[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዳያስፖራ ጋር እያወሩ ነው]
- እንኳን አገርህ በሰላም ለመግባት አበቃህ፡፡
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አገሪቱን እንዴት አገኘሃት?
- በእውነት ክቡር ሚኒስትር አዲስ አበባ የማላውቃት ከተማ ነው የሆነችብኝ፡፡
- ለመሆኑ ስንት ጊዜ ሆነህ ከአገር ከወጣህ?
- ሰላሳ ዓመት እየተጠጋኝ ነው፡፡
- ታዲያ ዕድገቱን እንዴት አየኸው?
- ከተማዋ እኮ በፎቅ ጫካ ተውጣለች፡፡
- ስለዚህ ዕድገት መኖሩን አረጋገጥክ ማለት ነው?
- አይ ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እኮ ዕድገት የለም ብዬ ሳይሆን ስታገል የነበርኩት ዴሞክራሲያዊ መብት የለም ብዬ ነበር፡፡
- ይኸው አገርህ እንድትገባ ያደረገህ ዴሞክራሲያዊ መብትህ አይደል እንዴ?
- እሱን እንኳን ተውት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን ሲባል?
- በፊት ይኼን ሥርዓት በመቃወሜ የደረሰብኝን መከራ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
- ምን ተደረግኩ ልትል ነው?
- እኔ ላይ በቀጥታ ባይደርስም፣ እዚህ የነበሩ ቤተሰቦቼ ላይ ምን ያህል መከራ ሲደርስባቸው እንደነበር መቼም አይዘነጉትም፡፡
- አንተ እኛ ውጭ በወጣን ቁጥር ስለምታደርስብን ግፍ ይኼ ሲያንስህ ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እንደ አንተ ዓይነቱን ሰው ስናስብ እኮ ነበር የውጭ ጉዞ የሚያንገፈግፈን፡፡
- ለምን ያስመስላሉ ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ማስመሰል ነው?
- እንደዚህ ቢያንገፈግፍዎት በየወሩ ውጭ ባልወጡ ነበር፡፡
- ውጭ የምወጣውማ ጥቅማ ጥቅሜን አስቤ እንጂ ለሌላ ለምን መስሎህ ነው?
- እኛም እኮ እንደዚያ አምርረን የምንቃወማችሁ ለሕዝቡ ሳይሆን ለጥቅማችሁ እንደቆማችሁ ስለምናውቅ ነበር፡፡
- አየህ መርሳት የሌለብህ ነገር እኛም እኮ የሕዝቡ አካል ነን፡፡
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ ስንጠቀም ሕዝቡ እንደተጠቀመ ይቆጠራል፡፡
- በእውነት ክቡር ሚኒስትር ዘመኑ የምሕረት በመሆኑ እንጂ ለእናንተ እኮ የሚገባችሁ ጓንታናሞ ነበር፡፡
- እኛ የሠራነው ልማት ፈጽሞ አይታይህም ማለት ነው?
- ነገርኩዎት እኮ ከልማታችሁ ጥፋታችሁ ነው የሚብሰው፡፡
- ለመሆኑ እዚህ ምን ልታደርግ ነው የመጣኸው?
- አገሬ አይደል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- አይ ያው እዚያ ቢያንስ እኛን እየተሳደብክ ገንዘብ መሰብሰብ ትችል ነበር ብዬ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ለዓመታት የታገልኩት ለገንዘብ ብዬ ሳይሆን ለሕዝቤ ተቆርቁሬ ነው፡፡
- ስለዚህ ለሕዝብ ከተቆረቆርክ እዚህ ፓርቲ መሥርተህ ሕዝብን ትታገላለህ ማለት ነው?
- የምን ፓርቲ ክቡር ሚኒስትር?
- ያው ውጭም ፖለቲከኛ ስለነበርክ እዚህም በዚያው ትቀጥላለህ ብዬ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ወደ አገር ቤት የተመለስኩት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብዬ ነው፡፡
- ገብቶኛል ስለዚህ አገር ውስጥ ስትገባ ፖለቲከኛ ሆነህ ነው የምትቀጥለው ወይ እያልኩህ እኮ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር መቼም ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም በውጭ አገር ያለ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ አምባሳደር ነው ሲሉ ሰምተዋል፡፡
- ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
- የአምባሳደርነትን ሥራ ዕድሜ ልኬን ስሠራው የቆየሁት ሥራ ነው፡፡
- አሁን ግራ እያጋባኸኝ ነው፡፡
- ከዚህ በኋላ መንግሥትን እየተቃወምኩ መኖር አልፈልግም፡፡
- ወዴት? ወዴት?
- ዘመኑ የመደመር በመሆኑ እኔም ተደምሬያለሁ፡፡
- የምን ጠጋ ጠጋ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት አንድ ነገር እንዲያደርገኝ ነው የምፈልገው?
- ምን?
- አምባሳደር!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋ ይደውላሉ]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ዝም ስልህ ዝም ትላለህ እንዴ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- በፊት በዚህ ሰሞን እየደወልክ ታጨናንቀኝ አልነበር እንዴ?
- ምን ብዬ ክቡር ሚኒስትር?
- እንኳን አደረሰህ ለማለት ማን ቀደመኝ እያልክ ትፎካከር አልነበር እንዴ?
- እንኳን አደረሰዎት ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያኔ ቤቴ የከብት ማደሪያና ቄራ እስኪመስል ድረስ አልነበረ እንዴት የምታጨናንቀኝ?
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- በሬው አይቀርህ በጉ፣ ፍየሉ ብትል ዶሮውን አግተልትለህ አልነበር እንዴ የምታመጣልኝ?
- መቼም በዚህኛው ዓመት በዓል ያን አይጠብቁም?
- ለምን አልጠብቅም?
- ሥርዓቱ እኮ ተቀይሯል፡፡
- የምን ሥርዓት ነው የምታወራው?
- አሁን እኮ የፍትሐዊነትና የእኩልነት ዘመን ነው፡፡
- ቆይ! ቆይ! ቆይ! በፊት እኮ ወዳጅ ስለነበርን የምታመጣልኝ መስሎኝ?
- እንደዚያ እንዳልሆነ መቼም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡
- ታዲያ ለምን ነበር?
- እኔ በየጊዜው ለእርስዎ ስጦታውን አዥጎደጉደዋለሁ፣ እርስዎ ደግሞ በምላሹ ለእኔ ሕንፃ አይሉ መሬት፣ ፋብሪካ አይሉ ሌላውን ያመቻቹልኛል፡፡
- እ. . .
- ክቡር ሚኒስትር ግንኙነታችን እኮ እከክልኝ ልከክልህ በሚለው መርህ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡
- አሁን የመርህ ለውጥ አለ እያልከኝ ነው?
- አሁንማ የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጊዜ ነው፡፡
- እነዚህን ቃላት የማልሰማበት የት ልሂድ?
- ክቡር ሚኒስትር ፍቅርና መደመር የሚሉት እኔ ይስማሙኛል፣ ግን ይህች የይቅርታ የምትለው ብዙም አትጥመኝም፡፡
- እንዴት?
- እርስዎ አሁን ያጠፉት ጥፋት በይቅርታ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ስለራሴ ባወራ በዓል በመጣ ቁጥር እንዲሁ ስባንን ነበር የማሳልፈው፡፡
- ምን ሆነህ?
- ለእርስዎ ስጦታ የማወጣውን ወጪ እያሰብኩ ነዋ፡፡
- ይኼን ያህል?
- ክቡር ሚኒስትር ሥርዓቱ በመቀየሩ ነው እኮ አሁንም ከዚህ ጭንቀት የተገላገልኩት፡፡
- ስለዚህ ስጦታ አላመጣም እያልከኝ ነው?
- ትንሽ ግን አያፍሩም ክቡር ሚኒስትር?
- በምኑ ነው የማፍረው?
- ይኸው መሪያችን በየሆስፒታሉ እየሄዱ ደም በሚሰጡበትና ቤት ለፈረሰባቸው ቤት በሚገነቡበት ዘመን፣ እርስዎ አሁንም ሊያስጨንቁን ሲሞክሩ እንዴት አያፍሩም?
- ሰውዬ ተረጋጋ፡፡
- ለዚያ ነው ይቅርታ ምናምን በሚሉት አላምንም የምለው፡፡
- ምን እንዳደርግልህ ፈልገህ ነው?
- እርስዎን ይቅርታ እንድልዎት አንድ ነገር ማድረግ አለብዎት፡፡
- ምን?
- ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት የበዓል ወጪዬን ሊሸፍኑ ይገባዎታል፡፡
- ማን?
- እርስዎ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ምነው ተከዙ ክቡር ሚኒስትር?
- ተወኝ እባክህ፡፡
- ምን ተፈጠረ? አዲስ ዓመት እየመጣ መነቃቃት ነው እንጂ የምን መቆዘም ነው?
- ግራ ገብቶኝ ነው ምን ላድርግ?
- ክቡር ሚኒስትር የመደመር ዘመን አይደል እንዴ?
- ጭራሽ የባሰ ደም ግፊቴን አታብስብኝ?
- ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ እኔ ሕይወት ራሱ እየመረረኝ ነው፡፡
- ኧረ እንደዚህ አይባልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኸው የወጣትነት ዘመናችንን መስዋዕት አድርገን የተረፈን የሕዝብ ጥላቻ ነው፡፡
- ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በየሄድንበት እኮ መሳለቂያ እየሆንን መዋረድ ነው የተረፈን፡፡
- እንዲህማ መሆን የለበትም፡፡
- ሻይና ቡና የምጠጣበት ቦታ እንኳን አጣሁ፡፡
- ከጎረቤት ጋር አይጠጡም እንዴ?
- ይህ የሚመጣ ሳይመስለኝ በልማት ሰበብ አስነስቼያቸው መቼ ጎረቤት አለኝ ብለህ ነው?
- እሱስ እውነት ብለዋል፡፡
- ከተማ ውስጥ ደግሞ ያኔ ቤት ተዘግቶልን እንዳልተዝናናን አሁን ግልምጫውን አልቻኩትም፡፡
- እሱማ እኔም ሰምቻለሁ፡፡
- በዚያ ላይ ሊያጠቁኝ ይችላሉ ብዬ ስለምሠጋ የቁም እስረኛ ሆኛለሁ፡፡
- ለነገሩ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- አገሪቱ ሙሉ እስር ቤት አልነበረች እንዴ በዚህ ብቻ ካለፈልዎት ጥሩ ነው፡፡
- ስማ ባለቤቴን ከዕድር አባረሯት፡፡
- ዕድር ደግሞ ምን ያደርግላችኋል ብለው ነው?
- ለማንኛውም ቢሆን ማኅበራዊ ሕይወት ያስፈልጋል፡፡
- ለነገሩ ዕድር የሚያስፈልግዎት ዋናው ጊዜ አሁን ሊሆን ይችላል፡፡
- እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለእኔ ምን ጊዜም ቢሆን ባለውለታዬ ነዎት፡፡
- ምን ያደርጋል ሕዝቡ ጠላኝ፡፡
- እርስዎ ባይኖሩ ኖሮ እንደ እኔ ዓይነቱ ያልተማረና ብቃት የሌለው ግለሰብ ሚሊየነር መሆን ይችል ነበር?
- እሱማ እንደ አንተ ዓይነቱን መኃይም ሚሊየነር ያደረገ ሥርዓት መገንባታችን የሚያሸልመን እንጂ የሚያስወቅሰን መሆን አልነበረበትም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ መቼም ቢሆን ውለታዎትን አልረሳም፡፡
- አንተ ብቻህን ምን ታደርግልኛለህ ብለህ ነው?
- እኔማ ለዋሉልኝ ውለታ ማሸለም አለብኝ ብዬ ቆርጬ ተነስቻለሁ፡፡
- ምንድነው የምታሸልመኝ?
- እንዲያው ካጣሁ ገዝቼም ቢሆን አሸልምዎታለሁ፡፡
- ምን?
- የክቡር ዶክትሬት!
[የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ከውጭ ይደውልላቸዋል]
- ክቡር ሚኒስትር ደስ የሚል ዜና ልነግርዎት ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ወደ አገሬ ልገባ ነው፡፡
- ምን አልክ?
- ወደ አገሬ ልመለስ ነው፡፡
- ይኼማ ፈጽሞ የማልቀበለው ነገር ነው፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ ውጭ ያለኝን ቤት አይሉ የባንክ አካውንት የምታንቀሳቅስልኝ ሰው እንዴት ነው አገር ቤት እመለሳለሁ የምትለኝ?
- ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ በዚህ ሥራ አልቀጥልም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ዘመኑ መቼም የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር መሆኑን ያውቃሉ?
- ለአንተ የሚጠቅምህ እነሱ ሳይሆኑ የእኔ ሀብት መሆኑን ረሳኸው?
- ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ በቃኝ፡፡
- ውጭ አገር ሃያ ምናምን ዓመት አንደላቅቄ ካኖርኩህ በኋላ እንደዚህ ስትል አታፍርም?
- ከዚህ በኋላ በቃኝ አልኩዎት እኮ?
- ስማ ያ ገንዘብ በአንተ ስም መሆኑን ታውቃለህ አይደል?
- ክቡር ሚኒስትር ገንዘቡ የእርስዎ እንዳልሆነ አያውቁም እንዴ?
- ምን ማለት ነው? ለዘመናት የለፋሁበት ሀብት እኮ ነው?
- ለዘመናት የዘረፍኩት ማለትዎ ነው?
- ሰውዬ አብደሃል እንዴ?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ በአፋጣኝ መጥቼ ገንዘቡን ወደ እኔ ታዘዋውረዋለህ፡፡
- እኔ ቀድሜ አዘዋውሬዋለሁ፡፡
- ወዴት?
- ወደ ትረስት ፈንዱ!