Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብድርና የዕርዳታ ፍሰት ላይ የመቀነስ አዝማሚያ እየታየ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአደጉ አገሮች የሚገኘው የፋይናንስ ድጋፍ (ኦፊሻል ዴቨሎፕመንት አሲስታንስ) እየቀነሰ መምጣቱ ተመለከተ፡፡ ያደጉ አገሮች በራሳቸው ችግር ምክንያት ሲያደርጉ የቆዩትን የፋይናንስ ድጋፍ እያቋረጡ መሆኑን ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ገልጿል፡፡ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ይኼንን ችግር በዘላቂነት ለመቋቋም ትኩረቱን ኤክስፖርትና ኢንቨስትመንት ላይ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የሚካሄዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ 2.2998 ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1.3133 ትሪሊዮን ብር የሚሆነው ለካፒታል ወጪዎች የሚያስፈልግ ነው፡፡

የፋይናንስ ምንጮቹ የተለያዩ ቢሆኑም፣ በተለይ ከአደጉ አገሮች የሚገኘው ብድርና ዕርዳታ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡

አቶ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ያደጉ አገሮች የሚያደርጉት የፋይናንስ ድጋፍ በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህ ክስተት ቀደም ሲል የታሰበበት ቢሆንም ከአጠቃላይ ወጪ አንፃር ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

‹‹ኦፊሻል ዴቨሎፕመንት አሲስታንስ (ODA) እየቀነሰ የመምጣት አዝማሚያ ቢኖረውም፣ ከውጭ አገር የሚፈሰው የውጭ ምንዛሪና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየጨመረ በመምጣቱ ልዩነቱ ተካክሷል፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚቻለው የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) በዕቅዱ መሠረት እየሄደ አይደለም፡፡ የውጭ ዕርዳታና ብድር እየቀነሰ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ፣ የወጪ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እንደሆነም አስምረውበታል፡፡

ነገር ግን የወጪ ንግድ ከሚያዝለት ዕቅድ ብዙ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በ2008 ዓ.ም. በአጠቃላይ 4.22 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማግኘት የተቻለው 1.423 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

የኤክስፖርት ዘርፍ ለማስተካከል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተገኘውን ገቢ ደግሞ ምርታማነት ባላቸው ዘርፎች ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጥሩ ፍሰት ያለው ቢሆንም፣ ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ ኢንቨስተሮችን መመልመል ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ኤክስፖርት ማድረግ የማይቻሉባቸው ምክንያቶች ቢኖሩም እንኳ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ ጌታቸው ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲጠናቀቅ (2012 ዓ.ም.)፣ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች