Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኦፌኮና ጌሕዴድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን እንደማይቀበሉ አስታወቁ

ኦፌኮና ጌሕዴድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን እንደማይቀበሉ አስታወቁ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ) እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ማክሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ‹‹የተወካዮች ምክር ቤት እንደተለመደው በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረበውን ሐሳብ በመደገፍና በማፅደቅ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው ውሳኔ አሳዝኖኛል፤›› ብሏል፡፡

ኦፌኮ፣ ‹‹የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስን ህልውና በመፈታተን ሕዝቡን ከዓላማው ማስቆም አይቻልም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ተጠያቂ ይሆናሉ የተባሉት የመንግሥት ተቋማትና መሪዎቻቸው በስም ተለይተው ባልቀረቡበት ሪፖርት የመንግሥት ተቋማትና መሪዎቻቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም፤›› ብሏል፡፡ የኢትጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ራሱ የመንግሥት አንዱ አካል ስለሆነ በሪፖርቱ ገለልተኛነት ላይ እምነት እንደሌለው ኦፌኮ በመግለጫው ገልጿል፡፡

‹‹ገለልተኛ ነኝ የሚለው ኮሚሽን ኦፌኮን በሕግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ሲያመቻች፣ ኦፌኮ ራሱን እንዲከላከልም ሆነ ንፅህናውን እንዲያስረዳ ጥያቄም ሆነ ሁኔታውን የመግለጽ ዕድል አልሰጠውም፤›› ብሏል፡፡ የአንድ አካል ገለልተኝነት ዝቅተኛ መለኪያ በሆነው በጠያቂነትም ሆነ በተጠያቂነት የሚገኙ አካላትን ማነጋገር ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርቱን የሠራው በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንነቱ ሳይሆን በኢሕአዴግ ባለሥልጣንነቱ እንደሆነ ያሳብቅበታል በማለት ኦፌኮ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን ኮንኗል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንደሚለው ሳይሆን ኦፌኮ ሕዝባዊ መነሳሳቱን አላባብስም ብሏል፡፡ ያንን የሕዝብ ማዕበል በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለማንቀሳቀስም አቅም እንደሌለውም ኦፌኮ አስታውቋል፡፡ ‹‹ኢፌኮ ያደረገውና ወደፊትም ህልውናው ተጠብቆ የሚቆይ ከሆነ የሚያደርገው ነገር ቢኖር፣ ማንም አካል ከሕገ መንግሥታዊ አግባብ ውጪ ሥልጣን መያዝም ሆነ ሥልጣን ላይ መቆየትን ፈጽሞ የማይፈቅድና ሕገ መንግሥታዊ አግባብን ረግጦ የሚመጣ አካል ካለም ሕዝባችን ለመሸከም የማይሻ መሆኑን አስምረን እየገለጽን፣ በጀመርነው ሰላማዊ የትግል ጉዞ የምንቀጥል መሆኑን  እናስታውቃለን፤›› ብሏል፡፡ ኦፌኮ አያይዞም ይህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሳይሳካ ቢቀርና ሕዝባዊ አመፁ ወደ አፈሙዝ የሚዞር ከሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ያልተቀበለው ኢሕአዴግ ተጠያቂ እንደሚሆን በመግለጫው አክሏል፡፡

ኢሕአዴግ ዛሬም የመብት ጥሰቶችን ማስቆም፣ ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለሕግ ማቅረብ፣ ካድሬዎችን አደብ እንዲገዙ ማድረግ፣ የፍትሕ አካላት ከሥራ አስፈጻሚው ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ሲገባው ችግሮችን በተቃዋሚ ፓርቲዎች (ኦፌኮ፣ ሰማያዊና ጌሕዴድ) ላይ ማላከክ እንደመረጠ ኦፌኮ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ኦፌኮ በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የውሳኔ ሐሳብና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ አንፃር ህልውናው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ የኦፌኮ ህልውናን በመፈታተን ሕዝቡን ከዓላማው ማስቆም እንደማይቻል አስገንዝቧል፡፡

በተመሳሳይ ዜናም የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ)፣ በደቡብ ክልል በጌድኦ ዞን የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ ጌሕዴድ እንደቀሰቀሰውና እንዳባባሰው ተደርጎ መወንጀሉ የተሳሳተ እንደሆነ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ዛሬም ለውስብስቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊመጥን በሚችል አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት በተግባር እንዲረጋገጥ ጌሕዴድ በመታገል ላይ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከጌዴኦ ውጪ ያሉ ብሔሮች ዞኑን ለቀው እንዲወጡ ጌሕዴድ እንደተንቀሳቀሰ አድርጎ የተገለጸውን እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡ የጌዴኦ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ለዘመናት የተጋባና የተዋለደ፣ ከዞኑም ውጪ በሌሎች ክልሎች በኢትዮጵያዊነቱ ሠርቶ ከኢትጵያውያን ወገኖቹ ጋር በሰላም የሚኖር እንደሆነም በመግለጫው አስረድቷል፡፡

‹‹ለሁከቱ መሠረታዊ መንስዔ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት፣ የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር መሆናቸውን ኮሚሽኑ ቢያምንምና የእነዚህ ችግሮች ዋና ፈጣሪ ገዥው ፓርቲ መሆኑ እየታወቀ እያለ፣ ተጠያቂነቱን በጌሕዴድና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ መለጠፉ ለሪፖርቱ ኢተዓማኒነትና ለፖለቲካዊ ወገናዊነት አንዱ ማረጋገጫ ነው፤›› ብሏል፡፡ ጌሕዴድ መሰል ሁከቶች በዘላቂነት ሊወገዱ የሚችሉት ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ ሕዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ ለሥልጣን የሚያበቃበትና የማይፈለገውን ደግሞ ከሥልጣን የሚያነሳበት የፖለቲካ ሥርዓት በተግባር ሲረጋገጥ  ብቻ መሆኑን ጠቁሞ ዜጎች በቋንቋ ሳይከፋፈሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎችም በየፓርቲያቸው ፍላጎት ሳይሸበቡ ለተቀናጀና ለተጠናከረ ትግል በጋራ እንዲሠለፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት አዘል ተቃውሞን በተመለከተ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ማለፉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...