Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚሠሩ 40 ኩባንያዎች ያልተገባ ሒሳብ ከተጠቃሚዎች በመውሰዳቸው ታግደዋል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ያለአግባብ ከቴሌኮም ደንበኞች ተቆርጧል

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ከሚሰጡ ከ180 በላይ ኩባንያዎች ውስጥ 40ዎቹ መታገዳቸውን ኩባንያው ይፋ አደርጓል፡፡ ያለአግባብ ከደንበኞች ገንዘብ የቆረጡ ኩባንያዎችን በፍርድ ቤት ጭምር የወሰዱትን ገንዘብ እንደሚያስመልስ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በቴሌኮም ደንበኞች ዘንድ በተደጋጋሚ አቤቱታ ከሚቀርብባቸው ጉዳዮች አንዱ ያለፍላጎታቸው በስልኮቻቸው የሚደርሳቸው የአጫጭር መልዕክቶች ናቸው፡፡ የዕርዳታ፣ የሽልማት፣ የመረጃ ንግድና ሌሎችም ይዘቶች ያሏቸው መልዕክቶች በርካቶችን እንዳማረሩ ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ የቴሌኮም ተጠቃሚዎች ያለፍላጎታቸው በሚደርሳቸው መልዕክት መታወካቸው ብቻም ሳይሆን፣ ከስልኮቻቸው ገንዘብ እየተቆረጠ መልክዕቱን ወደሚልኩት አካላት እየገባ ይገኛል፡፡

በቅርቡ በኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ በተደረጉ የታሪፍ ማሻሻያዎች ላይ መግለጫ የሰጡት አዲሷ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ እንዲህ ያለው የደንበኞች አቤቱታ ኩባንያው እየደረሰው ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ በአጭር የሞባይል መልዕክት የሚሰጠው አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውል በገቡ ኩባንያዎች አማካይነት የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ አገልግሎቶቹ በኢንፎሜሽን የበለፀገ ማኅበረሰብ ከመገንባት አንፃር ሚናቸው እንደሚጎላ ጠቁመው፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ግን መፈተሽ እንዳለበት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

አጭር መልዕክቶችን በስልክ በማስተላለፍ የሚሠሩ 180 አጋር ኩባንያዎች እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በገቡት የውል ግዴታ መሠረት መሥራት ቢጠበቅባቸውም፣ አንዳንዶቹ ከውል ውጭ በሆነ መንገድ ስለሚሠሩ ችግሮች እንደሚታዩ፣ ከእነዚህ ችግሮች መካከልም ደንበኞች ያለፍላጎታቸው መልዕክት እንዲደርሳቸው ማድረግ እንደሆነ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡ ከተገልጋዩ ጋር በተደረገ ውይይት፣ ይህ ችግር በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚቀርብበት ሲያብራሩም፣ ‹በማንፈልገው ሰዓት መረጃ ይመጣልናል›፣ ‹እንዲመጣልን ሳንጠየቅ መረጃ ይመጣልናል›፣ የሚሉ በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹ጥያቄው ለረዥም ጊዜ ሲቀርብ የነበረ ቢሆንም በአግባቡ ምላሽ አልተሰጠበትም፤›› በማለት ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ካሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች በመነሳት ጉዳዩ በምን መንገድ መታየት እንዳለበት ማጣራት ተካሂዶ ለጊዜው መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ዕምጃዎች ስለመወሰዳቸውም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በተደረገው ማጣራትም አገልግሎቱን የሚሰጡ የኢትዮ ቴሌኮም አጋር ኩባንያዎች ፈቃድ ሳያገኙ ለደንበኞች የአጭር የጽሑፍ መልዕክት በማስተላለፋቸውና ከደንበኞችም ያለአግባብ ገንዘብ ሲቆርጡ መቆየታቸው ተረጋግጧል፡፡

በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ከደንበኞች ጋር በቀጥታ ውል ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በመሆኑ የደንበኞችን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በማስታወቅ፣ እሴት የተጨመረባቸውን የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ከሚሠሩ አጋር ኩባንያዎች ጋር ያለውን ውለታ በመፈተሽ ከውል ውጭ የተካሄዱ እንቅስቃሴዎችን በመለየት ዕርምጃ እንደሚወሰድ ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስታውቀዋል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን በውላቸው መሠረት ያልሠሩትንም በደብዳቤ እንዲያውቁት መደረጉን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ አገልግሎቱ እንደማይቋረጥ፣ ነገር ግን ኩባንያዎቹ ደንብና ሥርዓቱን ተከትለው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ‹‹ደንበኞችን ማስቸገር የለብንም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ባደረገው ማጣራት 23 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከደንበኞች ተቆርጧል፡፡ ይህ አግባብ ባለመሆኑ በዚህ ተግባር  ተሰማርተው የተገኙት ላይ በውሉ መሠረት ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከሪፖርተር የተጠየቁት የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም መሐመድ፣ ከገቡት ውል ውጭ መልዕክት ሲልኩና ገንዘብ ሲቆርጡ የነበሩ 40 ኩባንያዎች ስለመታገዳቸው ገልጸዋል፡፡ ወ/ሪት ፍሬሕይወት በበኩላቸው አሁንም በደንብና በሥርዓት የማይሠሩ ከሆነ ከነጭራሹ አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ እንደሚደረግ አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹የደንበኞቻችንን ፍላጎት እየተጋፉ ከደንበኞቻችን ላይ ገንዘብ እየቆረጡ አይቀጥሉም፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ከ180 ኩባንያዎች ጋር በሚሠራው የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮም የ300 ሚሊዮን ብር ገቢ ይሰበስባል፡፡ ‹‹የደንበኞቻችን ቅሬታ ግን ከቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህንን ተሸክመን መሄድ የለብንም፤›› በማለት ከኢትዮ ቴሌኮም አንፃር ክፍተቶች እንደሚታዩ አልሸሸጉም፡፡ ክፍተቶቹን ለመቅረፍ የዘረጋው ሥርዓት አለመኖሩም ችግር እንደነበር ጠቅሰው፣ እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት እንደሚጥሩ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊዋ እምነት በአጭር መልክዕቶች አማካይነት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተዋውለው የሚሠሩ ኩባንያዎች፣ መልዕክቱ የሚላክላቸውን ደንበኞች የስልክ አድራሻ አያሳውቁም፡፡ ይህ በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮምና አጋሮቹ ወቅቱን ጠብቀው ስለማይሠሩ ክፍተቱ ሊፈጠር እንደቻለ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ አሠራር ሒደት ኩባንያዎቹም ያቀረቧቸው ቅሬታዎች ስለመኖራቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቅሬታቸው አግባብ ከሆነ እናያለን፤ እንፈትሻለን፡፡ ያለአግባብ ዕርምጃ የወሰድንባቸው ካሉም ዕርማት የሚደረግበት አሠራር ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡ ደንብና ሥርዓቱን ጠብቀው ለሚሠሩ አሁንም የኢትዮ ቴሌኮም በር ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህ አገልግሎት ዙሪያ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የሚታዩ ችግሮች እንደሚታረሙም ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮምና በአጋር ኩባንያዎቹ መካከል የሚደረገው ውል ከሚያካትታቸው መካከል፣ መልዕክቱን የሚልኩበት ሰዓትና መልዕክቱን የሚልኩለት ደንበኛን ማንነትን መለየትና በዚያም መሠረት አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አቶ አብዱራህማን ይገልጻሉ፡፡ አያይዘውም እስካሁን አንድ ደንበኛ ያለፍላጎቱ ለተላከለት መልዕክት ‹‹አቁም›› ወይም ‹‹Stop›› የሚል ምላሽ ከሰጠ፣ መልዕክቱ ዳግመኛ እንዳይደርሰው መደረግ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡ ይሁንና ደንበኞች በውላቸው መሠረት በማይሠሩ ኩባንያዎች የሚደርስባቸው ጫና ዋነኛው ችግር ሆኖ ስለመገኘቱ ተብራርቷል፡፡

ያለአግባብ የተቆረጠባቸውን ገንዘብ ለደንበኞች ለማስመለስ የተለያዩ ዘዴዎች እንደሚተገበሩ ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ያለአግባብ ከደንበኞች ገንዘብ የቆረጡ ኩባንያዎችንና የተቆረጠውን ገንዘብ ኢትዮ ቴሌኮም አስቀድሞ መቆጣጠር እንዴት አይችልም? ለሚለው ጥያቄ፣ ኩባንያዎቹ ባለአራት አኃዝ የአገልግሎት ቁጥር ከተሰጣቸው በኋላ የሚያስተዳድሩትም ራሳቸው በመሆናቸው ችግሩ ሊከሰት ስለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ከደንበኞች ያለአግባብ ገንዘብ የቆረጡ ኩባንያዎች ፍርድ ቤት በመውሰድ ጭምር የወሰዱትን ገንዘብ ለማስመለስ እንደሚሠራ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች