Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የመንገድ ዳር ምርቶች

በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ ቢዝነሶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ሕጋዊና ሕገወጥ ግብይቶች ተደበላልቀው ሲሠራባቸው ማየት የተለመደ የሠርክ ተግባር ነው፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ፣ እንዲሁ በዘልማድ ሸቀጣ ሸቀጦችን በየጎዳናውና በየመንደሩ ሲቸበችቡ የሚውሉ ጥቂት አይደሉም፡፡

አብዛኞቹ የመንገድ ዳር ምርቶች፣ አምቻቸው የሚታወቅ፣ ባለቤት ያላቸው ወይም በመደበኛ መደብሮች ውስጥም የምናገኛቸው ናቸው፡፡ በየመንገዱ የሚሸጡ አልባሳትና መጫሚያዎች በየጎዳናው በአነስተኛ ዋጋ ይሸመታሉ፡፡ በተለይ ልባሽ ጨርቆችና አገልግሎት የሰጡ ምርቶችን ከጎዳና ነጋዴዎች ላይ በቀላሉ ማግኘት ያረጀና ያፈጀ የንግድ መስክ ነው፡፡ ነጋዴዎቹ ሕጋዊ ፈቃድ ባይኖራቸውም በርካታ ደንበኞች አሏቸው፡፡ ጎብኚያቸው በርካታ ነው፡፡   

በመንገድ ዳር ገበያ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ ከምግብ ሸቀጥ ጀምሮ ለዓይን እስከሚያታክተው ቁሳቁስ ድረስ መንገድ ሲያጣብብ ይታያል፡፡ የዚህ ንግድ ሥራ ተዋናዮች በግብር ሥርዓቱ ውስጥ አለመካታተቸው ብዙ ባያነጋግርም፣ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ሲፈታተኑ መታየታቸው አልቀረም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የመንገድ ንግድ መበራከቱ ለኮንትሮባንድ መስፋፋት ምክንያት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ሕገወጥና ሕጋዊ የግብይት መድረኮች እየተደበላለቁ ስንልም፣ በየመንገዱ የሚሸጡ ምርቶች ምንጫቸው ከየት ነው? ለሚል ጥያቄ በማንሳት ለምላሹ ከጣርን፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት መላቅጡ የጠፋበት መሆኑ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ሊነግረን ይችላል፡፡

ለማንኛውም መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሚካሄዱ ግብይቶች በየመንገዱ በግልጽ ሲሸቀጡ ከምናያቸው ውስጥ የመዋቢያና የንጽህና መጠቢቂያ ምርቶች ይገኙባቸዋል፡፡ በቀላሉ በፀሐይና በአቡዋራ የሚበላሹ የምግብና የመጠት ዓይነቶችም በገፍ ይቸበቸባሉ፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ምርቶች በአዲስ አበባ ከተማ  በርካቶች በሚያዘወትሯቸው ጉዳናዎች ላይ በጠራራ ፀሐይ፣ ያውም በታዋቂ አርቲስት ተብዬዎች በሚለፈፉ ማስታወቂያዎች እየታጀቡ ላይ እንደ ልብ የሚሸጡ ምርቶች እተበራከቱ ነው፡፡

የሥራ ፈጠራውም ሆነ ምርቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ የሚደገፍ ሆኖ ሳለ፣ በተከለከለ መንገድ፣ የከተማውም ሆነ የአገሪቱ የንግድ ሕግ በማይፈቅደው አሠራር በየጎዳናው ዳር፣ በመኪናና በጃንጥላ ሥር እየተቀመጡ ለመዋቢያናነት የሚውሉ ምርቶችን የሚሸጡና የሚሸምቱ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ምርቶችን እንዲህ ባለው መንገድ መሸጥ ትክክል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የምርት ይዘታቸውና የጥራት ደረጃቸውን በሚመለከት ማስማመኛ የሚሰጥ ተቋምና አምራች ወይም ሕጋዊ ነጋዴ በሌለበት አግባብ ምርቶቹ ወደ ተጠቃሚው መቅረባቸው፣ የጥራት መዝሙር በሚደሰኮርበት አገር ውስጥ የሚያገባውና የሚመለከተው አካል ለማስተካከል ሲረባረብ አለመታየቱ አጀብ ያሰኛል፡፡   

ለፀጉር፣ ለሰውነት ቆዳና ለሌላም የሰውነት ክፍል እንደሚውሉ የሚለፈፍላቸውን ምርቶች ከጤና አኳያ በመመልከት ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት በምን አግባብ እንተመረቱ፣ የሚሸጡበት መንገድ በብክልትና ለጤና አደገኛ የመሆን ዕድላቸውን በመመልከት ተገቢው ጥያቄ እንዲደረግ ማድረጉ ቸል የተባለበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ይህም ይቅር፤ ምርቶቹ ለገበያ ከመቅረባቸው በፊትስ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የምዘናና የጥራት ማረጋገጫ ተቋማት ተፈትሸው ለጤና ጎጂ አለመሆናቸውን እንዲያረጋግጥ መጠበቅ ቂልነት ይመስለኛል፡፡ በየአደባባዩ ለፀሐይና ለአቧራ ተጋልጠው የሚሸጡ ምርቶች የደረጃ መስፈሩን ቢያሟሉ እንኳ መበከላቸውና ለጤናም ቢሆን አደገኛነታቸው አይጠረጠርም፡፡

ከዚህ አንፃር የመዋቢያና ከሰውነት አካላት ጋር ንክኪ ያላቸው የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን እንዳሻቸው መንገድ ዳር እያወጡ መቸብቸብ፣ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ አድራሻቸው የማይታወቅ፣ አምራቻቸው ማን እንደሆነ የማይገልጹ ምርቶች ሲስፋፉ፣ የከተማም የፌደራልም የንግድ ሥራ የሚመለከታቸው፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ የሚገዳቸው፣ የደንብ ማስከበር ተጠሪዎችና የመሳሰሉት ተቋማት ምነው መደዴ ደሃውን ሲያራራጡ በሚውሉበት ጎዳና እንዲህ ያሉትን ሕገወጦች ተሰብሰቡ፣ አደብ ግዙ ማለት አቃታቸውሳ?

የመንግሥትን እንተወውና ሻጮቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ተጠቃሚዎችም ምርቶቹን ገዝተው ከመጠቀማቸው በፊት ስለ ምርቱ እርግጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ በዋጋ ረከሰ፣ በማስታወቂያ ተወደሰ ብለው የሚሻሙበት ምርት ለሕወታቸው ጠንቅ እንዳይሆን ደጋግመው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምርቶቹ እንደማንኛውም ሸቀጥ አለያም እንደ ሰልባጅ ጨርቅ (ይህም ቢሆን የራሱ በርካታ ጉዳቶች እንዳሉት ሆኖ) ሊሸቀጥ የሚችሉ አይደሉም፡፡ አደገኖች ናቸው፡፡ የኬሚካል ውጤቶች በመሆናቸው ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ማሰብና መጠርጠር ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ መድኃኒቶች፣ የመዋቢያ፣ የፅዳት ዕቃዎችና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶችን እንዳሻቸው በየመንገዱ ሲቸበቸቡ ዝም ማለትም ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር አይሆንም፡፡ መደበኛ ያልሆኑ ግብይቶችን ካልተቆጣጠርን ነገ የሚያስከትሉት አደጋ በተጠቃሚው ጤና መቃወስ ብቻ የሚገታ ሳይሆን፣ ሥርዓትን የሚያፈርስ ሊሆን ስለሚችል ከወዲሁ ቢታሰብበት ብልህነት ነው፡፡  

ነገር ነገር ያነሳዋልና፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የመድኃኒት መደብሮች ውስጥ ከሚሸጡ መድኃኒቶች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው እንደማይገቡ መጠቆም ያሻል፡፡ እንደ ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለሕመም ፈውስ የሚውሉ መድኃኒቶችም በኮንትሮባንድ በኩል መግባታቸውና በአንዳንድ መደብሮችም በይፋ ሲሸጡ መታየታቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ አዲስ ባይሆንም በኮንትሮባንድ የሚገባ መድኃኒት መንገድ ዳር እየተሸጠ ከሚገኘው መድኃኒት የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡

ሕግ መጣሱ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ የአንዳንድ መድኃኒት ቤቶቻችን መደርደሪዎች በሕገወጥ መንገድ፣ ከአንዱ ተሽከርካሪ ወደ ሌላው እየተገላበጡ የሚጓጓዙ ናቸው፡፡ ፈዋሽነታቸው ቀርቶብን የጤና ቀውስ ስላለማስከተላቸው ጸሎትን እንኳ የሚመልሰው አይመስለኝም፡፡

ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችም ቢሆኑ ሕዝቡን ከእንዲህ ያለው አስከፊ ብዝበዘባና የህልውና ሥጋት መታደግ ብቻም ሳይሆን፣ የመንግሥትን ሕግ ማስከበር፣ የጤናማውን ነጋዴ በአግባቡ ለፍቶ ማግኘትና የአምራቾችን የተወዳዳሪነትና የገበያ ተጠቃሚነት ሥርዓት ማስፈን የውዴታ ግዴታቸው በመሆኑ ነገሩን ችላ ማለታቸው ውሎ አድሮ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል ይገነዘቡት ይሆን?

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት