኮት፣ የሕዝባችንን አኩሪ የጋራ እሴቶች መርህ ማድረግና የመሳሰሉት ያስፈልጋሉ፡፡ ለእነዚህ ስኬት ደግሞ ዋነኛ ማሰሪያው የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ሕግ ያክብር፣ ያስከብር፣ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ በተግባር እንዲረጋገጥ ይትጋ፡፡ ያኔ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ይሆናል፡፡ በሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አገር ያስተዳድራል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ፋይዳ ቢስ ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ሰላም የሚሰፍነውና እኩልነት የሚረጋገጠው ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ሁሉም ወገን በእኩልነት ሲተጋ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ያፈነገጡ ድርጊቶች ግን ከመወገዝም በላይ መወገድ አለባቸው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...