Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢኮኖሚ ፖሊሲው ላይ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ቅሬታና ወቀሳቸውን አሰምተዋል

ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያጠና ገለልተኛ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ተጠይቋል

መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የፖሊሲ ሐሳቦችን የሚያመላክቱ ጥናቶች ማካሄድ እንደጀመረ በማስታወቅ፣ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ከሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ የአገሪቱ ተወዳዳሪነት ዋናው ችግር እንደሆነ ያመላከተ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ነጋዴዎችና ባለሙያዎች ከፋይናንስ ዘርፉ እስከ ወጪ ንግዱ ባሉት መስኮች ላይ ቅሬታና ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡ 

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያ የልማት ግቦችና የመዋቅራዊ ሽግግር ፍላጎቶች የአጭርና የረዥም ጊዜ ተግዳሮቶችና ዕድሎች›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው የመጀመርያው የከፍተኛ ኃላፊዎች የኢኮኖሚ ፎረም ላይ፣ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የመነሻ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ባመላከተው ጽሑፍ፣ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን አቋም የሚተነብይና፣ ለኢኮኖሚው መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን መላምቶችን ያካተተ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ባለፉት ሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ምዕራፎች ውስጥ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል እየሰፋ የመጣ ልዩነት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሆኖ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፎች ያስመዘገበው የተወዳዳሪነት ችግር ዕድገቱን እየጎተተው መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የቻይና፣ የማሌዥያ፣ የታይላንድ፣ የደቡብ ኮሪያና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ አውስተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቱ እየነቀሰ ሲመጣ የቻይና፣ የማሌዥያና የደቡብ ኮሪያ ግን እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት በመጪዎቹ ስምንት ዓመታት ውስጥ ማስተካከያ ይደረግባቸዋል ከተባሉት ውስጥ የግብርናው፣ የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፎች ብሎም በፊስካልና በገንዘብ ፖሊሲዎች ላይ ለውጦች የሚደረጉበትን መንገድ የሚያመላክት የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴል አቅርበዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴሉ ድርቅን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችና ወሳኝ ችግሮች እንደማይከሰቱ ታሳቢ በማድረግ ባስቀመጣቸው ሁለት የትንበያ መነሻዎች መሠረት፣ አሁን የሚታዩበትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታል ተብሏል፡፡

አንደኛው የይሆናል መነሻ በአሁኑ ወቅት እየተወሰዱ ያሉ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ሊያመጡ የሚችሏቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦች የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው የይሆናል ወይም መላምታዊ መነሻ ደግሞ የግሉና የመንግሥትን የአጋርነት ማዕቀፍ ያደረገ የፖሊሲ አካሄድ የሚፈጥረውን ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ አቅም የሚመለከት ነው፡፡

እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር) እነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ መነሻዎች የአገሪቱን የብድር ጫና ከማቃለል ባሻገር ምርት እንዲጨምርና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም ወሳኝ ሚና እንዲኖረው የሚያስችሉ፣ ትርፍ ምርት እንዲመረትና ወደ ውጭ እንዲላክ የሚረዳ አቅም በመፍጠር የአገሪቱን የክፍያ ሚዛን ጉድለት በተለይም በገቢና በወጪ ንግዱ መካከል የሚታየውን ከፍተኛ ልዩነት የሚፈታ አቅም በመፍጠር፣ አገሪቱ በውጭ አበዳሪዎች ዘንድ ያለባትን ዕዳ ከመቀነስ አልፎ ተርፎ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖራት እንደሚያስችሉ አስረድተዋል፡፡

መድረኩን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በነፃነት ይጠቅማል ያሉትን ኢኮኖሚያዊ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ በፖለቲካው መስክ የታዩ ለውጦችን በኢኮኖሚውም እንዲታዩ ማድረግ ካልተቻለ የሚያስከትሉት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የኢኮኖሚውን ችግሮች በመፍታት አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ማስገባት የሚያስችሉ የፖሊሲ ሐሳቦች እንዲቀርቡም አሳስበዋል፡፡ አዲሱ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር አቶ እዮብ ተካልኝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ፣ ተቋማቸው የ12 ዓመታት የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ የሚመለከት ግዙፍ ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

እንዲህ ያሉ መነሻዎችን ያካታተው የመንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ ሐሳቦች አዳዲስ የፖሊሲ ሐሳቦች ሲቀርቡበት አልታየም፡፡ ይልቁንም የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበሩት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ቅሬታዎችና ወቀሳዎችን ሲያስተናግዱ ታይቷል፡፡ የፍሊንትስቶን ሆምስ መሥራችና ባለቤት አቶ ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር)፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት፣ ‹‹ወንዝ የሚያሻግር እንጂ እንደ ወንጭፍ የሚታይ መፍትሔ አያመጣም፤›› ብለዋል፡፡ ይልቁንም መንግሥት ለብድርና ለፋይናንስ ዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ሲገልጹም፣ ‹‹አገር እንደ ነጋዴ ማሰብ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ እንዲያውም በግሉና በመንግሥት አጋርነት ለሚመጣው ገንዘብ ወደፊት በታክስና በሕዝቡ ገቢ ላይ ጫና እንዳይመጣ ለማድረግ መፍትሔው፣ አገሪቱ ባላት አቅም መጠን መበደሯን እንድትገፋበት ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡   

አቶ ፀደቀ የአገሪቱ የባንክና የመድን ኩባንያዎች ኃላፊዎች ስለሚመሩት ኢንዱስትሪ ሐሳብና ትችት መሰንዘር የማይችሉበት አካሄድ በመኖሩ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚታሰበው ለውጥ ያለ ተቋማቱ ኃላፊዎች ተሳትፎ እንዴት ይታሰባል በማለት፣ ቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበሩትን ዮሐንስን (ዶ/ር) ወርፈዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቅጡ ሳይረዱ የፖሊሲ ሐሳብ ማቅረብ አይገባም በማለት ዮሐንስን (ዶ/ር) የወረፉት ሲሳይ ረጋሳ (ዶ/ር) የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ በጥቅምት ወር የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ የዋጋ ግሽበት አያስከትልም ማለታቸውን በማስታወስ ነው፡፡ ‹‹አሁን የሚያቀርቡትን የፖሊሲ ሐሳብም እጠራጠራለሁ፤›› ብለዋቸዋል፡፡ አያይዘውም መንግሥት የካፒታል ገበያ እንዲመሠረትም ጠይቀዋል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ በአገሪቱ ስለሚታየው የሎጂስቲክስ ዘርፍ የተወዳዳሪነት ችግር፣ ስለግሉ ዘርፍ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው አለመግባት፣ በአገሪቱ ስለሚታየው የንግድና የሌሎች ምርት ልውውጥ ወጪዎች ከፍተኛነትና ሌሎችም ችግሮች በማንሳት፣ እነዚህን ችግሮች ለማጥናት ገለልተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ግብረ ኃይል መቋቋም እንዳለበት በመፍትሔነት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

እንዲህ ያሉትን ወቀሳዎች ያስተናገደው መድረክ፣ የአገሪቱን የሎጂስቲክስ ሥርዓት የሚታዩበትን የወጪና የጊዜ ብክነት እንዲመለከትም ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ኢትዮጵያ በወደብ አጠቃቀም ረገድ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን በምን አግባብ ልትጠቀም እንዳሰበች፣ ያላት ተሰሚነትና እንደ ወደብ አልባ አገር ያላት የተጠቃሚነት የመብት ጥያቄ እስከ ምን ድረስ ተቀባይነት እንዳለው የጠየቁት፣ የሎጂስቲክስ ዘርፍና የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ከበደ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ማምረት ያልቻሉበት ጉዳይ እንዲታይ ከመጠየቅ በተጨማሪ፣ ፓርኮቹ ለውጭ ባለሀብቶች በካሬ ሜትር አንድ ዶላር በሆነ ሒሳብ የመከራየታቸው ጉዳይ ሁሉ ሊፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች በፍራንኮ ቫሉታ ጭምር የሚያስገቡትን የጥሬ ዕቃ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እየሸጡ እንደሚገኙ በማመላከት፣ የውጭ ባለሀብቶች የሚሰጣቸውን ማበረታቻ አላግባብ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡ የታክስ ዕፎይታ፣ የባንክ ብድርና ሌላውም የተሰጣቸው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር  እንዲያመጡ ተብሎ ቢሆንም፣ ‹‹የመጣው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር የታለ?›› በማለት አቶ መላኩ ጠይቀዋል፡፡ የግብርና ፖሊሲ መሻሻል አለበት ሲሉም የቁም እንስሳት ንግድና የኤክስፖርት ቄራዎችን ችግር አንስተዋል፡፡

የግዥ ሥርዓቱ የአገር ውስጥ አምራቾችና አቅራቢዎችን የሚያበረታቱ ሕጎችን ቢያወጣም፣ በተግባር ግን ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከውጭ መግዛት ስለሚመርጥ ሕጎች እንደማይከበሩ የጠቀሱት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ አገሪቱ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ አባል ለመሆን የጀመረችው የተጓተተ የድርድር ሒደትም በማሻሻው ሊታይ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሮችም መሻሻል አለባቸው ባሏቸው መስኮች ላይ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ቀደምም በሌላ መድረክ ያነሷቸው ሐሳቦች ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እሴት ወደ መጨመሩ መሄድ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የግብርና ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ የተመሠረተው የወጪ ንግድ ኢኮኖሚ ሊለወጥ፣ የግብርናው ዘርፍም የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የቴክሎጂ ዘርፍ ትኩረት ተነፍጎታል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢኮሜርስ) መተግበር ቢችል ለአገልግሎት ኢኮኖሚው ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አስረድተዋል፡፡

እንደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሁሉ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ገመዶ ዳሌም (ዶ/ር) የአገሪቱ ሀብቶች በተለይም እንደ ቁም እንስሳት ያሉት ወደ ውጭ የሚላኩበት አግባብ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፃረሩ፣ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነቷን የሚያሳጡ አካሄዶችን እንደሚያሳዩ፣ ለቡናና ሌሎች ግብርና ምርቶች የተሰጠው ትኩረት እንደ ውኃ ላሉት መስኮች ትኩረት ቢሰጠው፣ አገሪቱ ውኃ ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ አሁን ከምታገኘው የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኙላት ሞግተዋል፡፡

ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር የምርት እጥረት መሆኑን ጠቁመው፣ በሰሊጥ አምራችነታቸው የሚታወቁ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በሔክታር እስከ ስምንት ኩንታል ያስገኙ የነበረበት የምርት መጠን አሁን ወደ ሦስት ኩንታል ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስለእሴት መጨመር ከመነጋገራችን በፊት ምርቱ ይታይ፤›› ያሉት አቶ በላይነህ፣ ምርቱ ሲጨምር የሚላከው የግብርና ምርትም ስለሚጨምር የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሻሻል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች