መንግሥትና የግሉ ዘርፍ 30 ፓርኮች እንደሚገነቡ ይጠበቃል
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶች በጂማ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው ለመያዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ መንግሥትም ደስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር)፣ በኢንቨስትመንት አፈጻጸምና በአዲሱ ዓመት በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ እየተገነቡ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሙሉ በሙሉ በሊዝ ጠቅልሎ ለመረከብ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ የኤምሬትስ ባለሀብቶችም በጂማ እየተገነባ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ለብቻቸው ለመግዛት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሦስት ሳምንታት በፊት፣ ከኤምሬትስ ባለሀብቶች ጋር በመሆን የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ የግንባታ ሥራው 70 በመቶ የተከናወነውና 61 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀው የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ዘጠኝ የማምረቻ ሼዶችን ያካተተና በ75 ሔክታር ላይ የሚንጣለል ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም ለተለያዩ የውጭ ባለሀብቶች ሲደረግ ከነበረው የሊዝ አቅርቦት በተለየ መንገድ፣ ፓርኩን ሙሉ በሙሉ ለመረከብ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መንግሥትም ይሁንታውን ከመገለጹም በላይ፣ በግላቸው መግዛት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ዕድሉ እንደሚመቻችላቸውም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
ከጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሻገር በአዳማ እየተገነቡ ከሚገኙት ሁለት ፓርኮች ውስጥ አንደኛው በአንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት፣ ከበግና ከሌሎች እንስሳት የሚገኘውን ፀጉር ተጠቅሞ ናይለን የሚያመርተው ኪንግደም በተሰኘው የቻይና ኩባንያ ጨምሮ፣ የህንዱ አንቴክስ ኩባንያም አራት የማምረቻ ሼዶች ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርክ በአዳማ እየገነባ እንደሚገኝ ከኮሚሽሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከሞጆ ከተማ 57 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አነስተኛዋ አረርቲ ከተማም የሕንፃ መሣሪያዎችና የቤትና የቢሮ ዕቃዎች የሚመረቱበት ኢንዱስትሪ ፓርክም በቻይናውያን እየለማ የሚገኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በጠቅላላው 30 ያህል የኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ 2017 ዓ.ም. እንዲለሙ መታቀዱን የገለጹት ኮሚሽነር በላቸው (ዶ/ር)፣ የፓርኮቹ መገንባት የአምራች ኢንዱስትሪውን ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ለማሳደግና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋፋት ፋይዳው ትልቅ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በየዓመቱ 200 ሺሕ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር በተጨማሪ፣ የአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ አሁን ካለው የአራት በመቶ ወደ 25 በመቶ እንዲያድግ፣ ከወጪ ንግድ አኳያም አሁን ካለው የስምንት በመቶ ድርሻ ወደ 20 በመቶ እንዲያድግ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌና በኮምቦልቻ የተገነቡት እንዳሉ ሆነው የ11 ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሌሊሴ ነሜ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአራት ወራት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ሊመረቅ እንደሚችልም አስታውቀው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ በቂሊንጦ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም ለመድኃኒት ማምረቻነት ተመርጦ ስምንት የውጭ ኩባንያዎች ቦታ ተረክበው በራሳቸው የዲዛይን ምርጫ ግንባታ እያካሄዱ እንደሚገኙ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
መንግሥት ከዓለም ባንክ ለቦሌ ለሚ ሁለት ግንባታ ካገኘው ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ባሻገር፣ በዩሮ ቦንድ ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማዋሉም ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት በቦሌ ለሚና በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ማምረት የጀመሩ ኩባንያዎች ባለፈው ዓመት የ100 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ማስመዝገባቸውንና ከ55 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ኮሚሽነር በላቸው (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ እንደሚያስገኝ፣ በሁለት ፈረቃም ለ60 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ ሲገለጽ ነበር፡፡ ኮሚሽነር በላቸው (ዶ/ር) አንድ ቢሊዮን ዶላር ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኛል የሚለውን አጣጥለው፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ግን ከወዲሁ በአንድ ፈረቃ 20 ሺሕ የሥራ ዕድል ማስገኘቱንና ይህም ከሚጠበቀው ጊዜ ቀድሞ ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያስቸለው አመላካች ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ250 ሚሊዮን ዶላር በ300 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ማምረቻዎችን የገዙ 21 የውጭ ኩባንያዎች የሚገኙበትና 1.3 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ የሚያካልል ሞዴል የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡