Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአትሌቲክሱ ፈተናዎች

የአትሌቲክሱ ፈተናዎች

ቀን:

‹‹የደጋው በራሪዎች›› የውጤት ምስጥር ስለመሆኑ ለዓመታት ሲነገርለት የቆየው የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የአየር ሁኔታ አሁን ላይ በብዙ መልኩ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያየለ ስለመምጣቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ በርካቶች ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

የችግሩ ገፈት ቀማሽ አትሌቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ቢረዱትም ከአዲስ አበባ ርቆ የመሄድ ፍላጎታቸው ግን እምብዛም እንደሆነ፣ ትጥቅ አምራች ከሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በመጓዝ ዝግጅት ማድረግን የሚመርጡ አቅም ያላቸው አትሌቶች ስለመኖራቸው እየተነገረ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የአየር ብክለት በመካከለኛ ደረጃ በሚፈረጅ የብክለት መጠን ላይ እንደሚገኝ የአሜሪካ አጥኝዎች ከጥቂጥ ወራት በፊት ለሪፖርተር ጋዜጣ ማብራራታቸው ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ የሚነጨው ብክለት ከመኪና ጭስ፣ ከማገዶና ከመሳሰሉት የኃይል ምንጮች የሚወጣ ሲሆን፣ በተለይ በከተማዋ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የሚያመነጩት በካይና የተቃጠለ ጭስ፣ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ለውስብስብ የጤና እክሎች እንደሚያጋልጥ በዘርፉ ሙያተኞች ተረጋግጧል፡፡

የጉዳቱ መጠን በተለይ ሕፃናትን ለከፋ ጉዳት የሚዳርግና ለሞት የሚያደርስ ስለመሆኑ አጥኝዎቹ ማብራራታቸውም ተዘግቧል፡፡ የከተማዋን የአየር ብክለት መጠን በዕለቱ የሚለኩ መሣሪያዎች በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በኢንተርናሽናል ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ሁኔታ  መረጃ መቀበያ ጣቢያዎችና በሌሎችም ተቋማት ውስጥ መተከላቸው ይታወቃል፡፡   

ይህም በመሆኑ አቅሙ የሌላቸውና የፌዴሬሽኑን ዕገዛ የሚሹ አትሌቶች፣ ተቋሙ የሚያወጣቸውን መመርያዎችና ደንቦች ተከትለው ማናቸውንም ዝግጅቶች ለማከናወን ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ውክልናን የሚመለከቱ ምርጫዎች ሲኖሩ በመሥፈርትነት የሚቀመጡ ደንቦችና መመርያዎች በትክክል ስለማይተረጎሙ ከፌዴሬሽኑ ይልቅ ከሥልጠናና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የቅርብ ሰዎቻቸውን ምክርና ድጋፍ ላይ እንደሚመረኮዙ፣ ይህም በአገሪቱ የአትሌቲክስ ውጤት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱ ይነገራል፡፡

በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዲፓርትመንቱን በበላይነት የሚመሩት አቶ ዱቤ ጅሎ፣ ‹‹ተቋሙ እነዚህንና ሌሎች ተግዳሮቶችን መፍታት ይቻለው ዘንድ በ2010 የውድድር ዓመት መጀመርያዎቹ ወራቶች ውስጥ ከፍተኛ ሙያተኞችን ወደ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ልኮ የመስክ ምልከታን ያካተተ ዳሰሳ ጥናት አድርጓል፤›› በማለት ጥናቱ ያስገኛቸውን ውጤቶች አብራርተዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት ላይ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች የሳተፉበት ውይይት ስለመደረጉም አቶ ዱቤ ገልጸዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም የጥናቱ መነሻ ሐሳብ እንደገና ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች እንዲላክ ተደርጓል፡፡ ‹‹እነዚህ ውይይቶችና ስምምነቶች ሲደረጉ በዋናነት የአትሌቲክሱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሥልጠናና ዝግጅት እንዲሁም የሁሉም መዳረሻ የሆነችው አዲስ አበባ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ለአትሌቶች ሁለንተናዊ ዝግጅት ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ መፍትሔ ለመሻት ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡

መመርያዎችና ደንቦችን በተመለከተ፣ ‹‹እስካሁን ባለው ሁኔታ ከአትሌትም ሆነ ከአሠልጣኝ በኩል ከደንብና መመርያ ውጪ በደል ደርሶብናል የሚል አካል አልገጠመንም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዋናነት ተጠሪነቱ ለአትሌቶች እንደመሆኑ፣ ደንቦች፣ መመርያዎችና ሌሎችም ሕጎች ሲወጡ እነዚህ አካላት ሳይመክሩበት ሕጋዊ ሆኖ አያውቅም፤›› የሚሉት አቶ ዱቤ፣ በተለይ አሁን ባለው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አትሌቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አዲስ አበባን ለሥልጠና ምርጫቸው ስለሚያደርጉ፣ የአየር ብክለቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከተማዋና የከተማዋ ዙሪያ ገባ በግንባታዎችና በሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የተነሳ ለአትሌቶች ዝግጅት አስቸጋሪ እየሆኑ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡ የተቋሙ ፕሬዚዳንት ኃይሌም በተለያዩ መድረኮች ይህንኑ በማስመልከት ደጋግሞ ሲናገር ተደምጧል፡፡

ለዓመታት በአንድ ማዕከል ዝግጅትና ሥልጠናውን በማከናወን የሚታወቀው የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን እንዲበተንና ዝግጅቱንም በሁሉም ክልሎች እንዲያከናውን የተደረገው፣ ከአደረጃጀት ጀምሮ በተቋሙ ውስጥ ለዓመታት ሲንከባለል የቆውን ችግር ከመሠረቱ ለማስወገድ ታስቦ እንደሆነ ኃይሌ ያናገራል፡፡

ክልሎችን ያማከለው ዝግጅትና የክትትል ክፍተት

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ2010 የውድድር ዓመት መጀመርያ፣ በሁሉም ክልሎችና የመስክ ዳሰሳ ጥናት ማድረጉን አቶ ዱቤ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ያከናወነው የመስክ ጥናትና ጉብኝት በአንታዊነቱ ቢታይም፣ የዳሰሳ ጥናቱን መነሻ በማድረግ ማስፈጸሚያ ሰነድ የተላከላቸው ክልሎች ምን ያህሉን ተግባር ላይ አውለዋል? በማለት ፌዴሬሽኑ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንዳልሠራ የሚወቅሱ ክልሎች አሉ፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ዱቤ እንዳሉት፣ ቀደም ሲል በሁሉም ክልሎች የተደረገው የመሰክ ጉብኝትና የዳሰሳ ጥናት ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ ጥናቱ ተጠናቆ በውጤቱ ላይ ክልሎችን በማሳተፍ የተደረገው ውይይት እስኪጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ፣ የቁጥጥርና ክትትል ሥራው በሚፈለገው መጠንና በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዳይሄድ ተፅዕኖ መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ በጥናቱ ላይ የተደረገውን የውይይት ግብዓት በማካተት ለሚመለከታቸው እንዲላክ መደረጉን የሚናገሩት አቶ ዱቤ፣ በሰነዱ አተገባበር ሒደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮች መነሻቸው ፌዴሬሽኑ የጊዜ መጣበብ ስለገጠመው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በ2011 የውድድር ዓመት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዕቅዶች አንዱና የመጀመርያው ይኸው ጉዳይ እንደሆነም አቶ ዱቤ ይገልጻሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት የቴክኒክ፣ የወድድር፣ የሥልጠናና ሌሎችም ጉዳዮች የሚመለከታቸው የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ባለሙያተኞች ግምገማ መቀመጣቸውና ኃይሌም ጠንካራ መመርያ መስጠቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከከተማ ውጪ የታቀደው ዝግጅትና ተቃውሞው

ብሔራዊ አትሌቶችን ጨምሮ ሌሎችም ስፖርተኞች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለው የአየር ሁኔታ ተዘጋጅተው ኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫን ቀርቶ በግል ውድድር ላይ ውጤታማ መሆን አይችሉም በማለት ኃይሌ ጠንካራ አቋሙን ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት አትሌቶችም ሆኑ አሠልጣኞች የፌዴሬሽኑ የመጀመርያ ምርጫ በሆነው በአሰላ ጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል ዝግጅት እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ መመርያዎች ቢወጡም ተቀባይነት ሳያገኙ መቅረታቸው ይነገራል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው አቶ ዱቤ በበኩላቸው፣ መመርያውን በመተላለፍ አልቀበልም ብሎ ያንገራገረ አትሌትም ሆነ አሠልጣኝ እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በቅርቡ የተደረጉትን ሁለት አኅጉራዊ ወድድሮችን ጭምሮ ለሌሎችም ዝግጅቶች ከአዲስ አበባ ይልቅ አሰላ የሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል ተመራጭ እንደሆነ ወስኖ በተግባር ለምን አልተፈጸመም? ለሚለው ጥያቄ አቶ ዱቤ ሲመልሱ፣ በፌዴሬሽኑ ፍላጎት እንጅ በአትሌቶቹና በአሠልጣኞች እምቢተኝነት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ግን፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት በአንድ ማዕከል እንዳይሆን ቢወስንም በርካታ ነገሮች ሲከናወኑ የሚስተዋለው ግን በፌዴሬሽኑ አልያም በአሠልጣኞች ሳይሆን፣ በአትሌቶች ፍላጎት ነው፡፡ አትሌቶች ለአሠልጣኞች ክብር የላቸውም፡፡ የአትሌቶች ፍላጎት ካልሆነ በቀር አሠልጣኞች ሰዓት ከመቆጣጠር ያለፈ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ካቆሙ ዓመታት ተቆጥረዋል፤›› በማለት አትሌቶች ከፌደሬሽኑ በተቃራኒው ሆነው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

እንደ አሠልጣኙ ማብራሪያ ከቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ (ነፍስ ኄር) ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ደ/ር) በኋላ፣ ለወትሮ በአትሌቶችና በአሠልጣኞች መካከል የነበረው መከባበር አሁን ላይ አይታሰብም በማለትም በተቋሙ ውስጥ ሥር እየሰደደ ስለመጣው የአትሌቶች ሥርዓት አልበኝነት ይናገራሉ፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከአንድ ወር በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ‹‹በአትሌቶችና አሠልጣኞች፣ የሠልጣኝነትና አሠልጣኝነት ግንኙነት መናናቅ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ አንዳንድ አትሌቶች ምናልባት በቆይታ ብዛት ሊሆን ይችላል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከአሠልጣኙ በላይ የሚሠሩትን የልምምድ ዓይነትና መጠን ያውቃሉ፡፡ አንድ አሠልጣኝ በሠልጣኙ ይህን ያህል የዕውቀት ንጽጽር ውስጥ የሚገባ ከሆነ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኝ በማንኛውም መመዘኛ ከሚያሠለጥነው አትሌት በላይ የሆነ ሙያዊ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፤›› በማለት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያስረዳበት መንገድ ይጠቀሳል፡፡

አቅም ያላቸው አትሌቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝግጅት ከማድረግ ይልቅ ወደ ተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ግዛቶች መጓዝን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ለዚህም ዮሚፍ ቀጀልቻና ገንዘቤ ዲባባን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቶችና በአሠልጣኞች መካከል ያለውን የሙያ ክህሎት ማቀራረብ የሚችል፣ በየጊዜው ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚያሻሽል የአሠልጣኞች የሙያ ሥልጠና መስጠት በቋሚነት ማዘጋጀት እንደሚገባው የሚመክሩ አልታጡም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...