Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ጥቁር ገበያውን ለመቀነስ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማስፋፊያ አሠራሮችን ማስፈን ይገባል››

አቶ አዲሱ ሃባ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት

አቶ አዲሱ ሃባ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ባንኮች አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪው ከ40 ዓመታት በላይ የሠሩ ሲሆን፣ በተለይ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በኋላም የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡ በባንኮች ግፊት እየተደረገባቸው ያሉ  መመርያዎች ለውጥ ላይ የባንኮች ማኅበር ምን እያደረገ እንደሆነና ሰሞኑን ተደረጉ የተባሉትን መጠነኛ ማሻሻያዎች በተመለከተ ዳዊት ታዬ አቶ አዲሱ ሃባን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት አቋም በተለይ ባንኮች በምን ደረጃ ላይ ናቸው ማለት ይቻላል?

አቶ አዲሱ፡- ባንኮች የዚህ ዓመት አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳየው ጥርት ያለ ሪፖርት ገና ቢሆንም፣ ከግርድፍ መረጃዎች የምንመለከተው አሁንም ዕድገት እያሳዩ መቀጠላቸውን ነው፡፡ ጥሩ አፈጻጸም እንዳላቸውና ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውን ለመረዳት ይቻላል፡፡ አሁንም ትርፋማ ናቸው፡፡ በቅርንጫፎች ብዛት፣ በካፒታልና ከሰጡት የብድር መጠን አንፃር ካየናቸው ዕድገቱ መቀጠሉ ግልጽ ነው፡፡ በጥቅሉ የአገሪቱን ባንኮች ከተለያዩ መለኪያዎች አንፃር ስንመዝናቸው ጥሩ ውጤት የታየባቸው ሆነዋል፡፡ እኔ የምመራውን ባንክ ብጠቅስልህ እንኳን በተለየ ሁኔታ ጥሩ ውጤት የተገኘበት ዓመት ነው ልል እችላለሁ፡፡ ስለዚህ በየትኛውም መለኪያ ባንኮች ዕድገት አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማደግ የሚገባቸውን ያህል አድገዋል ወይ? ከተባለ መልሱ አላደጉም ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ስለመሆኑ ከሚታዩት አኃዛዊ መረጃዎች አንፃር ብዙ የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡ ማደግ የሚገባቸውን ያህል አላደጉም የምንልበት ምክንያት ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶች በመኖራቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተግዳሮቶቹ ምንድናቸው?

አቶ አዲሱ፡- ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የተፈለገውን ያህል የሠለጠነ የሰው ኃይል ያለማግኘት ችግር አለ፡፡ የባንክ ቴክኖሎጂን ፈጥኖ ወደ ኅብረተሰቡ በማድረሱ ረገድ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በሚፈለገው መጠን ማደግ አልተቻለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የግል ባንኮች ከሚያበድሩት ብድር ላይ 27 በመቶውን እያሰሉ ለብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዥ እንዲያውሉ እንደተደረገበት ዓይነት መመርያዎችም፣ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህንን ለቦንድ ግዥ የሚውል ገንዘብ በገበያ ዋጋ ብናበድር የተሻለ ጥቅም እናገኝ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮች ከምናገኘው የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ እንድንሰጥ የሚያስገድደውን መመርያም ቢሆን ባንኮች እንደ ተግዳሮት የሚያዩት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰጡትን ገንዘብ ደግሞ ባንኮች ቢሠሩበት ኖሮ የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት መሆኑ ሲታሰብ፣ እንዲህ ያሉ መመርያዎች መሻሻል እንደሚኖርባቸው ያመለክታል፡፡ እንዲህ ያሉ መመርያዎች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አሁን ካገኙት ውጤት በላይ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ዕድል ይኖር ነበር፡፡  ከመሠረተ ልማት አኳያም ቢሆን ኮሙዩኒኬሽን ራሱ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ባንኮች የጠራ አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡ የኔትወርክ መቆራረጥ አለ፡፡ በተፈለገው መጠን እየቀረበ ባለመሆኑ ባንኮች የሚገባቸውን ያህል እንዳያድጉ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠትና ለማስፋፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት ሊጎዳ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት ማኅበር ለባንኮች እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እየሆኑ ናቸው ያላቸው መመርያዎች እንዲሻሻሉ፣ በቅርቡ ጥያቄ ማቅረባችሁ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ማሻሻያ ይገባቸዋል ብላችሁ ያቀረባችዋቸው መመርያዎች ምን ዓይነት ይዘት ያላቸው ናቸው? እርስዎስ ምን ይላሉ?

አቶ አዲሱ፡- ለሥራችን ማነቆ ናቸው ብለን የለየናቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቅርበናል፡፡ መሠረት ያደረግነው ደግሞ ቀደም ብለው የወጡ መመርያዎችን በተመለከተ፣ መሻሻል አለባቸው በማለት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንወያይ ብለን ያቀረብነው ነው፡፡ እነዚህ መመርያዎች ባንኮች በሚገባቸው መጠን ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አድርገዋል ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ለምሳሌ 27 በመቶ የቦንድ ግዥ ተካቷል፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎ ስቶክ ማርኬት መፈጠር አለበት የሚል ሐሳብ ያካተተ ነው፡፡ ባንኮች በአጭር ጊዜ ብድር ላይ ነው ያተኮሩት፡፡ ስለዚህ የረዥም ጊዜ ብድር ለመስጠት የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ ስቶክ ማርኬት የግድ በመሆኑ፣ ኢንዱስትሪው የተሻለ ውጤት እንዲኖረው እንዲህ ያሉ ሐሳቦችም ያቀረብንበት ነው፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ ውድድር እንዲኖር መሻሻል ያለባቸው አሠራሮች እንዲኖሩ ጠይቀናል፡፡ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ጥብቅ የኢኮኖሚ ግንኙነት አላት፡፡ ወደ ቻይና የሚደረግ ኤክስፖርት በሙሉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ነው የሚካሄደው፡፡ ይህ ደግሞ የግል ባንኮችን እየጎዳ በመሆኑ ይህንን የሚመለከተው መመርያ መሻሻል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥም ወደ ቻይና ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት ሁሉ በንግድ ባንክ በኩል ተፈጻሚ እንዲሆን መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ተገቢ ያልሆነ አሠራር እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የግል ባንኮችንም ስለመጉዳቱ በግልጽ የታየ ነው፡፡ እስኪ የዚህ መመርያ ጉዳት እንዴት እንደሚገለጽ ያብራሩልኝ? ለዚህ መመርያ መውጣት ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰውስ ምንድነው? ለእናንተ የተነገራችሁ ነገር ነበር?

አቶ አዲሱ፡- እሱን በግልጽ ተናግረናል፣ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ አገሪቱ ያለባትን ብድር ለመክፈል ታስቦ የወጣ ነው፡፡ ዕዳው የሚከፈለው ደግሞ ከወጪ ንግድ ከሚገኝ ገቢ በመሆኑ፣ ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሆነው በዚያው በባንኩ በኩል ዕዳው እንዲከፈል ነው፡፡ የዚህ መመርያ ተግባራዊ መሆን ግን የግል ባንኮች ደንበኞችን ወደ ንግድ ባንክ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ በመባሉ፣ ከሌሎች ባንኮች ጋር ይሠሩ የነበሩ ላኪዎች ደንበኝነታቸውን አቋርጠው ወደ ንግድ ባንክ እንዲሄዱ ያስገድዳል፡፡ የእኛ ደንበኛ የሆኑና ምርቶቻቸውን ወደ ቻይና ይልኩ የነበሩ ደንበኞችን በእኛ በኩል ምርታቸውን ወደ ቻይና መላክ ስለማይችሉ፣ ባንኮቻችን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያገኙ ማድረጉም ጉዳት ነው፡፡ በዚህ መመርያ ምክንያት የግል ባንኮች ደንበኞች ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሄደዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- መመርያው ወደ ቻይና በሚላኩ ምርቶች የአገሪቱ የግል ባንኮች ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳያደርጉ የገደበ ነው ማለት ነው?

አቶ አዲሱ፡- አዎ፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት የግል ባንኮች ጥቅም ተነክቷል፡፡ በእኛ በኩል ምርት ወደ ቻይና ቢላክ ኖሮ ባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ፣ እንዲሁም ከወጪ ንግድ  የአገልግሎት ክፍያና ኮሚሽን እንዲያገኙ ያስችላቸው ነበር፡፡ ይህንን ዕድል አጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል ብላችሁ ላቀረባችሁት ጥያቄ ምን ምላሽ እያገኛችሁ ነው?

አቶ አዲሱ፡- ገና ነው፡፡ በእነሱ በኩል (በብሔራዊ ባንክ) ጥናት እየተጠና ነው፡፡ ከእኛ ጋርም ውይይት ያደርጋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም ሐሳቦችን በዝርዝር ማቅረብ አለብን፡፡ ከዚያ ተነስተው ማሻሻያውን እንዲያደርጉ እንፈልጋለን፡፡ ለምሳሌ 27 በመቶው የቦንድ ግዥ መመርያ ጨርሶ እንዲነሳ እንፈልጋለን፡፡ ካልሆነ መጠኑ ይቀንስ፡፡ ይህ ባይቻል እንኳን ለቦንድ ግዥ ለምናወጣው ገንዘብ የተሻለ ወለድ ይከፈለን ብለን እየጠየቅን ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ አቅርበናል፡፡ ይህ ግን ውይይት የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ በ27 በመቶው የቦንድ ግዥው መመርያ ላይ ማሻሻያ ብሎ ያስታወቀው፣ ለቦንድ ግዥ ይከፈል የነበረውን የሦስት በመቶ የወለድ መጠን ወደ አምስት በመቶ ማሳደጉን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከለውጥ አይቆጠርም የሚሉ አሉ፡፡ ማሻሻያው የታሰበውን ያህል አልሆነም ማለት ነው?

አቶ አዲሱ፡- አንደኛ ብዙዎቹ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ የሚያሰባስቡት ሰባት በመቶ ወለድ በመክፈል ነው፡፡ ይህ ዝቅተኛው ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈል የወለድ መጠን ነው፡፡ በጊዜ ገደብ ለሚያሰባስቡት ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ ከአሥር በመቶ በላይ ነው፡፡ 12 በመቶ 13 በመቶ የሚከፈልበት የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ የዚህን ያህል ወለድ እየከፈልን የሰበሰብነውን ገንዘብ ነው እንግዲህ ቦንድ ስንገዛ ሦስት በመቶ ብቻ ወለድ ሲታሰብልን የነበረው፡፡ አሁን ደግሞ አምስት በመቶ ሆኗል፡፡ ስለዚህ አሁንም የባንኮች ወጪ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፣ ቢያንስ በዝቅተኛው የወለድ መጠን ሰባት በመቶ እንኳን ቢሆን ምናለ ብለን ነው ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ ለቦንድ ግዥ የምናውለው ገንዘብ አምስት በመቶ መሆን አለበት ብለን ጠይቀን የነበረው ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. በፊት ነው፡፡ ከጥቅምት በኋላ ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው ወለድ ሰባት በመቶ እንዲሆን በመወሰኑ፣ በቅርቡ ያስገባነው ጥያቄ ለቦንድ ግዥው የሚለው ገንዘብ የሚታሰብለት ወለድ ወደ ሰባት ከፍ እንዲል ነው፡፡ ዋናው ጥያቄያችን ግን የቦንድ ግዥው መመርያ ይቅር ወይም መጠኑ ይቀንስ የሚል ነው፡፡ አሁን የተደረገው ማሻሻያ ትንሽም ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ግን በመሠረታዊ ጥያቄያችን ላይ አሁንም ውይይት እንዲደረግና ለምን 27 በመቶው ይቅር ብለን እንደምንሞግት ማብራሪያ እንሰጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በእኛ በኩል እንግዲህ ከሦስት አምስት ይሻላል፡፡ እስካሁን ለብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ የምናውለው ገንዘብ ሦስት በመቶ እየታሰበለት ቆይቷል፡፡ አምስት በመቶ መሆኑ ለውጥ ነው፡፡ ግን ወጪያችንን መሠረት አድርጎ መሻሻል አለበት፡፡ 

ሪፖርተር፡- አሁን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የተባሉ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፡፡ እርስዎ በፋይናንስ ዘርፍ መለወጥ አለበት የሚሉት ወይም የፋይናንስ ዘርፉ ቀጥታ እንዲህ ቢሆን ይሻላል ብለው የሚያስቡት ነገር አለ?

አቶ አዲሱ፡- የፋይናንስ ዘርፉ ለውጥን ስንመለከት የአገሪቱ የለውጥ አካል ነው፡፡ ለውጡን የተመለከቱ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ባንኮችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ዘርፉን በሚገባ ለማንቀሳቀስ የሚታዩ ማነቆዎች ተነስተው፣ ለአገሪቱ ለውጥ አጋዥ መሆን በሚችልበት ደረጃ መቃኘት አለበት፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ያልተሳተፈበት ማንኛውም ዕቅድ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስለዚህ በየትኛውም መንገድ አብሮ ለማደግ በፋይናንስ ዘርፉም ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ የሚያስፈልግ ከፋይናንስ ዝግጅት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ይጠበቅበታል፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ ሲታሰብ ለፋይናንስ ኢንዱስትሪውም ትልቅ ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ራሱን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አሁን  አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው አመለካከት የበለጠ ወደ ግል ዘርፉ እያጋደለ ስለሆነ፣ ይኼ ደግሞ የተሻለ እንድንወዳደርና የተሻለ እንድንሠራ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የተሻለ አቅም እየፈጠርን መሄድ አለብን፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በተደራሽነትና በመሳሰሉት ባንኮች የበለጠ መሥራት አለባቸው፡፡ አሁን እንደምናየው ባንኮች ትኩረት ያደረጉት ከተማ አካባቢ ነው፡፡ ወጣ ብለን ለመሥራት በሚያስችለን ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ይደረጋል ሲባል እንደ ቴሌ ያሉ ተቋማት ቀጥታ ተዋናይ ስለሆኑ፣ እነሱም ከለውጡና ከሚፈለገው ዕድገት ጋር መራመድ አለባቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- እንግዲህ አሁን እየተደረጉ ካሉ እንቅስቃሴዎች አንፃር ወደፊት የውጭ ባንኮች ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የአገራችን ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ? እንዲህ ያለው ዕርምጃስ እንዴት መሆን አለበት?

አቶ አዲሱ፡- በእኔ እምነት የእኛ ባንኮች አቅም ገና ነው፡፡ ጠንካራ አይደሉም፡፡ ቢደመሩ እንኳን በሌላ አገር የሚገኝ መካከለኛ የሚባል ባንክን ያህል አይሆኑም፡፡ ውድድሩን መቋቋም አለባቸው ሲባል ዝም ብሎ ፍላጎት ሳይሆን፣ በተደራጀ መንገድ አቅማቸው እንዲያድግ መደረግ አለበት፡፡ የውጭዎቹ በቴክኖሎጂ የተደራጁ ናቸው፡፡ የተሻለ የሰው ኃይል አላቸው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው ሁኔታ ራሳችንን ካላዘጋጀን በቀር፣ አሁን የውጭ ባንኮች ይግቡ ቢባል ገበያውን ይቆጣጠሩታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ውሳኔ በፊት የአገር ውስጥ ባንኮችን እንዲደራጁ ማድረግ ይገባል፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱ በባንኮች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ጥቅሙ እዚሁ ይቀራል፡፡ መልሰው ኢንቨስት የሚያደርጉት እዚሁ ነው፡፡ የውጭዎቹ ግን ጥቅማቸውን ይዘው ነው የሚወጡት፡፡ ከዚህ አኳያ የውጭ ባንኮች ቢገቡ የሚባለው እንዳለ ሆኖ፣ የአገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን ማደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼ በሌለበት ሁኔታ ዝም ብሎ ይግቡ ከተባለ አደጋ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ዓለምን መምሰል ግድ ነው እየተባለ ነው፡፡ አሁን እንኳን ባይሆን ነገ የውጭ ባንኮች ሊገቡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላልና እንዴት ይስተናገዳሉ?

አቶ አዲሱ፡- አገባባቸው እንዴት ይሁን የሚለው ጥናት ላይ ተመሥርቶ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳት በማያደርሱበት ሁኔታ በየትኛው ዘርፍ ይሳተፉ? በጥምረት ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር መጓዝ ይገባቸዋል ወይ? የሚሉትና ዙሪያ ገባውን ማየት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ባንኮች ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የሚሰጡት ብድር ከፍተኛ መጠን ያለው ወለድ እየተጠየቀበት ነው፡፡ ለአንድ ሥራ ብድር ሲጠየቅ ለብድሩ እስከ 20 በመቶ ወለድ እየተከፈለም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህን ያህል የወለድ መጠን ብድር ማቅረብ አደጋ የለውም? በኢንቨስትመንት ዕድገት ላይስ ተፅዕኖ አይኖረውም?

አቶ አዲሱ፡- ምንም ጥያቄ የለውም፣ የወለድ መጠን መጨመር ኢንቨስትመንቱን አያበረታታም፡፡ አሁን ወለድ በጨመረ ቁጥር የሚመረተው ምርት ገበያ ላይ ሲወጣ ውድ ይሆናል፡፡ ውድ ከሆነ የሰዎች የመግዛት አቅም ይቀንሳል፡፡ ሽያጭ ከሌለ ደግሞ ፋብሪካዎችና እርሻዎች ለማምረት አይበረታቱም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ላለው የባንኮች ወለድ እየጨመረ የመጣበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አዲሱ፡- በባንኮች በኩል ሲታይ የብድር ወለድ መጠን መጨመር ባንኮች በጊዜ ገደብ ተቀማጭ በምንሰበስብበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ወለድ እየከፈለበት መሆኑ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪዎች አሉ፡፡ ከሠራተኛ ደመወዝ ጀምሮ ወጪያቸው እየጨመረ ነው፡፡ ቅርንጫፎች በመጨመር ቁጥር አሁን እየጨመረ ካለው የቤት ኪራይ አንፃር እየወጣ ያለው ወጪ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ እኛም አገልግሎት ለመስጠት በምናደርገው ጥረት በዙሪያችን እየጨመረ ካለው ውጪ ጋር አናበን የሚያዋጣንን ነው የምናቀርበው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ እስከ 14 በመቶ ወለድ ሰብስበን የምናመጣው ተቀማጭ ገንዘብ ቦንድ ስንገዛበት የሚታሰበው ወለድ ሦስት በመቶ መሆንም፣ ለባንኮች የብድር ወለድ መጠን መጨመር ሌላ ምክንያት ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እናድርግ ካልን ትርፋችን ማደግ አለበት፡፡ የሰው ኃይል እናፍራ ካልን የግድ ገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የሆኑ ወደ ዕድገት የሚወስዱ ተግባራትን ለማከናወን ትርፋችን ማደግ አለበት፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ባንኮቻችን ደካሞች ናቸው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ትርፍ አትርፈን አቅማችንን እያጎለበትን ለመሄድ አንዱ የብድር ወለድ መጠንን ማሳደግ ነው፡፡ ነገር ግን ገቢያችን ወለድ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን የወለድ ወጪንና የወለድ ገቢን ብናነፃፅርና ሌሎች ወጪዎችንም እዚህ ጋ ብናመጣ፣ ከወለድ የሚገኘው ትርፍ ብዙም አይደለም፡፡ ባይሆን ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ የምንሠራው ሥራ የሚያመጣው ትርፍ ነው የሚያካክሰው፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ ሲታይ የብድር ወለድ የጨመረው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የወጣውን ወጪያችንን ለመሸፈን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ ምን እያደረገ ነው? አባል ባንኮችን ጠቅሟል ትላላችሁ?

አቶ አዲሱ፡- ማኅበሩ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ምድነው? አትራፊ ድርጅት አይደለም፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በመመርያዎች ላይ ያለውን ሐሳብ ይሰጣል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ከዚህ ባሻገር እርስ በርስ አንዳንድ ያለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ የምናስታርቅበትም መድረክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዕርቅ የሚያበቃ በባንኮች መካከል ምን የሚፈጠር አለመግባባት አለ?

አቶ አዲሱ፡- ይፈጠራል፣ ተፈጥሯልም፡፡ ለምሳሌ አንዱ ባንክ ቅርንጫፍ ለመክፈት የያዘውን ቦታ ሌላው ለመውሰድ የሚጥርበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዱ የሌላውን ደንበኛ የመቀማት ዓይነት ነገርም ሊታይ ይችላል፡፡ ይህም አንዱ ባንክ በጥሩ ሁኔታ ይዞ ያሳደገውን ደንበኛ፣ ሌላው ሳይለፋና ሳይደክም ብድር ሰጥቶ ለመቀማት መሞከርና የመሳሰሉት ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያላግባብ የዋጋ ጦርነት ውስጥ የመግባት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ያልተገባ የቢሮ ኪራይ ዋጋን መስቀል፣ በጊዜ ገደብ ለሚቀመጥ ገንዘብ የሚከፈል ወለድ ላይ መጨመር አለ፡፡ ይህንን ያደረገውን ባንክ ኧረ ይህንን ነገር ተው ማለትም አለ፡፡ ነገር ግን አቁም አንልም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ቢሮ አካባቢ ያሉ መደብሮች በሙሉ ታሽገዋል፡፡ የታሸጉት ደግሞ በጥቁር ገበያ ንግድ ስለተሰማሩ ነው፡፡ በጥቁር ገበያው ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንዲህ ያለው ደረጃ መድረሱ ችግሩን ያሳያል፡፡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ እንደ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ አዲሱ፡- ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡ ‹ፓራራል› ገበያ ወይም ጥቁር ገበያ የምንለው ነገር የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለማስቀረት ጥቁር ገበያ ይካሄድባቸዋል የተባሉ መደብሮችን ማሸግ ብቻ መድኃኒት አይሆንም፡፡ እጥረቱ እስካለ ድረስ አሁንም ሌላ መንገድ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኘቱን እንዴት እናስፋ? እንዴት እናሳድግ የሚለው ነገር ላይ መሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ አዲሱ፡- ይኼ እንግዲህ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ነው ሊሠራ የሚችለው፡፡ ለኮንስትራክሽንም ይሁን ለፋብሪካ የሚሆኑ ግብዓቶችን የምናስገባው ከውጭ ነው፡፡ ይህንን ከውጭ የምናስገባውን ግብዓት ማስቀረት እንኳን ባንችል እንዴት ነው መቀነስ ያለብን? ብሎ መሥራት ይጠይቃል፡፡ የአገር ውስጥ ምርትን መጨመር ያስፈልጋል፡፡ በእርሻው ረገድም ለምሳሌ ቡናን ብንወስድ ዋጋው እየወረደ ነው፡፡ ስለዚህ ምርቱን መጨመርና በጥራት እንዲላክ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ የወጪ ምርቶችን ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገባ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠርም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡ አሁን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስገባት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል ይባላል፡፡ ግን አሁንም ብዙ መሥራትና ማየት የሚገቡን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰላም ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ አንድ ኢንቨስተር ቢጎዳ ሺዎች እንደተጎዱ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ስለዚህ ሰላማዊና አስተማማኝ ከባቢ መፈጠር አለበት፡፡ ሌላው ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎችም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም ይዘው ሳይመጡ ገንዘባችንን አጭበርብረው ስለሚወጡ፣ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቆጣጠር የሚያስችል የጠነከረ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እየተገኘበት ያለው ቱሪዝም ላይም ጠንክሮ መሥራት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት በአጭር ጊዜ መሠራት ያለባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ረዥም ጊዜ የሚጠይቁ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ ዘርፎችን ለይቶ ከአሁኑ የፖሊሲ ለውጦችን በማድረግ ጭምር መሠራት አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በዳያስፖራው ላይ የተፈጠረውን መልካም አመለካከት ተከትሎ እየታየ ያለው ለውጥም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ወደ አገር ዶላር አትላኩ የሚለው ነገር ቀርቶ፣ እንዲያውም ጨምረን መላክ አለብን መባሉ ራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህም እንዲጎለብት ማድረግ ያሻል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ያለው የውጭ ምንዛሪ ጨምሯል ማለት ይቻላል?

አቶ አዲሱ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሪ በባንክ እንዲመነዘር አቅጣጫ ከሰጡ በኋላ ባንካችን በካሽ የተሻለ ግዥ ፈጽሟል፡፡ በገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችም ከቀድሞ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ እየመጣ ነው፣ ለውጥ አለው፡፡ ዕድገት ይታያል፡፡ ይህንን ማስቀጠል ይገባል፡፡ ስለዚህ ጥቁር ገበያውን ለመቀነስ እንዲህ ያሉ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማስፋፊያ አሠራሮችን ማስፈን ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በማሻሻል በአጭር ጊዜ ለውጥ መንግሥት ትልልቅ ተቋማትን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ለማዛወር የሚሻል መሆኑን በማሳወቅ፣ ይህንን ለማስፈጸም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ይህንን የመንግሥት አቋም እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ አዲሱ፡- መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ጊዜያዊ ችግሩን ለመወጣት ነው፡፡ የውጭ ዕዳ ለመክፈልና ለሌሎች ተግባራት የውጭ ምንዛሪ ከመፈለግ አኳያ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉትን የተመለከትን ከሆነ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቋማት ሊኖርባቸው የሚችለውን ክፍተት በመድፈን እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ እኔ በመንግሥት እጅ ቢቆዩ እላለሁ፡፡ አገራዊ ጠቀሜታቸው ታስቦ ቢጤን ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ ችግሩስ እንዴት ይፈታ ታዲያ?

አቶ አዲሱ፡- አገራዊ ችግሩን ለመፍታት ሌሎች ነገሮችም ማሰብ ይገባል፡፡ ፕራይቬታይዝድ በሚደረግበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ትተን ቴሌን፣ መብራት ኃይል፣ ንግድ መርከብ ድርጅትን ብንወስድ በጥቂት ብልጣ ብልጦች እንዳይጠለፉ  መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በሌሎች አገሮች ፕራይቬታይዝ በሚደረግበት ጊዜ ጥቂቶች ቢሊየነር የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም እንዳይመጣ የረዥም ጊዜውንም በማሰብ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ መንግሥት የገጠመውን ችግር እንዴት መፍታት ይችላል የሚለውን ብድርን በብድር ባንልም፣ በአገር ደረጃ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ጅምር ጥሩ ሥራ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እንዲህ ያሉ ሥራዎች የሚሠሩት አብዛኛውን ሕዝብ ለመጥቀም ነውና ጥቂቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መሠራት አለበት፡፡ ፕራይቬታይዝ የሚደረጉት ድርጅቶች ለሁሉም ኅብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ከመሆናቸው አንፃር፣ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ቴሌን ብንወስድ ሁለት ቦታ መክፈል ቢቻል የተሻለ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ፕራይቬታይዝ ተደርጎ ግማሹ የግል ግማሹ የመንግሥት ከሆነ ብዙም ለውጥ ላይኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም አሁን የታሰበው የቴሌን አክሲዮን መሸጥ ነው፡፡ ስለዚህ የባለቤትነት ይዞታን መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቴሌ ዓይንት ሌላ ተወዳዳሪ ኩባንያ የሚፈጠርበት ሁኔታ መፈጠርም ማካተት ይገባል፡፡ እንዲህ ማድረጉ በተሻለ አገልግሎት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አገሪቱም ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡ ተወዳዳሪ መፈጠር አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...