Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበእስር ላይ የሚገኙት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

በእስር ላይ የሚገኙት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ቀን:

ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው እንዲከበርላቸው ከሚሠሩበት ተቋም ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ሲያቀርቡ የነበሩትና በወንጀል ተጠርጥረው ሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዘጠኝ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ማክሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧቸው፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር፣ የሌሎች ሠራተኞችን ፊርማ በማመሳሰል ፈርመው ለአድማ በማነሳሳት፣ በቡድን በመደራጀት፣ በሥራ ላይ ጫና በመፍጠርና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች መጠርጠራቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

- Advertisement -

ተጠርጣሪዎቹ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ደመወዛቸው እንዲስተካከልላቸውና ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከበሩላቸው ከመጠየቀቅ ባለፈ፣ የተጠቀሰውን ድርጊት አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የዋስትና ጥያቄውን በማለፍ፣ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ላቀረቡት የመብት ጥያቄ ምላሽ በመነፈጋቸው ከነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አሳውቀው፣ የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ፖሊስ ‹‹ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማደናቀፍ በማሰብ የሥራ ማቆም አድማን ሲያስተባበሩና ሲመሩ ነበር›› በማለት፣ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር አውሎ በመመርመር ላይ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ተኮላ አይፎክሩ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ተጠርጣሪዎቹ የበረራ ሒደቱን ለማስተጓጎልና ከውጭ አገር የሚመጡ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሕጉን ተከትሎ የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ለጊዜው የተኩት በውጭ አገር የሚኖሩና በጡረታ ተገልለው የነበሩ ባለሙያዎች ቢሆኑም፣ ‹‹ከአዲስ አበባና ከናይሮቢ የሚነሱ አውሮፕላኖች ሲተላለፉ አስፈላጊውን ደረጃ በጠበቀ ሁኔታ እየተሠራ አይደለም፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ እየተላኩ ያሉ የበረራ ግመታዎች ሙሉ በሙሉ ስህተት ናቸው፡፡ የአውሮፕላን ዓይነትና መዳረሻቸው ሳይቀር ስህተት ይሆናሉ፤›› ሲል የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማኅበር ማስታወቁን፣ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ተፈጽመው የነበሩት የትብብር ስምምነት መመርያዎች እየተጣሱ መሆኑን፣ አደጋ ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ አዲስ አበባ የሚገኙ ሠራተኞች ኬንያ ለሚገኙ ሠራተኞች ያለ ቅድመ ግመታ እንደሚደውሉም ማሳወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በጡረታ ተገልለው የነበሩና አሁን የተጠሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአየር ክልሉ ግንዛቤ እንደሌላቸው፣ የትብብር መመርያውን እንደማያውቁ፣ ግራ እንደተጋቡና በዘገምተኝነታቸው ምክንያት የሚነገራቸውን ለመስማትና መልዕክት ለማስተላለፍ አዳጋች እንደሆነባቸው ማኅበሩ ቢገልጽም፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል)፣ ማኅበሩ ያወጣው መግለጫ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ብለዋል፡፡ የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ራሳቸው በአድማ የሚታወቁ ስለሆኑ፣ ለኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው አጋርነትን ለማሳየት ሲሉ ያወጡት መግለጫ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ለመላክ እያረቀቀ እንዳለ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የሚመለከታቸው ሁሉ መጥተው እንዲጎበኙና እንዲገመግሙ ለማድረግ በራችን ክፍት ነው፤›› ማለታቸውን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግር ውስጥ እንደሆነ ምሥል በመፍጠር የገበያ የበላይነትን ለመውሰድ የሚደረግ ሩጫ ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡  

ማኅበሩ ግን የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት እንዲተባበሩ በማለት ለዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበር ፌዴሬሽን፣ ለኬንያ አየር መንገድ ፓይለቶች ማኅበርና ለዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ግልባጭ ባደረገው መግለጫ ጥሪውን ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...