Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛስ ማን ነን? ጥያቄያችንስ የማን ነው?

ሰላም! ሰላም! እነሆ ብሶት ወልዶን ብሶት እያስረጀ ካስተዛዘበን 25 ዓመታት ደፈንን። ይገርማል 25 ዓመታትም እንደ 25 ብር ካርድና 25 ሳንቲም ቶሎ ያልቃሉ ለካ?’ እያሉ ጎረቤቶቼ ሲጨቃጨቁ ሰነበቱ። እኔማ ካሁን አሁን የኑሮ ውድነት ማለት በለመደብን አፋችን፣ የጊዜ ውድነት ያመጣብን የዕድሜ ዋጋ ማጣት ውጤት ነው ብለው ይስማማሉ እያልኩ አዳምጥ ነበር። ከማዳመጥ ምን አጣን? እንኳን ከማዳመጥ ደም ከመፋሰስ የጎደለብን ያለ እንመስላለን እንዴ? እውነቴን እኮ ነው። እና የሚገርማችሁ በአሁኑ የግንቦት ሃያ የድል ቀን (በእኛው መዝገበ ቃል እርስ በርስ መሸናነፍም ድል ነውና) ቅዳሜ መዋሉ ብዙ የሠፈሬን ወጣቶች የተመቻቸው አይመስሉም። ምክንያቱም ቅዳሜ ያው ቅዳሜ ነው።

 ያው የወትሮ ምሱ እንደተጠበቀ ነው። የመኪና አደጋው ጠጥቶ እያሽከረከሩ በወጡበት መቅረት፣ እንዲሁም የከሰዓት በኋላው ፍራሽ ላይ በጫት ተሟሙቆ በአበደ የምርቃና ወሬ በምናብ የኑሮ ውድነቱን መቆጣጠሩ፣ የገንዘብን የመግዛት አቅም የማሳደጉ፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት በቀላሉ የሚኮንበትን ዘዴ የመቀየሱ፣ ብሎም የሐሜት ሥነ ሥርዓት እንደተጠበቀ ነው። ታዲያ ቅዳሜን ካላንደር ዘጋው ከፈተው ምን ለውጥ አለው ነው ነገሩ። በነገራችን ላይ አብዛኛው የማውቃቸው ወዳጆቼ እኔ እንዲህ ያሉ ካላንደር የሚዘጋቸው ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች ቅዳሜና እሑድ ላይ መጥተው ሲያርፉ የማይወዱ ናቸው። የአዞበት ቀን ላይ ሲያርፉ ግን ስሜቱ ልዩ ነው። ሥራ የለም የተባለ ቀን ሰነፉ ቅልጥ ያለ አርበኛ ይሆናል። እንዲያውም እንደ ባሻዬ ልጅ ስላማዊ የፖለቲካ አተናተን ከሆነ፣ የአሁኑ የግንቦት ሃያ ቀን ቅዳሜ ላይ ማረፉ ለገዢው ፓርቲ የትግል ዓመታትና የድል ዝክር ጥላ እንዳያጠላበት ያሠጋል፡፡ አዳሜ የቅዳሜ ጉዳዩ ላይ ሆኖ ምን ተባለ? ምን ተደረገ? የሚለው ግድ አይሰጠውማ!

መቼም አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስብላሉ። አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል እንዲል ጥላሁን ገሠሠ። እናማ ሥራ ሲዘጋ ደስ ከመሰኘታችን በፊት አብዛኞቻችን በትምህርት ቤት ዘመናችን ነገ ትምህርት የለም ስንባል ጮቤ የረገጥን ነን። እንዲያው ይኼን ጨዋታ የማጫውታችሁ ተጠያቂው ማን ነው? የሚለውን እንድታብሰለስሉት ነው። መቼም ሰው ሥረ መሠረቱ ልጅነቱም አይደል? በቀደም የባሻዬ ልጅ፣ “የአንድ ሙሉ ሰው አባት ወላጅ አባቱ ሳይሆን ልጅነቱ ነው፤” ስላለው ዶስቶቪስኪ የሚባል የሩሲያ ጸሐፊ ሲያጫውተኝ ነበር። እሱ ምሁራዊ አተያዩን ከማስረጃ ጋር እያቀናበረ ሲያጫውተኝ እኔ የማስበው ልጅነቴን ነበር። አንዳንዴ ዛሬያችሁ ግራ ሲጋባችሁ፣ እኔ እንዲህ ነኝ? ኧረ ማን ነኝ? ስትሉ ዝም ብላችሁ አስተዳደጋችሁ ዘንድ ሂዱ። እመኑኝ መልሱ ያለው እዚያ ብቻ ነው።

ታዲያ ምነው ሥራው ላይ ከመረባረብ በግምገማ፣ በስና ግለሒስ ተጠምደን እየዋልን መፍትሔ ያጣን? የሚል ጥያቄ ያላችሁ ግምገማውን ረግጣችሁ የመውጣት መብት አላችሁ። መልስ አልባ ሆኜ ብቻ ሳይሆን ዶስቶቪስኪ በሕይወት ስለሌ ጭምር እንጂ ቢያንስ እሱን ለማጠያየቅ መሞከሬ አይቀርም ነበር። እና ልጅነታችንን ስናጠና ትምህርቴ ቤት አርፍዶ የመግባት የአብዛኞቻችን አባዜ ትዝ ሲለኝ ዛሬ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ‹ሥራ አስኪያጁ ገና አልገቡም› የሚባለው መዳኛው ይጠፋኛል። ሠልፉና የባንዲራ ሥነ ሥርዓቱን አድምቀን ስናበቃ አንደኛው ክፍለ ጊዜ ላይ የተሰጠንን የክፍል ሥራ በገዛ ስንፍናችን ወደ ሦስት ቀን የቤት ሥራነት ስንቀይረው ያደግነውን ልጆች ሳስብ፣ ዛሬ ስለአገር ክብር፣ ዕድገትና ልማት ያዙኝ ልቀቁኝ ብለን ስናበቃ ከምናቃልለው ሸክም የቆለልነው እየታየኝ ተጠያቂው ይጠፋብኛል።

ለግርግርና ለሆታ ቅድሚያ በመስጠት ለሐሜትና ለአሉባልታ ትኩረት መድበን ስንጓዝ ብቻ እንጀራ እንደሚወጣልን እየነገሩ ያሳደጉንን ወላጆች የታዘዝን እኛ፣ ለሠርግና ለድግሱ የምንጨነቀውን ያህል ለፍቺው አለመብሰልሰላችን እውነት ምን ይገርማል? ተፈጥሮ ያላደለንን አብሾና ሥር ሥር እየጋቱ ለአንደኝነት፣ ኮሌጅ ለመበጠስ፣ በልጦ ይዞ ተቆጣጥሮ ለመገኘት ካሳደጉን ወላጆቻችን የተገኘን እኛ፣ ዛሬ ከተማውን ተቆጣጥረን ኪስ አውላቂና ሙሰኛውን ብንረሳው ምን ያስተቻል? አይደለም? ነው? “በመበላለጥ የኑሮ ብልኃት የተቃኘ ልጅነት . . . ” አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በቀደም ዶፍ ዘንቦ፣ ዝናቡን ለመጠለል የወሰደብን ጊዜ እጥፍ ጎርፉ እስኪጎድል ቆም ስናወራ። “ . . . በመበላለጥ የተቃኘ ልጅነት በጉልምስና ዘመን እያነጣጠቀ አገር ከመበጥበጥ ሌላ ውጤቱ ምን ሊሆን ኖሯል?” ሲለኝ፣ “ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?” አልኩት አስፋልቱ ላይ የሚፈነጨውን ጎርፍ እያየሁ፡፡ ‘ጎርፍ ያመጣሽ እንደሁ ልጠብቅ ወንዙን’ ብዬ ለማንጠግቦሽ ያፏጨሁበትን ዘመን እያስታወስኩ።

 ይኼን ጊዜ አንድ ሙር ዶፉ እላዩ ላይ ያለቀና በጉያው ሦስት አራት  የጫት እንጨት የሸጎጠ መጣና  “ጎርፉ ሳይደርቅ አንድ ብር ስጡኝ፤” አለን። ዝም ስንለው “ስለጎርፉ?” ብሎ ደገመው። የባሻዬ ልጅ አንድ ብር አውጥቶ ሰጠው። በቆመበት ቁጢጥ ብሎ ብሯን አጣጠፋት። አጥፎ አጥፎ ሲያቃናት ጀልባ ሆነች። “እኔን አልቀናኝም እስኪ አንቺ ሞክሪው፤” ብሎ አንሳፈፋት። የባሻዬ ልጅ ተናዶ “አንተ?! ወንጀል እኮ ነው፤” እያለ የሚያደርገው ሲጠፋው፣ “ለምን የእኔን አላልክም?” አለው። የባሻዬ ልጅ ግራ ገባው። “እኔም እኮ ሥጋና ነፍስ ያለኝ የምራመድ ወንጀል ነኝ። ሲለምኑብኝ ለምን ዝም አልክ? ዋጋዬን ሲከለክሉኝ፣ ግዴታዬና መብቴ ላይ ሲጫወቱ፣ ውኃ ሲያስበሉኝና የትም ሲጥሉኝ መልሰው ስሜን ብቻ እያነሱ በጥጋብ ሲሳከሩብኝ ለምን ዝም አልክ?” ቢለው ምን ይበል? ረክሳ ሰውን የምታረክስ ዓለም!

በቀደም አንድ ሪሞርኬ ሳሻሽጥላችሁ ሻጩ ደንበኛዬ ትኩር ብሎ የጣት ቀለበቴን እየተመለከተ፣ “ትዳር እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹አሸወይና ነው። ወርቅ ሚስት አለችኝ፤” አልኩት። አንዳንዴ ከጥያቄው በፊት የተዘጋጁ መልሶች ችግር ይፈጥራሉ እኮ። ለካስ ዕድሜው ከእኔ ከጎልማሳው የማያንሰው ደንበኛዬ አራተኛ ጣት ባዶ ኖሯል። ምን ብዬ ጨዋታዬን ልቀጥል። “ይገርምሃል ከጓደኞቼ ሁሉ ሳላገባ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤” አለኝ፡፡ ‘ግድ የለም ሁሉም በጊዜው ይሆናል’ ብዬ ሌላ የተዘጋጀ መልስ ከመመለስ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ አንዳንዱ  ባለማግባቱ የሚበሳጨውን ያህል ሌላ በምንም ሲበሳጭ አላየሁማ፡፡ “ምነው አልክ?” አልኩት ብዙም እንዳልደነቀኝ ሆኜ፡፡ “ዕድሜ ለጓደኞቼ፡፡ መማሪያ ሆኑኛ፡፡ አንድ ሁለቱ ይሻላሉ እንጂ የሰባቱ ኑሮ ሲኦል በለው። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው። ዘመኑ እንደምታየው ስለእኩልነት የሰበከውን ያህል ስለአንተ ትብስ አንቺ አይሰብክም። እናም እኔ ይኼን እያየሁ ምን ተማምኘ ላግባ? ያውስ በመሸበት ማደር በቀለለበት ዘመን?” ሲለኝ ከልቤ አዘንኩ።

ኋላ ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ከባሻዬ ጋር ስንጫወት ይኼው ደንበኛዬ ያለኝን ብነግራቸው፣ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው ‘ዋ’ ብለው ቀሩ። “ምነው?” ስላቸው፣ “ያለሙያቸውና ፍጥረታቸው ገብተው የተደናገሩ ከበሮ መቺዎችን እያየ ስንቱ ከበሮውን ትራስ አደረገው? ስንቱ ዛሬ ታይተው በነጋታው በፈረሱ ትዳሮች ውጥኑ ፈረሰ? ለአገር ለወገኑ ስንት ዓላማና ዕቅድ ያለው ከእሱ በፊት የነበሩትን እያየ ስንቱ ሀሞቱ ፈሰሰ? ስንቱ ከሰላማዊ ትግል ሸሸ? ስንቱ ሕይወትን ተፀየፈ?” ሲሉኝ  አዝማቹን እየደጋገምኩ አጀብኳቸው። ‹እባብ ያየ በልብጥ በረየ› እንደሚባለው ሰው በስንቱ ይንገፈገፋል? ኧረ ስንቱ? ስንቱ?!

በሉ መሰነባበቻችን ደርሷል። እኔና የባሻዬ ልጅ ወደተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ጎራ ብለን አንድ አንድ ማለት ጀምረናል። ‘ያም ሲያማ ያም ሲያማ፣ ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ’ ይላል በሚስረቀረቅ ድምፁ የሙዚቃው ንጉሥ። አንዱ ከመቀመጫው ተነስቶ፣ “25 ዓመታት ምን ተሠራ? መንገድ፣ ግድብና የጋራ መኖሪያ ቤት ወዘተ ወዘተ፡፡ በእርግጥ ብዙ ለውጥ አየን፡፡ ጥያቄው . . . መንገዱን እየፈነጨበት ያለው ማን ነው? ነው፡፡  መልሱ . .. .”  ሲል የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በአንድ ድምፅ “ሌባው!” ብለው አስተጋቡ። ድንግጥ አልኩ። ሌላው ተነስቶ፣ “ብሶት ቀብረን ብሶት የምናምጥ ከሆነ ለምን አንደኛችን ድምፃችንን አዘግተን አንገላገልም?” ሲል ሰው አሽካካ። ደግሞ ሌላው ተነሳና “ማሳሰቢያ አለኝ!” አለ። ‘በል’ ሲባል “ሳቃችሁን በቁጥጥር ሥር አውላችሁ ሳቁ ለማለት ነው። ምናልባት ከጣራ በላይ ስትስቁ ‘ፊውዝ’ ተቃጥሎ ሳምንት መብራት እንዳይጠፋ። አመሰግናለሁ፤” ብሎ ገና ሳይቀመጥ ሌላ ሳቅ። እኔ በመገረምና ግራ በመጋባት ድባቡን አስተውላለሁ። ሁሉም ተቺ ነው። ሁሉም ጥያቄ አለው። ሁሉም አንደበቱ ለነገርና ለሒስ የሰላ ነው።

 ‘እኛስ ማን ነን? ሌባው ጎረቤቴ አብሬው የጠጣሁት አብሬው የበላሁት፤ አይዞህ አትፍራ ምን አባቱ ያልኩት አይደለም እንዴ?’ የሚል አንድ እንኳ የለም። ኋላ ውሎ አድሮ ለባሻዬ ትዝብቴን ስነግራቸው፣ “ንጉሥ ዳዊት ራሱን በአምላኩ ፊት ሲያይ ምን አለ መሰለህ?” አሉኝ፡፡ “ምን አለ?” ስላቸው “‘እኔስ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው?’ – አየህ ‘ጠቢብ ሰው ዓይኖቹ በገዛ መንገዱ ላይ ናቸው’ ያለንን ጠቢቡን ሰለሞንን የወለደው እንግዲህ እሱ ነበር፤” አሉኝ። አላልኳችሁም? ዛሬያችሁ ላይ ጥያቄ ካላችሁ ልጅነታችሁን መርምሩት አላልኳችሁም? ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው ጎበዝ? ጠያቂውስ? ‘ኧረ እኛስ ማን ነን? ጥያቄያችንስ የማን ነው?!’ ብለን ተለያየን፡፡ “ራስን የማወቅ ዘመን ያድርግልን’ ብለዋል ባሻዬ። አሜን አትሉም? መልካም ሰንበት!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት