Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ይከበሩ!

  ኢትዮጵያዊነት በጀግኖች ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ የኅብረ ብሔራዊነት መገለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በጥቅብ ያቆራኙት የጋራ እሴቶቹ የሚደምቁት በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የጋራ እሴቶቹ በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ገመድ የተያያዙ በመሆናቸው፣ ሕዝቡ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ ቢኖርም ሥነ ልቦናው ግን በጣም ተቀራራቢ ነው፡፡ የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነትና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ አንድ ላይ መኖር የቻለውም፣ የጋራ እሴቶቹ ቁርኝት ጠንካራ ስለሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተፈጥሮ የታደለው አስተዋይነትና አመዛዛኝነት የአገር ፍቅር ስሜትን ጥልቅ በማድረግ፣ ኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም የሚኮሩበትን በቅኝ ያለመገዛት አንፀባራቂ ታሪክ አጎናፅፏል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ጦርነት ድል አስገኝቷል፡፡ በዚህ ድል ምክንያትም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ጋሻ በመሆን፣ የጋራ መሰባሰቢያ ቤታቸው እንድትሆን አስችሏል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቶት አዲስ አበባ እንደ ኒውዮርክና ጄኔቭ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ለመሆን ችላለች፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች የበለጠ እየተከበሩ ሲሄዱ ደግሞ፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሻምፒዮን መሆን ይቻላል፡፡

  ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ግን በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ሕወጥነትንና ሥርዓተ አልበኝነትን አደብ ማስገዛት አለባት፡፡ ለሕግ የበላይነት ተገቢውን ክብር በመስጠት ከአፋኝነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ ማቀላጠፍ ይገባል፡፡ አንዱ የሌላውን እያከበረና እያስተናገደ ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ሰላምና ዴሞክራሲ በጋራ መቆም ያስፈልጋል፡፡ የጋራ እሴቶቻቸውን አክብረው የኖሩት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ እየጠበቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳስተላለፉት ሁሉ፣ የአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያንም አገራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችላትን ሰላም አጥብቀው መፈለግ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ታላቁ ምሥል የሚገለጸው በጋራ እሴቶች ስለሆነ፣ ቃልና ተግባር ሰምና ወርቅ እንዲሆኑ ቀና መሆን ተገቢ ነው፡፡ ከጎራ ፖለቲካና ከሴራ ድርጊቶች በመላቀቅ ለአንዲት እናት አገር ክብርና ሰላም ከልብ መጨነቅ የግድ ይላል፡፡

  የብዙኃን አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እርስ በርሱ ሲከባበርና ዕውቅና ሲሰጣጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ የጋራ አገር መሆኗን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በማንነትም ሆነ በተለያዩ ልዩነቶች ምክንያት አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ ማለት የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ፍትሐዊ የሆነ እኩልነት መስፈን ይኖርበታል፡፡ ከአሁን በኋላ ማንም በማንም ላይ የበላይ መሆን እንደማይችል፣ ማንም ለማንም እንደማያጎነብስ፣ የጌታና የሎሌ ዓይነት ግንኙነት እንደማይኖር፣ የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅሮችና የፀጥታ አካላት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያገለግሉ እንጂ አድልኦ የሚፈጽሙ መሆን እንደሌለባቸው፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነት ተረጋግጦ ፍትሕ መስፈን እንዳለበት፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና በፍፁም መደበላለቅ እንደሌለበት፣ ወዘተ. በሚገባ መስረፅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሹማምንት በፍፁም እንደማያስፈልጉ ሁሉ፣ ብቃት የሌላቸውም በምንም ዓይነት ሁኔታ መሾም የለባቸውም፡፡ ከሞላ ጎደል በዚህ ደረጃ መጓዝ ከተቻለ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ገነት ትሆናለች፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ግን የጋራ እሴቶች ይከበሩ፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ጥልቅ እያሉ የሚታዩ ነውረኛ ድርጊቶች በጊዜ መላ ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የአስተዳደር መዋቅሮች ሥራቸውን ማከናወን አቅቷቸው፣ በጉልበት የተደራጁ ቡድኖች ያሻቸውን እያደረጉ ነው፡፡ በሕግ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እጅና እግራቸው ተይዞ፣ ሕገወጦች በሕዝብ ላይ እየፈነጩ ነው፡፡ ፀጥታ የማስከበር ሕጋዊ ኃላፊነት ያለባቸው አካላትም እንዳላዩ እየሆኑ ሥርዓተ አልበኝነት እየሰፈነ ነው፡፡ ሕጋዊ አካላት ለሕገወጦች ሲንበረከኩ ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ በግልጽ በአደባባይ ሰብዓዊ ፍጡርን በደቦ ፍርድ መግደል ከተለመደ፣ የተደራጁ ሕገወጦች አገርን ያተራምሳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገመደባቸው የጋራ እሴቶች ይናዳሉ፡፡ ኢትዮጵያም በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ቀውስ ውስጥ ትገባለች፡፡ ነውረኛ ድርጊቶች በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ እነዚህ አሳፋሪ ድርጊቶች የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች በመናድ አገር ያፈርሳሉ፡፡

  አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ታስቦ ሥራ ላይ የዋለው የፌዴራል ሥርዓት፣ እውክታ እንደገጠመው በግልጽ ታይቷል፡፡ ተወደደም ተጠላም ለኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ እንደማይቻል ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በምን ዓይነት ቅርፅና ይዘት ይደራጅ ለሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወስንበት ዕድል እንደሚኖር ይታመናል፡፡ በሕዝብ ተሳትፎ በሚገኘው ውጤት መሠረትም፣ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ይታሰባል፡፡ ዞሮ ዞሮ የተለያዩ ፍላጎቶችን አማካይ ሆኖ የሚያስተናግደው የፌዴራል ሥርዓት መኖሩ የግድ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅሙንና ደኅንነቱን የሚያስከብርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲችል ግን የሕግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር እንኳን የደቦ ፍርድ ሊፈጸም፣ በሕግ ጥፋቱ ያልተረጋገጠበት ዜጋ እንደ ንፁህ ይቆጠራል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የጋራ ዕድሉ መመሥረት ያለበት፣ ከታሪክ የተወረሱ የተዛቡ ግንኙነቶችን በማስተካከልና የጋራ ጥቅሙን በእኩልነት በማስከበር ነው፡፡ የዚያኑ ያህል የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችም ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ በሐሰተኛ ታሪክ ተብዬዎች ሕዝብን የሚከፋፍሉና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን የሚንዱ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶችን በማክበር መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ ይጠቅማል፡፡

  ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲኖር ከተፈለገ ከዘረኝነትና ከራስ ወዳድነት መፅዳት ያስፈልጋል፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አኗኗር አይመችም፡፡ ራስ ወዳድነት የሥነ ምግባር ብልሽትና የሌብነት መገለጫ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ የጋራ ጥቅሙና መብቱ በሕግ የበላይነት ሥር ሲከበርለት፣ ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ አሉ የሚባሉ ልዩነቶች ከኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጋር ሲነፃፀሩ ኢምንት ናቸው፡፡ ትስስሩና ሥነ ልቦናዊ መቀራረቡ ሚዛን ይደፋል፡፡ በተዛቡ አመለካከቶች ሳቢያ የሚፈጠሩ ቅሬታዎች ወደ ቅራኔ እያደጉ፣ ለፀፀት የሚዳርጉ እኩይ ድርጊቶችን ከማስፈጸም የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የመሰለ የቅድስና ሥፍራ ውስጥ ነውረኛ የሆነ ግድያ የሚያስፈጽሙ እኩይ ስብከቶችና ቅስቀሳዎች፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን መላ አገርን የሚያሳፍሩትና ለፀፀት የሚዳርጉት ጠንካራውን ኢትዮጵያዊነት ስለሚያዋርዱ ነው፡፡ የአገሩን ህልውና ከራሱ ህልውና በላይ የሚያስብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የገዛ ወገኑን ደም በከንቱ አያፈስም፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች የሚያስተምሩትም ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ይከበሩ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

  ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...