ኢትዮጵያ ባለዝናና የዓለም ሕዝብ በብዙ የታሪክ ገድሎቿ የሚያውቃት አገር ነች፡፡ ያኔ ገናና በነበረችበት ዘመን እስከ ዓረብ ባህረ-ሰላጤ ድረስ በመዝለቅ አገሮቹን ከማስገበር ባሻገር፣ የተቀዳጀቻቸው የጦር የበላይነትና ኃያልነት በዓለም ፊት እስከ ዛሬ ድረስ አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትሄድና አፏን ሞልታ እንድትናገር አስችሏታል፡፡
ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲገልጹ፣ ‹‹በሦስት ተዛማጅ አዕማዶች ሥር ይጠቃለላል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ባዕድ ሕዝብ (ጠላት) በአገሪቱ ላይ ጣልቃ በሚገባበት ወቅት እንደ እሾህ ተዋግቶ፣ እንደ ንብ ተናድፎ የሚያባርር ሕዝብ ባለቤት መሆኗ ነው፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን አገላለጽ ኢትዮጵያ ለጠላት እጅ ሰጥታ የማታውቅ እጅግ አኩሪ ገድልና ዝናን ተጎናጽፋ የኖረች አገር ነች፡፡ ከግብፅ የወረራ ፍላጎት እስከ ዚያድ ባሬ፣ ከእንግሊዝ እስከ ጣሊያን የወረራና የቅኝ ግዛት ፍላጎቶች እጅ ያልሰጠችና የነፃነት ተምሳሌት ተብላ በታሪክ የተመዘገበ ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡ ለዚህም በብዙ የአፍሪካ አገሮች የመማሪያ መጻሕፍት ውስጥ ሳይቀር ስሟ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
የታሪክ ድርሳናቶቿ እንደሚያመለክቱት 3,000 ዓመታትን ሻማ ለኩሳ ልደቷን ያከበረች አገር ከብሉልኝ ጠጡልኝ አኩሪ ባህሏ ባሻገር፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከሰቱ ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ቀድማ በመድረስ የሚሊዮኖችን እንባ አብሳለች፡፡
ከዚህ በተቃራኒ አገሪቱን ጥላሸት በመቀባትና የነበራትን ስመ ገናናነት ወደኋላ ጎትቶ ያስቀረ ታሪክም ባለቤት መሆኗ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ የታሪክ አጋጣሚዎች ብንነሳ እንኳ በደርግ መንግሥት ወቅት የነበረውን ሁኔታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የፊውዳሉ ሥርዓት ተገርስሶ በትረ ሥልጣኑን የደርግ መንግሥት ሲቆናጠጥ ያመጣል ተብሎ ይታሰብ የነበረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ ቀረ፡፡
ደርግ የፖለቲካ መዘወሩ ላይ ሲወጣ ጀምሮ የአስተዳደር ሥርዓቱን አምባገነን በማድረግ የሕዝቡን ብሶትና ምሬት የባሰ አደረገው፡፡ የዚህ ብሶትና ምሬት ሰለባ የሆኑ ወጣቶች ይጠብቁት የነበረው ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደማይሳካ ሲያውቁ ‹‹ኢሕአፓን›› አቋቁመው መታገል ጀመሩ፡፡
ኢሕአፓ ሲመሠረት ሕዝባዊ መሠረት የነበረውና በተማረው ማኅበረሰብ ይመራ የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ግን እንደ ሶቭየት ኅብረት ከመፈረካከስ የታደገው አልነበረም፡፡ በሌላ የትግል ቅኝትና ዓላማ ተቋቁሞ የነበረው ሕወሓት የአምባገነኑን ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡
ሕወሓት ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ኢሕአዴግ የሚባለውን ግንባር መሥርቶ እልህ አስጨራሽና መራራ ትግል ለዓመታት ካደረገ በኋላ የአምባገነኑን ሥርዓት ገርስሶ መጣል ቻለ፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላም ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም አገሪቱን ለመምራት የሚያስችለውን ፖለቲካዊ አጀንዳ መቅረፅ ጀመረ፡፡
በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ግንባር ቀደም ከነበሩ ድርጅቶች አንዱ ኢሕአዴግ ነው፡፡ የአራት ፖለቲካ ፖርቲዎች ድምር የሆነው ኢሕአዴግ እስከ ዛሬ ድረስ አውራ የመንግሥት የፖለቲካ ፖርቲ ሆኖ እነሆ ለ25 ዓመታት ዘልቋል፡፡
ኢሕአዴግ አገር መምራት ከጀመረ በኋላ በአገሪቱ የታዩ ዕምርታዎች ብዙ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል የፌዴራሊዝም ሥርዓት መፈጠርና መጐልበት አንዱ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የብሔርና ብሔረሰቦችን እኩልነት በማረጋገጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ጥረት ሲያደርግ ይታያል፡፡
ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያገኘበትና ዋናው ተደርጎ የሚወሰደው ጉዳይ፣ አገሪቱን ከመበታተን አውጥቶ ፀጥታ የሰፈነባት ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ ግዙፍ የመከላከያ ኃይል በመገንባት ለአገሪቱ ብሎም ለአፍሪካ ዘብ መቆም የሚያስችል ቁመና ያለው ወታደራዊ ኃይል ገንብታለች ሲሉ የመስኩ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ግሎባል ፋየርፓወር (Global Firepower)ን ጠቅሶ አፍሪካን መጋዚን እንደዘገበው፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በወታደራዊ ኃይሏ ከግብፅና ከአልጄሪያ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2015 ድረስ በኬኒያ ጋሪሳና ዌስትጌት የገበያ ማዕከል እንደደረሰው ዓይነት የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ ሳትሆን ቆይታለች (በ2016 ይህ እውነታ የተቀየረ ቢመስልም) ሲሉ፣ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ኢሕአዴግ ከፀጥታው ባሻገር በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይም ይበል የሚያሰኝ ዕርምጃዎችን ተራምዷል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱና ሌላኛው ጉዳይ (ብዙዎችን የሚያስማማው) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡ ምንም እንኳ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሐሳብ የተጀመረው ‹‹በፊውዳሉ ሥርዓት ነው›› የሚሉ መከራከሪያዎች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ቢሆንም፣ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት የተቻለው ግን በዘመነ ኢሕአዴግ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ይህ የህዳሴ ግድብ ደግሞ የአገሪቱን ዜጐች ከጫፍ እስከ ጫፍ በማነቃነቅ በአንድነት ያስተሳሰረ ነው፡፡ ይህ የህዳሴ ግድብ የዜጐች የደም ሥር ሆኖ የታየው ከኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ካለው ፖለቲካዊ ፋይዳም ጭምር እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት ጥሩ ውጤት ተደርጐ የሚወሰደው የመንገድ መሠረተ ልማት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በ25 ዓመታት ውስጥ ኢሕአዴግ በመንገድ ዘርፍ ይበል የሚያሰኙ ዕምርታዎችን አስመዝግቧል፡፡ በገጠር ቀበሌን ከቀበሌ ከማገናኘት ጀምሮ በከተማ የባቡር ሐዲድ እስከ መዘርጋት የዘለቀ ተግባር አከናውኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሕአዴግ በ25 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ውስጥ ያልሄደባቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ከእነዚህ መካከል የወደብ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ አገራችን ወደብ አልባ በመሆኗ ለወጪና ገቢ ንግዱ የምትከፍለው የወደብ ኪራይ ታክስ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እጅግ እየጐዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ‹‹አገሪቱ 25 ዓመታት ሙሉ በደረቅ ወደብና በደረቅ እንጀራ የኖረች የምሥራቅ አፍሪካዋ አገር›› ሲሉ ብዙዎቹ ሲሳለቁ መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ‹‹አገራችን ከኤርትራ ጋር ያላትን የአይጥና የድመት ጥላቻ ወደኋላ በመተው እንደቀደመው ሁሉ በአሰብ ወደብ ዕቃዎቻችንን በነፃ ብናስገባና ብናስወጣ የተሻለ ነው፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ሌላው ኢሕአዴግ የቤት ሥራውን ሳይሠራ እንደሠራ አድርጎ በ25ኛ ዓመት የልደት በዓሉ ዋዜማ በየሚዲያው የሚለፍፈው ጉዳይ ነው፡፡ እውነታው የአገሪቱን ዜጎች ከድህነት ማውጣት አለመቻሉ ነው፡፡ መንግሥት በ11 ፐርሰንት እንዳደግን በሚዲያው በተደጋጋሚ ሲናገር ቢደመጥም እውነታው ግን የተገላቢጦሽ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዜጎች አስከፊ በሚባል ደረጃ ወደ ውጭ አገር በመሰደድ የባህር ሰለባ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የጎዳና ተዳዳሪና ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ዜጋ ቁጥር እጅግ እየጨመረ መምጣቱን ጥናት ሳያደርጉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነትም በ11 ፐርሰንት ስለማደጋችን ጥርጣሬ የሚከት ጉዳይ ነው፡፡
ከድህነት ባሻገር ሥር የሰደደው ሙስናና ብልሹ አሠራር አገሪቱን ጥላሸት እየቀባ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ የ25ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር ከሠራቸው ሥራዎች ይልቅ ያልሠራቸው ሥራዎች ሚዛን ስለሚደፉ፣ እንደ ጃፓን አንገቱን ደፍቶ በመሥራት አገሪቱን ከድህነትና ኋላቀርነት ማላቀቅ አለበት፡፡
በአፍሪካ በወታደራዊ አቅማችን የገነባነውን ኃይል በኢኮኖሚውም መድገም አለብን፡፡ በመጨረሻም የሰር ሔነሪ ዎተንን ግጥም በመጋበዝ ልሰናበት፡፡
ምነኛ ደስ ይለው —
ዕድገቱ ያረቀው
ትምህርት ያነፀው ሰው
ህሊናውን ሸጦ የማያደገድግ
እውነተኛነቱን መከታው እሚያደርግ
ምን ቅንጣት ብታክል በሀቅ የሚመካ
በሳልነቱንም በዚሁ እሚያስለካ
ምንኛ ደስ ይለው —
እንደዚህ ያለ ሰው —
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡