Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የእንጀራችንን መልካም ስም የሚያጐድፍ ‹‹እንጀራ››

በመዲናችን አዲስ አበባ በየመንደሩ የጦፈ ቢዝነስ እየተሠራባቸው ወይም በከፍተኛ ደረጃ ግብይት ከሚፈፀምባቸው ምግብ ነክ አቅርቦቶች ውስጥ አንዱ እንጀራ ነው፡፡ ወትሮ ከቤት ውጭ የማይዘጋጀውና እንደ አሁኑ በየመደብሩ ለሽያጭ የማይቀርበው እንጀራ የደራ ገበያ የሚገኝበት እየሆነ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የቀደመው ልምዳችን ወይም የአኗኗር ዘያችን እንደሚነግረን እንጀራን ከመደብር መግዛት እንደ ነውር ይቆጠር ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ታሪክ ተለውጧል፡፡ እንደ እንጀራ ሁሉ እንደ በርበሬና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን በጓዳችን ከማዘጋጀትና ከመጠቀም ይልቅ የተዘጋጀውን ከመደብሮች ገዝቶ መጠቀም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ዛሬ በየመንደሩ በሚገኙ ብዙዎቹ መደብሮች ውስጥ እንጀራ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ሱፐር ማርኬቶች ሳይቀሩ እንጀራን ለደንበኞቻቸው ያቀርባሉ፡፡ አሁን እየታየ ያለው ፍላጐት ወደፊትም እየጨመረ የመሄዱ ነገር አያጠራጥርም፡፡ በቤት ለማዘጋጀት ቢፈለግ እንኳን ለማዘጋጀት የሚሆን ቦታ የለም፤ ጊዜ የለም፡፡

ከአመጋገብ ባህላችን ጋር ተያይዞ በየዕለቱ ከገበታችን የማይጠፋውን እንጀራ ለመመገብ ቤት ካልተገኘ ወደ አንዱ መደብር ሮጥ ብሎ ገዝቶ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ችግሩ ግን እየተስፋፋ የመጣው የእንጀራ ገበያ አደጋና ሥጋት እየሆነ መምጣት መጀመሩ ነው፡፡ ፍላጐት እየጨመረ ሲሄድ ገበያውን ለመቀላቀል ብዙ ሸፍጦችም ብቅ ይላሉ፡፡ በብዛት ለማቅረብ ሲባል በጥራት የማዘጋጀት ፍላጐት እየቀነሰ እንዲመጣ እያደረገውም ነው፡፡

ሸማቾች በእምነት የሚገዙት እንጀራ የጥራት ደረጃ ማንም የሚመዝነው የለም፡፡ እንጀራነቱን እንጂ ከምንና እንዴት ተዘጋጀ ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ ያው በስመ የጤፍ እንጀራ እየሸመትን እንጠቀማለን፡፡ እንጀራን በግልና በማኅበር የሚያዘጋጁና በጅምላ የሚያቀርቡ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እንጀራ የሚጋግሩበት ሥፍራ ምን ያህል ፅዳቱን የጠበቀ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ አካል ስለሌለ፣ ፅዱ ባልሆነ ቦታ እንጀራ ይጋገራል፡፡ የከተማችን ባለኮከብ ሆቴሎችን ጨምሮ እንደየአቅማችን የምንጠቀምባቸው ምግብ ቤቶች የሚያቀርቡልን እንጀራ ራሳቸው የሚያዘጋጁት ስላልሆነ የግዥ እንጀራ በየሄድንበት ይከተለናል፡፡

ልብ ብላችሁልኝ እንደሆን ንፅህናው ባልተጠበቀ ሠፌድ ተደርድሮ በአደፈ ጨርቅ ወይም ላስቲክ ተሸፍኖ በታክሲዎች ላይ የሚጫነው እንጀራ ተጓጉዞ ከአንዱ ሆቴል ገብቶ እንመገበዋለን፡፡ አዘገጃጀቱ ከሚጋገርበት ቦታ ወደ መብሮችና ሆቴሎች የሚጓጓዝበት መንገድ ሁሉ ደስ አይልም፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት በይፋ የሰማነው ዜና ማረጋገጥ እንደቻልነውም በአዲስ አበባ ከተማ ከእንጨት ፍቅፋቂ ወይም ሰጋቱራ የተቀላቀለበት እንጀራ እየተዘጋጀ ለገበያ ሲቀርብ መያዙን ነው፡፡ ሰጋቱራን ከተለያዩ እህሎች ዱቄት ጋር ቀላቅለው የሚያዘጋጁትን እንጀራ ለገበያ ሲቀርብ መያዙን ያስታወቀው የመድኃኒትነት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ እንጀራ እንዲህም እየተዘጋጀ በድፍረት ተመገቡ እየተባልን መሆኑን ያረጋገጠልን ይህ ድርጊት፣ የእንጀራ ግብይት ላይ ልዩ ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡

ይህ ሰሞናዊ ወሬ በተመሳሳይ መንገድ እስከ ዛሬ የተፈጸመው ወንጀል ምን ያህል ሸማቾችን ጤና እንዳወከ ቤት ይቁጠረው ከማለት ውጭ ምን ሊባል ይችላል? ማን ያውቃል ‹‹እንጀራ›› ተብሎ የቀረበለትን ተመግቦ የማይድን በሽታ የታቀፈ እንዳለም እንገምታለን፡፡ የእንጀራ አቅርቦት በተለያየ መንገድ የሚከናወን ሲሆን እንጀራ የመጋገሩንና የመቸርቸሩን ሥራ አጣምረው የሚሠሩ፤ ጋግረው ለሆቴሎችና ለመደብሮች የሚያከፋፍሉ አሉ፡፡ ትልቁ ችግር ያለው ግን በብዛት ጋግረው ወይም አስጋግረው ለመደብሮችና ለሆቴሎች የሚያቀርቡት ናቸው ሊባል ይችላል፡፡

ባለመደብሮቹ የቀረበላቸውን ‹‹እንጀራ›› ሸጠው የራሳቸውን ትርፍ ቀንሰው ያለጣጣ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እንጀራው ቢያድርና ባይሸጥ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የጥራት ደረጃው ምንም ይሁን ምን የሚከራከሩ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ ባለሆቴሎችም ቢሆኑ በተመሳሳይ መንገድ ከእንጀራ አቅራቢዎች የሚቀበሉ ናቸውና ዋጋው ቀነስ ያለውን ይመርጣሉ፡፡ ጥራቱ ላይ ትኩረት የላቸውም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ነገር ግን እንዴት እንደሚጋገር እንጀራው ከምን የተዘጋጀ እንኳን እንደሆነ ለማጣራት የሚሞክር አለ ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ እንዲህ ካለው የእንጀራ አዘገጃጀትና ግብይት ግን አደጋው ቀላል እንደማይሆን መጠርጠር የለበትም፡፡ ከሰሞኑ የሰማነውም ዜና በዜና ደረጃ ስለተነገረ ነው እንጂ ከዚህም የባሰ ውንብድናዎች እንደሚፈጸሙ መገመት አያዳግትም፡፡

ለዚህም ነው እንጀራና ሌሎች የባልትና ውጤቶች ተጠቃሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውና ምርቶቹም በቀጥታ ከጤና ጋር የሚገናኙ በመሆኑ፣ ግብይቱ ቁጥጥር ያሻዋል የሚባለው፡፡

እነዚህ ምርቶች በኅብረተሰቡ ላይ ከሚያስከትሉት አደጋ አንፃር ታይቶ የመቆጣጠሪያ ሥልት እስካልተበጀ ድረስ አደጋው የከፋ እንደሚሆን የሰሞኑ ክስተት ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል፡፡

በርበሬ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ መሸጥ፣ ቅቤን ከሙዝ ጋር ሰልቅጦ ግዙን ማለት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በእግር እየተረገጠ ፋጉሎ ዘይትም ተመርቶ ገበያ ውስጥ ሲሸጥ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እያንዳንዳችን የገበታ ጠረጴዛ ላይ የማይታጣው ሽሮ ወጥ ለማዘጋጀት የምንጠቀምበት ሽሮ በእርግጥ ከንፁህ አተር ወይም ሽንብራ ተዘጋጅቶ ስለመቅረቡ ምን ማረጋገጫ አለን?

ነገር ግን እነዚህን ምግብ ነክ ምርቶች በትክክል በተገቢው ማዘጋጃ ግብዓቶች በጥራት ስለመዘጋጀታቸው የምናረጋግጥበት መንገድ ቢኖር ሰሞኑን አጀብ ከተሰኘንበት የእንጀራ አዘገጃጀት የባሰ ውንብድና እንደሚገኝ በእርግጠኝነት መናገር ይችላል፡፡ ችግሩ ተቆጣጣሪ መጥፋቱና ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕድል አለመኖሩ ነው፡፡

ለማንኛውም እነዚህን ምግብ ነክ ምርቶች እየሰፋ ካለው ገበያቸው፤ እንዲሁም ተጠቃሚዎቻቸውም እየተበራከቱ ከመምጣታቸው አንፃር ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት እንዴት እንደሚዘጋጁ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ማመቻቸት ያሻል፡፡ ምርቶቹን አዘጋጅተውና አቀነባብረው የሚያቀርቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ማንነት የሚለይበት መንገድ መፈለጉም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

ዛሬ ከውጭ የሚገቡ የታሸጉ ምርቶች ሊይዙ የሚገባቸውን ደረጃ እንደምናስቀምጥ ሁሉ ለእነዚህም ምርቶች ደረጃ ማውጣት እንዲሁም ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ አካል እንዲዋቀርላቸውም ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ካልሆነ በዘፈቀደ በሚዘጋጁ እንደ እንጀራ ያሉ ምርቶች ዜጐች አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀርም፡፡

ዳቦ ምን ያህል ግራም በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥና የማምረቻ ግብዓቱ ምን መሆን እንዳለበት የተቀመጠ አሠራር አለ አይደል? ለእንጀራ፣ ለበርበሬና ለመሳሰሉትስ ደረጃ ማውጣት ምን ይገዳል? የግብይቱ ሒደትም ቢሆን መላ ካልተበጀለት ለመኖር የምንመገበው እንጀራ ወደ ሞት እንዳይወስደን ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ከሰሞኑ ከሰማነው መረጃ ያገባኛል፤ እንዲያውም ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ድርጊቱን ይፋ ያደረገው ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ያለበት ኃላፊነት ብዙ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ላሉ አሳሳቢ የምንላቸው ጉዳዮች መፍትሔ ለመፈለግ የግድ ተቆጣጣሪው ላይ ብቻ እምነት መጣልና የእርሱን ዕርምጃ መጠበቁ ብቻ አይበቃም፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆንም አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየዘርፉ ተቆጣጣሪ የምንላቸው ተቋማት እንደመስቀል ወፍ በዓመት አንዴ ብቅ የሚሉና ከበርካታ ወንጀሎች አንድና ሁለት ድርጊቶችን ብቻ አገኘን የሚሉ ናቸው፡፡ ጉልበትና አቅማቸው ከተሰጣቸው ኃላፊነት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ በእነሱ ላይ ብቻ እምነት መጣሉ ብዙ አያራምድም፡፡ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ ግድ ይላል፡፡ ቢሆንልንማ እነዚህ ተቋማት ጉልበት ቢኖራቸው ምኞታችን ነበር፡፡ ሆኖም እነሱ አቅም እስኪፈጥሩ ድረስ እንጀራ አቅራቢዎች በተለይም ተረካቢዎች የእንጀራ አዘገጃጀቱና ምንጩን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ሌላው ቢቀር በስመ እንጀራ ለገበያ የሚቀርበው ‹‹እንጀራ›› ከንፁህ ጤፍ ስለመዘጋጀታቸው ማረጋገጫ ሊሰጥ የሚችል አካል ሊኖር ይገባል፡፡

በነገራችን ላይ እንጀራ ከጤፍ ብቻ የሚዘጋጅ አይደለም፡፡ ከገብስም ሆነ ከሌሎች የሰብል ዓይነቶች ይዘጋጃል፡፡ ዋናው ግን ጤፍ ነው፡፡ ዛሬ በየመንደሩ የምንሸምተውም ሆነ ታች ካለው ምግብ ቤት እስከ ከፍተኛ ሆቴሎች የሚቀርብልን እንጀራ ከንፁህ ጤፍ የተዘጋጀ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም፡፡

በእንጀራ ግብይት ዙሪያ ያለው ችግር የጥራትና አዘገጃጀት ብቻ አይደለም፡፡ የመሸጫ ዋጋው ሁሉ በችግር የታጨቀ ነው፡፡ ጤፍን ከሌላ እህል ጋር ቀላቅሎ የተዘጋጀውም እንጀራ፣ አይገኝም እንጂ በንፁህ ጤፍ የሚዘጋጅ እንጀራ፣ ከጥቁርና ከሰርገኛ ጤፍ ተዘጋጅቷል የተባለው እንጀራ፣ ሁሉም ዋጋው አንድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሰጋቱራ ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ ሲቀርብ የነበረው እንጀራ ዋጋው ያው ነው፡፡ ነገር ግን የጥቁር ጤፍና የነጭ ጤፍ ዋጋ የተለያየ ከመሆኑ አንፃር እንደተዘጋጀበት የጤፍ ዓይነት የእንጀራ ዋጋውም ሊለያይ አይገባም ነበር? ስለዚህ እንጀራን እንቆጣጠር ከተባለ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች መታሰብ አለባቸው፡፡ እንጀራ ዝግጅት ስለሚለያይም ለገበያ የሚቀርበው እንጀራ ከንፁህ ጤፍ መዘጋጀቱ ከተረጋገጠ ይህንን ያህል ዋጋ ይሸጣል ይባል፡፡ ከጥቁር ጤፍ የተዘጋጀው ደግሞ ይህን ያህል፤ ጤፍን ከሌላ ሰብል ዱቄት ጋር ተደባልቆ የተዘጋጀ ከሆነም ይህንን ያህል ዋጋ አለው ተብሎ ሸማቹ መረጃ ኖሮት በአቅሙና በፍላጐቱ መሠረት እንዲሸመት ዕድል ይሰጠው፡፡ በስመ እንጀራ የሚሠራው ሸፍጥም ይቁም፡፡ ቁጥጥር ይደረግበት፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት