ከ120 በላይ ታዳጊ ወጣቶች በክለብ እንዲታቀፉ ተመልምለዋል
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከነሐሴ 13 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ሲካሄድ የሰነበተው ስድስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊዎች የምዘና ውድድር በአስተናጋጁ ክልል አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የትግራይ ክልል በውድድሩ እንደሚሳተፍ ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ የሶማሌ ክልል ደግሞ በፀጥታ ምክንያት ከሻምፒዮናው ውጪ መሆናቸው መረጋገጡ ተነግሯል፡፡
በኦሊምፒክ ስፖርቶች ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚሁ የአገር አቀፍ የምዘና ውድድር በወንዶች 1,480፣ በሴቶች 968 በድምሩ 2,443 ታዳጊ ወጣቶች ሲሳተፉ፣ መስማት በተሳናቸው በወንዶች 243፣ በሴቶች ደግሞ 150 በድምሩ 393፣ በአጠቃላይ 1,723 አትሌቶች በተለያዩ ስፖርቶች መካፈላቸው ውድድሩን በበላይነት የመራው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ረዳት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንየው አሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ አገር አቀፉ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር በስፖርታዊ ጨዋነት የታቀደለትን ዓላማ ግብ አሳክቶ ተጠናቋል፡፡ የምዘና ውድድሩ ዋና ዓላማ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ዓመቱን ሙሉ ሲከናወን የቆየው የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ያሉባቸውን ደካማና ጠንካራ ጎኖች በውድድር ለመለካትና ለመገምገም ያለመ መሆኑ ረዳት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም ለሚቀጥለው የውድድር ዓመት በሰባት ስፖርቶች ከሦስቱ ከተሞች ከአዳማ 74፣ ከአሰላ 40 እና ከቢሸፍቱ ስምንት ተተኪ ስፖርተኞች ለክለቦችና ለማሠልጠኛ ማዕከላት እንዲከፋፈሉ የተመለመሉ ስለመሆኑ ጭምር አቶ እንየው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በውድድሩ ያልተሳተፉት ሁለቱ ክልሎችን አስመልክቶ ረዳት ኃላፊው፣ የትግራይ ክልል ከዚህ ከምዘና ውድድሩ አስቀድሞ ስለውድድሩ ደንብ መመርያ አዳማ ላይ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተገኝቶ የሚጨመሩና የሚቀነሱ ሐሳቦች ላይ ተችቷል፡፡ ክልሉን የሚወክሉ ታዳጊ ወጣቶች ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ መሆኑን ጭምር አስታውቋል፡፡ ይሁንና እስካሁን በውድድሩ ሳይሳተፍ የቀረበትን ምክንያት ጭምር እንዳላሳወቀ ነው አቶ እንየው ለሪፖርተር የገለጹት፡፡ ሶማሌን በተመለከተ ግን በፀጥታ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ በተለይ የትግራይ ክልልን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
በአዳማ፣ በአሰላና በቢሸፍቱ ከተሞች ከሁለት ሳምንት በላይ ቆይታውን ባደረገው ዓመታዊ የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር፣ አስተናጋጁ የኦሮሚያ ክልል በ56 የወርቅ፣ በ49 የብርና በ44 የነሐስ በድምሩ በ149 ሜዳሊያዎች አንደኛ ሲሆን፣ አማራ በ54 የወርቅ፣ በ41 የብርና በ45 የነሐስ በድምሩ በ140 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ፣ ደቡብ በ28 የወርቅ፣ በ35 የብርና በ32 የነሐስ በድምሩ በ95 ሜዳሊያ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ አዲስ አበባ በ74፣ ድሬዳዋ በ47፣ ሐረሪ በ12 እና የአፋር ክልሎች እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡
በፓራሊምፒክ አስተናጋጁ የኦሮሚያ ክልል በ42 የወርቅ፣ በ17 የብርና በ30 የነሐስ በድምሩ በ89 ሜዳሊያ አንደኛ፣ አማራ በ20 የወርቅ፣ በ36 የብርና በ18 የነሐስ በድምሩ በ74 ሜዳሊያ ሁለተኛ፣ አዲስ አበባ በ10 የወርቅ፣ በ13 የብርና በ11 የነሐስ በድምሩ በ34 ሜዳሊያ ሦስተኛ ሲያጠናቅቁ፣ ደቡብ በ25፣ ጋምቤላ በሁለት የብር፣ አፋር በሁለት የነሐስ ሜዳሊያ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡