በሪዮ ኦሊምፒክ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ዝግጅቱን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በቡድኑ ዙሪያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ አትሌቶች ከምርጫና ከሥልጠና ጋር በተገናኘ ‹‹ከእኛ በላይ ስለእኛ የሚያውቅልን አይኖርም›› የሚሉ ብሔራዊ አትሌቶች እንዳሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ከማራቶን ተወዳዳሪዎች ውጪ ቁጥራቸው ከ66 በላይ አትሌቶች በሆቴል ተሰባስበው ሁለተኛውን የዝግጅት ምዕራፍ ጀምረዋል እያለ ነው፡፡
31ኛው ኦሊምፒያድ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ይካሔዳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 በላይ የዓለም አገሮች ብሔራዊ የልኡካን ቡድኖቻቸውን በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በዋናነት የምትሳተፍበትና በኦሊምፒክ መድረክ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ከሚካተቱ አገሮች አንዷ ትሆን ዘንድ የምትታወቅበት አትሌቲክስ ይጠቀሳል፡፡ የአበበ ቢቂላን የሮም ኦሊምፒክ ጣፋጭ ድል ተከትሎ በታሪክ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ አሁን በዙሪያው የሚነገረው ከተስፋው ይልቅ አሉታዊ ነገሩ እየጎላ መምጣቱ የሚያሳስባቸው በርክተዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ከአትሌቶች ምርጫና ከሥልጠና ጋር ተያይዞ እየተነገረ የሚገኘው ክስተት የአገሪቱን የቆየ የአትሌቲክስ ባህል እንዳይበርዝ ለአትሌቲክሱ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ሥጋታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት ምንጮች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት ለብራዚል ኦሊምፒክ ተመርጠው ዝግጅት እያደረጉ ከሚገኙት ብሔራዊ አትሌቶች የማራቶን ተመራጮችን ጨምሮ፣ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች በግል አሠልጣኞቻቸው ካልሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በመደባቸው አሠልጣኞች ለመሠልጠን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህንኑ አንዳንድ ብሔራዊ አትሌቶችም አረጋግጠዋል፡፡ አትሌቶቹ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ከጎረቤት አገር ኬንያውያን ጀምሮ በርካታ የዓለም ታላላቅ አትሌቶች አሁን በኢትዮጵያ እንደሚነገረው ዓይነት ሥልጠና እንዲወስዱ የማይገደዱ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡
የአትሌቶቹን ወቅታዊ አቋምና አስተያየት አስመልክቶ ሪፖርተር ለፌዴሬሽኑ አንዳንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአትሌቶችንም ሆነ በስፖርቱ ዙሪያ ያሉ ሙያተኞችን አስተያየት በመውሰድ ብዙ ጊዜ ለማቀራረብ ቢሞክርም ሊሳካለት እንዳልቻለ ነው ያስረዱት፡፡ መፍትሔውስ ለሚለው ቀጣይ ጥያቄ አመራሮቹ አትሌቶቹ በመረጡት መሔድ ካልሆነ ደግሞ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሔድ የሚችሉትን አትሌቶች መርጦ ማዘጋጀት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ሪፖርተር ለአትሌቶቹ ደኅንነት ሲባል ማንነታቸው ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሆቴል ተጠቃለው ከገቡት አትሌቶች በግል አሠልጣኞቻቸው በመሠልጠን ላይ ያሉትን አትሌቶች ማንነት ሳይቀር የፌዴሬሽኑ አመራሮች ይፋ አድርገዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ከምርጫ ጋር በተገናኘም ተመሳሳይ ችግር መኖሩንም አልሸሸጉም፡፡