Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት እየተሠራ ነው

የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት እየተሠራ ነው

ቀን:

በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለይቶ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የምሥራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ጉባዔ ከነሐሴ 24 እስከ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ተካ ገብረ ኪዳን፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለይቶ የማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቅርቡ በአዳማ ከተማ ዓመታዊ ግምገማ አካሂዷል፡፡ አቶ ተካ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አገሪቱ እየተከተለችው ካለው የለውጥ ሒደት ጋር ተያይዞ የሕግ የበላይነት ለማስክበር፣ ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅና በአጠቃላይ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን በፍትሕ ሥርዓቱ ያሉ ጉድለቶችን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የኅብረተሰቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት፣ ኅብረተሰቡ በፍትሕ ተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖረው መንግሥት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ቁጠኝነት ማሳየቱን ገልጸው፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አመራሩንና ፈጻሚውን በማንቀሳቀስ የተሻለ ሥራ ለመሥራት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

መሥሪያ ቤቱ ብቻውን ከመሥራት ይልቅ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ያሉበትን ክፍተቶች በመጠቆም የመፍትሔ ሐሳብ የሚሰጡት የሕግ ባለሙያዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአባልነት የሚገኙበት አማካሪ ጉባዔ ማቋቋሙን አቶ ተካ አስታውሰው፣ አማካሪ ጉባዔው በቅርቡ የሚሻሻሉ ሕጎች ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በኢንቨስትመንት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት በሚዳኙበት ወቅት፣ እነዚህን ጉዳዮች ሊከታተሉ የሚችሉ በቂ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ በጉባዔው ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ላይ በመሆኗና ታላላቅ የመሠረተ ልማት ግንባዎች በማካሄድ ላይ የምትገኝ አገር ስለሆነች፣ አልፎ አልፎ በውጭ ኩባንያዎችና በመንግሥት መካከል ከኮንትራት ውሎች ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በመንግሥትና በውጭ ኩባንያዎች መካከል አለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ይወሰዳል፡፡ በዚህ ወቅት እነዚህን ጉዳዮች መያዝ የሚችሉ የሕግ ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ፣ መንግሥት የውጭ ጠበቆች ለመቅጠር ይገደዳል፡፡ ይህም በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል፡፡

‹‹በዚህ መስክ የተጠናከረ ተቋምና የተካኑ ባለሙያዎች የሉንም፡፡ ጥቂት ኢትየጵያውያን ባለሙያዎች ቢኖሩም በውጭ የሚኖሩ ስለሆኑ፣ አገር ውስጥ ያሉትም ጥቂት በመሆናቸው በዚህ ረገድ አቅማችንን መገንባት እንዳለብን ተገንዝበን፣ በፍትሐ ብሔር ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች ይዘን አገራዊ አቅም ለመፍጠር እየሠራን ነው፤›› ያሉት አቶ ተካ፣ ባለሙያዎችን እንዴት መሳብና ከግል ጥብቅና ቢሮዎች ጋር እንዴት ተባብሮ መሥራት እንደሚቻል ጥናት እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዚህ ዘርፍ የተሻለ ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያውያን እያማከሩን ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክረ ሐሳብ በግብዓትነት ይዘን አለመግባባቶችን መፍቻና  ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ሒደቶች የምንከታተልበት የተሻለ ሥርዓት እንዘረጋለን፡፡ አሁን ገና በጅምር የሚገኝ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት በመስፋፋቱ በዚህ ላይ ብዙ ሥራ ማከናወን ይጠበቅብናል፤›› ያሉት አቶ ተካ ጉባዔው ወቅታዊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጉባዔው አዘጋጅ የኢንተንርናሽናል አርቢትሬሽን አፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሪት ልዩ ታምሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ በመሆናቸው፣ በኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ሥርዓትና ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤቶች የሚሄዱ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ማሠልጠንና ተቋማዊ አቅም መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በርካታ የአፍሪካ አገሮች በየጊዜው የሚያጋጥማቸው ፈተና መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሪት ልዩ፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር አለመግባባት ሲፈጠር የውጭ የጥብቅና ቢሮዎች እንደሚቀጠሩ ይህም ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአገር ውስጥ የጥብቅና ቢሮዎች በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤቶች ልምድ ስለሌላቸው፣ መንግሥት የውጭ የጥብቅና ቢሮዎች ይቀጥራል፡፡ ይህ ጉዳይ እየቀጠለ ከሄደ የአገር ውስጥ የጥብቅና ቢሮዎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ልምድ የሚያገኙት መቼ ነው?›› ያሉት ወ/ሪት ልዩ፣ ቢያንስ የውጭ ጠበቆች ሲቀጠሩ ከአገር ውስጥ የጥብቅና ቢሮዎች ጋር በጥምረት እንዲሠሩ የሚያስገድድ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በማዕድን ልማትና በኃይል ማመንጨት ዘርፍ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተሰማሩ ስለሆነ፣ አለመግባባቶችን የመፍታትና የግልግል ሥራዎች ለመሥራት አገራዊ አቅም መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳንና ጂቡቲ ከማዕድንና ኢነርጂ ጋር የተያያዙ ከኩባንያዎች ጋር አለመግባባቶች ተፈጥረው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የካሳ ጥያቄዎች የቀረቡባቸው ክሶች በግልግል ፍርድ ቤቶች ክስ መመሥረቱ ተገልጿል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ጉባዔ ላይ ከ250 በላይ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...