Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉግንቦት 20 እና የአዲሱ ምዕራፍ እንቅፋቶች

ግንቦት 20 እና የአዲሱ ምዕራፍ እንቅፋቶች

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

የሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወታደራዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ከወረደ ሩብ ክፍለ ዘመን አለፈ ሲባል ቀላል ይመስላል፡፡ ግን ዝግ ብሎ ለቆጠረው የአንድ ፈርጣማ ወጣት ዕድሜ ነው (የአንድ ትውልድ የጎብዝና ምዕራፍ እንዲሉ)፡፡ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ላይ ቆመን ታዲያ ስለቀደመው ሥርዓት ከንቱነት፣ አምባገነንነትና አውዳሚነት ብቻ ልናወራ አንችልም፡፡ በዚያ በኩልማ አፍሪካም ዓለምም በርካታ አምባገነናዊ ሥርዓቶችን አራግፈዋል፡፡

በተመሳሳይ ከግንቦት 21 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም፣ በአገሪቱ ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻም ሊያወራ አይችልም፡፡ በዚያው ልክ ኢሕአዴግ የሚመራት አገር አንድ ክፍለ አገር ያጣች፣ የባህር በር የሌላት፣ ሕዝቦቿ አንድነት የሌላቸው፣ የባንዲራ ፍቅር የሌላት፣ ወዘተ ሆናለች እያልንም ስናለቅስ አንከርምም፡፡

ይልቁንም ትናንት 25 ዓመት የሞላው የሥርዓት ለውጥ በተጓዘው ረጅም ምዕራፍ ውስጥ በተገኘው ውጤት ላይ (በብዛት ሰሞኑን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተነግሯል) ተጨማሪ ውጤት ለማምጣትና አገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለመውሰድ ምን ላይ ቢተኮር ይበጃል የሚሉ ነጥቦችን እናነሳለን፡፡ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ተስፋዎች የሚመለከቱ ታዛቢዎች አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነትና ትርምስ ያሳለፈችውን ጊዜ በቁጭት እንደሚያስታውሱ ሁሉ፣ እኛም ከመፀፀት እንዲህ ቢሆን ማለትን ለማስቀደም እንሻለን፡፡ ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን እያነሳን እንወያያለን፡፡

ሕግና ሕገ መንግሥት ይከበሩ

አገሪቱ ያወጣችው ሕገ መንግሥት በመርህና በያዛቸው አንቀጾች ዲሞክራሲያዊነት ደረጃ የሚታማ አይደለም፡፡ አንዳንድ በመስመሮች መሀል ጥርጣሬ የሚነሳባቸው አንቀጾች መኖራቸው ባይካድም፣ አብዛኞቹ ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ስምምነቶችን ያከበሩ ናቸው፡፡ ከኖርንበት አሀዳዊና ያልተማከለ ሥርዓት አንፃር አንቀጽ 39ንም ቢሆን ‹‹ይበትነናል›› ስንለው ብንኖርም፣ በዓለም አገሮች ሕገ መንግሥታት ውስጥ በፍፁም የሌለ አንቀጽ አይደለም፡፡

እንደሚታሰበው በአንድ ጊዜ አገር እንደ ወረቀት የሚገነጣጥል አንቀጽ አለመሆኑም ቢያንስ ባሳለፋቸው ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ታይቷል፡፡ በእርግጥ የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነትና ኅብረት አጠናክሯል አላልቷል? የማንነትና የብሔር ጥያቄዎችን መልሶ ጨርሷል ይቀይረዋል? የሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍልን አረጋግጧል ይቀይረዋል? የሚለውን ከፖለቲካና ከፕሮፓጋንዳ አድልኦ ወጥቶ በምሁራዊና በገለልተኛ መንገድ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

አሁን የዚህ አገር ፈተና የሆኑት ግን ሕገ መንግሥቱና የሚወጡ ሕጎች ሳይሆኑ አፈጻጸም ላይ ያለው መጓደል፣ የሕግ ምሰሶዎች የመነቀልና የመጣል አደጋ ነው፡፡ በእርግጥ የማስፈጸም አቅም፣ ከኖረው አመለካከት ከታችነትም ይበል ከተጠያቂነት መረቡ መርገብ የአፈጻጸም ጉድለቱ በእጅጉ ሲታረም አልታየም፡፡ በዚህም በሕግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ ቀላል የማይባሉ ጫናዎች እየተፈጠሩ መጥተዋል፡፡

ለአብነት ያህል ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ በመላው አገሪቱ እያነታረከ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝብ ሲያስመርር የቆየው በቀዳሚነት ሕግ በመጣስ፣ በማዛባትና በተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ ጥቂት ሕግ ተርጓሚዎችና አስፈጻሚ አካላት በተሰጣቸው ሥልጣን በማናለብኝነት ያሻቸውን ካደረጉ አደጋው ለሁሉም ነው፡፡ መሬት እንዴት ይተዳደራል? ይተላለፋል? የመንግሥት ዕቃ እንዴት ይገዛል? ይሸጣል? የሕዝብ አገልግሎት በፍትሐዊነት እንዴት ለሕዝብ ይሰጣል፣ ወዘተ ለሚባለው ሁሉ ሕግና ሥርዓት አለው፡፡

በአንድ በኩል የወጡት የሚያማምሩ የአገሪቱ ሕጎች እየጣሱና እያጣረሱ ሊገለገሉባቸው የሚሹ ዜጎች (በተለይ አንዳንድ ባለሀብቶች፣ ደላሎችና ጉዳይ ገዳዮች) እየበረቱ፣ በሌላ በኩል የሕግ የበላይነትን በገቢር ያልተቀበሉ መንግሥት ውስጥ የመሸጉ ሙሰኞች በእንጭጩ እየታረሙ ካልሄዱ ያለጥርጥር ሥርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ሲወድቅም ደግሞ ሕዝብ ተማሮና ተንገፍግፎ ከሆነ ወደኋላ መመለስንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ናይጄሪያ፣ ብሩንዲ… ሳያድጉ ቀርተው ሳይሆን ችግር ውስጥ የገቡት የሕግ የበላይነት ስላጡ ነው፡፡

የሀብት ክፍፍል በፍትሐዊነት ይረጋገጥ

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ‹‹ከልማታዊ›› ባህሪው አኳያ ከነፃ ገበያ የተሻለ የገበያ ጣልቃ ገብነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግሥት መንገዶች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክና የመጠጥ ውኃ አገልግሎት እየገነባ ያቀርባል፡፡ ከዚያ የሚገኘውንም ጥቅም እየወሰደ ለሌላ ልማት እንደሚያውል ይጠበቃል፡፡ ሥርዓቱ አቅሙ በፈቀደው መጠን መደጎሙ ገበያ ማረጋጋቱና የታክስ ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋቱ በፍፁም ሊካድ አይችልም፡፡

እንዲህ እያደረገ ያለ መንግሥት ‹‹እንዴት ፍትሐዊ የሀብትና የሥራ ዕድል ክፍፍል ማረጋገጥ ይሳነዋል?›› ነው ጥያቄው፡፡ አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቃን ከ30 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ይመረቃሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ‹‹በሥራ ፍጠሩ›› ተልዕኮ ሥራ አጥ ሆነው የሚቀመጡ ናቸው፡፡ ከኮብልስቶን እንደ መለስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ያለው የጥቃቅን ዘርፍም እንደሚታሰበው ለሁሉም የሚመች አይደለም፡፡ የግል ባለሀብቱና የመንግሥት መዋቅሩ የመቀበል አቅምም ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በየመንደሩ ‹‹ሥራ አጥ ምሁራን›› የነገ ኢትዮጵያ ሸክም እየሆኑ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት፣ ሰፊ የሥራ ዕድልና ባለድርሻ አካላትን የያዘ ነው፡፡ ግን በዘርፉ የተሰማሩት እነማን ናቸው? የአገሪቱ የሙያ ሰዎች ተሳትፎ ምን ይመስላል? ተብሎ ሊታይ ይገባዋል፡፡ መንግሥት የዘርፉ ዋነኛ ተዋናይ በሆነበት ሁኔታስ ፍትሐዊ ተወዳዳሪነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ መጠየቅ ካልተቻለ ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ንግዱም፣ ኢንዱስትሪውም፣ የአገልግሎት ዘርፉም ያው ነው፡፡

ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ሥርዓቱ ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን ደግሞ ሥርዓቱ ላይ ያሉ እንከኖች ተለይተው እየታረሙ መምጣታቸው ሒደቱን እንደሚያሻሽለው ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን በከተሞች የተቀጣሪው ደመወዝና ለምግብ፣ ለልብስ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርትና ለሌሎች ወጪዎች ምጣኔ ሲሳሳ ከፍተኛ ቀውስ የሚጋብዙ ሁኔታዎች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል የገበያና አገልግሎት ክፍያን በማረጋጋት፣ በሌላ በኩል የብዙኃኑን የከተማ ተቀጣሪ ነዋሪ ክፍያ በማሻሻል የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት መዘርጋት ካልተቻለ፣ በዚህ መንገድ ሌላ 25 ዓመታትን ለመቀጠል የሚታሰብ አይሆንም፡፡

ለሀብት ክፍፍል መረጋገጥ የሥልጣን ዲሞክራሲያዊ ክፍፍልና መልካም አስተዳደርን ማስፈንም ያላቸውን ሚና መዘንጋት አይገባም፡፡ ብዙኃኑን ሊጠቅም የሚችለው ብዙኃኑ የሥልጣን ባለቤት ሲሆኑን ነው፡፡ ሕዝቡ በፈቃዱ የመሾምና የመሻር፣ የመጠየቅና የመከታተል ባለቤትነትን ሲያገኝም ነው፡፡ ምንም ቢሆን የጥቂቶች አድራጊ ፈላጭነት ወይም ‹‹አየሩን ሁሉ ልሙላው ባይነት›› ሊኖር አይገባም፡፡ ሄዶ ሄዶ ከሕዝብ መነጠልን ያስከትላል፡፡ የሚታሰበውን ያህል ረጅም ርቀትም ሊወስድ አይችልም፡፡ ስለዚህ መጪው ጊዜ በጥብቅ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን ያለመ ጉዞን የሚሻ መሆኑ ሊጤን ይገባዋል፡፡

የአገር ሉዓላዊነትና ክብር አይደፈር

አሁን ያለው መንግሥት የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ፖሊሲዎች አቅጣጫ ይታወቃል፡፡ በአብዛኛው በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ፣ ጠላቴ ድህነትና ኋላቀርነት ነው ብሎ ወደ ውስጥ ብቻ የማያማትር፣ ጠላትና ወዳጅ ለይቶ ከመቀመጥ ይልቅ ከሁሉም ጋር በጋራ ጥቅም ላይ መደራደር የሚል ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ቀላል የማይባሉ ትርፎች ስለመገኘታቸው በግሌ አልጠራጠርም፡፡

ነገር ግን የኢሕአዴግ መንግሥት በግልጽ የሚወቀስባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የአገሪቱ ወሰንና ድንበር ላይ ግልጽ አቋም ይዞ አለመቆጨት፣ በድንበር አካባቢ በዜጎች ላይ የሚደርስን ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል ከ‹‹ጉርብትና አይብስም›› ብሎ ማለፍ ይቀናዋል፡፡ በሰሜኑ በኩል ከኤርትራ ጋር ‹‹ጦርነት የለም ሰላም የለም›› ፍጥጫ ውስጥ ለዓመታት መቀጠሉ ለአባባሉ ማሳያ ነው፡፡

በመሠረቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገሮችም ጋር ቢሆን ፀብን በመሸሽ የዜጎችን ሕልፈትና ስቃይ በዝምታ የሚያልፋቸው አጉል ለዘብተኝነቶች አሉ፡፡ (እዚህ ላይ ሞገደኛና ፀብ አጫሪ ይሁን ለማለት ባይሆንም) ለአብነት ከሳዑዲ ዓረቢያ 150 ሺሕ ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን መባረር፣ የደቡብ አፍሪካ የደርባኑ ጥቃት፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በሱዳን የታጎሩ ዜጎች ሁኔታ እምብዛም ሲያስጨንቀው አልታየም፡፡ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች (የሶማሊያና የሱዳን) የሞትና የቁስለኛ መረጃ መሸሸግንም ከዚህ ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡  

ከዚህ አንፃር የአገርን ድንበር፣ ሰንደቅ ዓላማና ሕዝብ ማክበርና ማስከበር ከመንግሥት በላይ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል እንደሌለ ሊጤን ይገባዋል፡፡ አንዳንድ በእነዚህ ቁልፍ የአገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ አቋም መያዝ ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ከማንነት በላይ አስበልጦ ማቀንቀን›› ተደርጎ እንደሚቆጠርም ይታወቃል፡፡ ትምክህተኝነትና ‹‹የቀደሙት ሥርዓቶች አቀንቃኝነት›› ታፔላም ያስለጥፋል፡፡ ይኼ ግን ስህተት ብቻ ሳይሆን ፍፁም ስህተት መሆኑን መረዳት ያለብን፣ በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም አገሮች የሚሰጡትን ትርጉም ስንፈትሽ ነው፡፡

አንድ የማይካድ እውነት አገር የሚከበረው ከድህነትና ከኋላቀርነት ሲላቀቅ ነው፡፡ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሚሊተሪ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሲኖረውም ነው፡፡ ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለሕዝቡ፣ ለድንበሩ፣ ለሉዓላዊነቱና ለሰንደቅ ዓላማው ቀናዒ በሆነ ሕዝብና መንግሥትም አገር ይከበራል፡፡ ስለዚህ ቀጣዩ የመንግሥትም ሆነ የትውልዱ ትኩረት በዚህም ላይ ሊሆን ግድና ግድ ነው፡፡

ለአብነት ያህል በእግር ኳስ፣ በሩጫ፣ በኪነ ጥበብ፣ በጥናትና ምርምር፣ ለአገር በሚደረግ ውለታ፣ ወዘተ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዜጎች የሚከበሩበትና ዋጋ የሚያገኙበት ሥርዓት መበጀት አለበት፡፡ ባለውለታዎች እየተገፉ ‹‹ድንገት የታወቁ ጥራዝ ነጠቆች›› አየሩን በሞሉት ዕውቀት፣ የላቀ ሥራና አገር ማስከበር ዋጋ ሊኖር አይችልም፡፡

የፖለቲካ መተማመንና የጋራ እሴት ይገንባ

የሠለጠነው ዓለም የብሔራዊ መግባባትና የፖለቲካ መተማመን ደረጃው ከፍተኛ ስለሆነ፣ በአንድ በኩል ከሰላማዊና ከዴሞክራሲያዊ አካሄድ ውጪ የሥልጣን ሽግግር የለም፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ቢለዋወጡ እንኳ የነበረውን እያፈረሱ ከአዲስ የመጀመር አባዜ የለባቸውም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ አገር ለዘመናት የመጣንበት መንገድ የመጠፋፋትና የማፍረስ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 150 ዓመታት በሥልጣን ሽኩቻው ውስጥ እዚያና እዚህ የተላጋው የአገሪቱ ዜጋ፣ የሞተውና የቆሰለው እንዲሁም እስካሁን በጥላቻ የፖለቲካው ራስ ምታት የሚናውዘው ሲታይ ገና ተሃድሶ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥ ነው ከግንቦት 20 ቀን 1983 ወዲህ በኢትዮጵያ አዲስ ዓይነት የፖለቲካ አየር መንፈስ ጀምሯል፡፡ ቢያንስ መጠኑና ፍትሐዊነቱ ቢያከራክርም ዕድገት አለ፡፡ አንፃራዊ ሰላሙና ጅምሩ ዴሞክራሲም ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን አሁንም የፖለቲካ መተማመንና የጠበቀ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት አይቻልም፡፡

መንግሥትና ገዥው ፓርቲ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ‹‹ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል›› ይላል፡፡ ጭፍን ተቃዋሚ ኃይሎች ደግሞ እንደ ዓባይ ግድብን በመሰሉ አገራዊ ሀብቶች ላይ እንኳን ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ትችት ነው የሚቀናቸው፡፡ የባሰበት ደግሞ ‹‹እስከጠቀመ›› ድረስ፣ የፖለቲካ ትርፍ እስካገኘ ድረስ የሚሠራው የፖለቲካ ሥራ አገር ቢበተን ወይም ሕዝብ ቢበድል የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዲሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ) ኢሕአዴግም ቢሆን ‹‹በሥልጣን ካልቀጠልኩ አገሪቱ ትበታተናለች›› የሚለውን መዝሙር ደጋግሞ መግለጽ ይቀናዋል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ብዝኃነት (የፌዴራል ሥርዓቱን) ከኢሕአዴግ ውጪ የተቀበለው የሌለ ይመስል፣ የሥልጣን ሽግግር ተደረገ ማለት በሥልጣን ላይ የነበሩ አካላት ይጠቁና የአገሪቱም ልማትና ሀብት ይወድማል በሚል ጨለምተኛ ቅስቀሳ ውስጥ የፖለቲካ አለመተማመን እንዲፈጠር ማድረግ አፍራሽነቱ የጎላ መሆኑ አይቀርም፡፡

በመሠረቱ የፖለቲካ መተማመን ለመገንባት ከፖለቲካ ኃይሎች ባልተናነሰ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ሚናም ሊጎለብት ግድ ነው፡፡ ‹‹እሺ እሺ›› ባይ በበዛበት ከብዙኃኑ ሕዝብ አመለካከት ወጣ ባለ መንገድ ለእውነት፣ ለመርህና ለአገር ሲባል አቅጣጫ የሚያሲዝ ከሌለ አሁንም የፖለቲካ አለመተማመኑ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ በተለይ ደግሞ መጪው ትውልድ በጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና በአንድ የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ መቆም ካልጀመረ ጦሱ ቀላል አይሆንም፡፡

በጥቅሉ 25ኛ ዓመት የግንቦት 20 በዓል አልፎ 26ኛውን ዓመት አንድ ብለን በጀመርንበት በዛሬው ቀን፣ ሥርዓቱ በጉድለቶቹ ላይ መነጋገሩ ሁሉንም ወገን የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ሐሳባችሁን እንድትሰነዝሩበት እጋብዛለሁ፡፡            

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...