Sunday, October 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ትኩረት ለትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች!

  የአገር ጉዳይ ሲባል የመላው ሕዝባችን ጉዳይ ማለት ነው፡፡ የአገራችን ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበው የአገሩ ህልውና ነው፡፡ ይህ ህልውና ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን የጋራችን ናቸው የሚሏቸው ጥቅሞችና ፍላጎቶች በእኩልነት ሲከበሩ ነው፡፡ የአንድን ወገን ፍላጎት በሌላው ላይ በግድ ለመጫን መሞከር፣ ወይም የአንድ ጎራን የበላይነት ለማስፈን መጣጣር በዚህ ዘመን ተቀባይነት የለውም፡፡ ይልቁንም ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚያግባቡና ለጋራ ጥቅም የሚረዱ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ልዩነቶችን እንደ ፀጋ ተቀብሎ አገራዊ አንድነትን በመርህ ማጠናከር የወቅቱ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከትውልድ ወደ ትውልድ አገራቸውን እየጠበቁ የኖሩት፣ ለልዩነታቸው ዕውቅና በመስጠት የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት በመቻላቸው መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ በዝግታም ቢሆን ወደፊት እየተራመደች ነው፡፡ ጉዞው አድካሚና አሰልቺ ቢሆንም ፍጥነት በመጨመር ይቀጥላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ተሁኖ ግን ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጊዜና የአገር ሀብት ከማባከን፣ ለትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የግድ ይሆናል፡፡ አገሬን እወዳለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የሚፈለግበትን ማበርከት ይኖርበታል፡፡

  ትልልቅ ከሚባሉት አገራዊ ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱት ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ግጭት፣ ደም መፋሰስና ወድመት፣ እንዲሁም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይከተላሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ደግሞ መሠረታዊ የሚባሉት መብቶች ተከብረው፣ ዜጎች መብትና ግዴታቻውን በመረዳት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት መሆን የሚችለው ደግሞ ከላይ እስከ ታች በሕግና በሥርዓት መተዳደር ሲቻል ነው፡፡ የይስሙላ ቁጥሮች በመደርደር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳለ መደስኮር ሳይሆን፣ በተጨባጭ ሰብዓዊና ቁሳዊ ዕድገት የሚመዘገብበት ልማት ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍትሐዊ ልማት የሚረጋገጠው ግን የፖሊሲ ማስተካከያዎች ሲደረጉና የመስኩ ባለሙያዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሲጨምር ብቻ ነው፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በተጨባጭ ዕውን መሆን የሚችሉት፣ ከአደባባይ ዲስኩር ቀነስ በማድረግ የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሲደረግ ነው፡፡ ምሁራን አገርን ፈቀቅ ከማያደርጉ እንካ ሰላንቲያዎች ተላቀው ለትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ሰፋፊ ለም መሬቶች፣ ክረምት ከበጋ የማይነጥፉ የውኃ ቋቶች፣ በጣም ብዙ ማዕድናትና የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችና ፀጋዎች እያሉት ሲራብ፣ ሲጠማ፣ ሲታረዝና ምፅዋት ሲለምን ኖሯል፡፡ በተደጋጋሚ ባጋጠሙት ረሃብና ቸነፈር ምክንያት ለዕልቂትና ለስደት ተዳርጓል፡፡ ከድህነት ወለል በታች መከራ ዓይቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተፈራረቁበት ገዥዎች መፈጠሩን እስኪጠላ ድረስ ተቀጥቅጦ ተገዝቷል፡፡ አገሩን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች እየጠበቀም አርዓያነት ያለው ተግባር ፈጽሟል፡፡ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተምሳሌት ሆኗል፡፡ ይህ እጅግ የተከበረ ሕዝብ በሰላም ጊዜ የሚያሠራው ቢያገኝ ተዓምር እንደሚፈጥር ጥርጥር የለም፡፡ ነገር ግን ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላው ሽግግር በተደረገ ቁጥር፣ ትልልቅ አገራዊ አጀንዳዎች እየተዘነጉ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ትኩረት እየተደረገ መልካም አጋጣሚዎች ይባክናሉ፡፡ ለአገራዊ ትልልቅ ጉዳዮች ትኩረት ከማድረግ ይልቅ፣ ግለሰቦችና የቡድን ጉዳዮች ላይ በመንጠላጠል ፈቀቅ ማለት አልተቻለም፡፡ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮና ዘክሮ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ፣ ግለሰቦችና ቡድኖች አጀንዳ እየሆኑ ቅራኔ ይበረታል፡፡ ጥንቃቄ በሚያሻቸው የታሪክ ሰበዞች ላይ በስክነት መነጋገር ሲቻል፣ በስሜት እየነጎዱ መነታረክ ከፍቷል፡፡ ይህ ለአገርም ለሕዝብም አይጠቅምም፡፡

  በመጀመርያ ደረጃ የአገር አንድነት የሚፀናው አንዱ የሌላውን መብትና ነፃነት ሲያከብር ብቻ ነው፡፡ ከጎራ የፓርቲ ፖለቲካ በላይ የአገር ህልውና እንደሚቀድም በማሰብ፣ ልዩነቶችን በፀጋ ተቀብሎ በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሸገው ጽንፈኝነት ለአገር ሰላም ጠንቅ ነው፡፡ ጽንፈኝነትና ሴረኝነት እየተመጋገቡ ስለአገር አንድነት መነጋገር አይቻልም፡፡ በግለሰቦች ምክንያት የሚለኮሱ የቃላት ጦርነቶች ወደ ደጋፊዎች ሲሸጋገሩ የአገርን ሰላም ያደፈርሳሉ፡፡ ሰላም ሲደፈርስ ዋናው ተጎጂ ሕዝብ ነው፡፡ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ሲቻል ግን ሰላም ይሰፍናል፡፡ ሰላም ሲኖር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚስተናገዱበት የፖለቲካ ምኅዳር ይፈጠራል፡፡ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆን የሚችለው በሕግ የበላይነት ሲታመን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚኖረው ደግሞ ሁሉም ወገን ለሰላም ዘብ ሲቆም ነው፡፡ በጥቃቅን ጉዳዮች እየተናቆሩ ትልልቅ አገራዊ አጀንዳዎችን መዘንጋት ከጥፋት በስተቀር ፋይዳ የለውም፡፡ ዜጎች በየተሰማሩባቸው መስኮች አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል፣ ለአገራዊ ትልልቅ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡

  ዘወትር የተሳሳቱ ነገሮችን በመሞከር የተለየ ውጤት እንደማይገኘው ሁሉ፣ ተቋማትን ሳይገነቡ ግላዊና ቡድናዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ መንጠላጠል የሚፈይደው የለም፡፡ አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ጥራት ያለው ትምህርት፣ በገበያ ሕጎች የሚገዛ የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ ፍትሕ፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳርና በሐሳብ ነፃነት የሚያምን ማኅበረሰብ መገንባት ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ማሰብ ሲጀመር ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የሚመጥኑ ተግባራትን ለማከናወን መዘጋጀት ጠቃሚ ነው፡፡ የአገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ ማስፈን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንጣፍ ማዘጋጀት፣ ከዚያም ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚያሳትፍ ልማት ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱ ሥራ ተፈጥሮለት የዕለት ዳቦውን ማግኘት መቻሉ ለሰላም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የመንግሥት አታካችና ሀብት የሚበሉ ፕሮጀክቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ በማዘዋወር በሚገኝ ገንዘብ ለወጣቱ ሥራ መፍጠር ይገባል፡፡ ለውጥ ብሎ የተነሳው ወጣት ዳቦ ማግኘት ካልቻለ ችግሩ የከፋ ይሆናል፣ የአገር ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ያበርክቱ፡፡ ለአገር ይጠቅማልና፡፡

  ወጣቶች ከጎዳና ሠልፎች በመለስ የንቃተ ህሊና ማጎልበቻና የግንዛቤ ማስፋፊያ መድረኮች ያስፈልጉዋቸዋል፡፡ ለወጣቶችም ሆነ ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙት የአዳራሽ ውይይቶችና ክርክሮች ናቸው፡፡ በተለይ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ያላቸው የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ያስፈልጋሉ፡፡ ያልነቃና ያልተደራጀ ሕዝብ መብትና ግዴታውን በሚገባ ስለማይረዳ፣ በትልቁም በትንሹም በቀላሉ ለግጭት ይዳረጋል፡፡ ምሁራን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማትን በተመለከተ የተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ከመሠረታዊ እስከ ጥልቅ ትንተናዎች ድረስ ያለመታከት ግንዛቤ የማስጨበጥ የዜግነት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለእነዚህ ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ዋጋ ካልተሰጠ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት የበላይነቱን ይይዛል፡፡ በስሜት መነዳት ደግሞ ሰላም ያደፈርሳል፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ጉዞ ያደናቅፋል፣ በሕዝብ ፈቃድና ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ልማት እንዳይመጣ ያሰናክላል፡፡ ስለዚህ ለአገር የማይጠቅሙ ትርኪ ምርኪ ጉዳዮች ላይ ውሎ ከማደር ለአገራዊ ትልልቅ ጉዳዮች ትኩረት ይሰጥ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የንብረት ታክስ ጉዳይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተባለ

  መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን...

  የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

  የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ...

  ኢንቨስተሮች የሰብል ምርቶቻቸውን በስድስት ወራት ውስጥ ለገበያ እንዲያቀርቡ ግዴታ ተጣለባቸው

  ወደ ውጭ የሚላኩ የሰብል ምርቶች በመጋዘን ውስጥ እየተከማቹ መሆኑን...

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች