Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አድማ በአየር ክልል አስተዳደር ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

  የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አድማ በአየር ክልል አስተዳደር ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

  ቀን:

  በብሩክ አብዱና ነአምን አሸናፊ

  ከሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እየተደረገ ባለው የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚወጡና የሚገቡ አውሮፕላኖችን በአግባቡ ማስተናገድ ላይ ችግር እየፈጠረ እንዳለና አየር ላይ ባሉ ሁለት አውሮፕላኖች መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀር እንደማይጠበቅ የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር ዓርብ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

  ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ለጊዜው የተኩት ከውጭ አገርና በጡረታ ተገልለው የነበሩ ባለሙያዎች ቢሆኑም፣ ‹‹ከአዲስ አበባና ከናይሮቢ የሚነሱ አውሮፕላኖች ሲተላለፉ አስፈላጊውን ደረጃ የጠበቀ ልየታ እየተሠራ አይደለም፤ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ እየተላኩ ያሉ የበረራ ግመታዎች ሙሉ በሙሉ ስህተት ናቸው፤ የአውሮፕላን ዓይነትና መዳረሻቸው ሳይቀር ስህተት ይሆናሉ፤›› ሲል የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡

  መግለጫው አክሎም፣ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ተፈጽሞ የነበረው የትብብር ስምምነት መመርያዎች እየተጣሱ መሆኑንና፣ አደጋን ሊፈጥር በሚችል መንገድ አዲስ አበባ የሚገኙ ሠራተኞች ኬንያ ለሚገኙ ሠራተኞች ያለቅድመ ግመታ እንደሚደውሉም ያትታል፡፡

  በጡረታ ተገልለው የነበሩና አሁን የተጠሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአየር ክልሉ ግልዛቤ እንደሌላቸው፣ የትብብር መመርያውን እንደማያውቁ፣ ግራ እንደተጋቡና በዘገምተኝነታቸው ምክንያት የሚነገራቸውን ለመስማትና መልዕክት ለማስተላለፍ አዳጋች እንደሆነባቸው መግለጫው በሥጋት ይገልጻል፡፡

  ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፣ ማኅበሩ ያወጣው መግለጫ ሙሉ በሙሉ ስህተት እንደሆነና የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ራሳቸው በአድማ የሚታወቁ ስለሆኑ ለኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው አጋርነትን ለማሳየት ሲሉ ያወጡት መግለጫ ነው ብለዋል፡፡

  ባለሥልጣኑ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ለመላክ እያረቀቀ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የሚመለከታቸው ሁሉ መጥተው እንዲጎበኙና እንዲገመግሙ ለማድረግ በራችን ክፍት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ይህ ምናልባት ‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግር ውስጥ አለ› የሚለውን ምስል በመፍጠር የገበያ የበላይነትን ለመውሰድ የሚደረግ ሩጫ ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

  ማኅበሩ ግን፣ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት እንዲተባበሩ በማለት ለዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበር ፌዴሬሽን፣ ለኬንያ አየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበርና ለዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ግልባጭ ባደረገው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...