Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀል ኮንትራክተሮች የነገሡበት የ5.6 ቢሊዮን ብር የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ ቢሊዮኖች ዋጋ ያላቸው የመንገድ ግንባታ የኮንትራት ስምምነቶች የሚፈፀምበት የቀድሞ አውራ ጐዳና የአሁኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ጠባብ አዳራሽ ባለፈው ሐሙስ ከወትሮ በተለየ ተጨናንቋል፡፡

በዚህች ጠባብ አዳራሽ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንድ ቀን የሚደረጉ የኮንትራት ስምምነቶች ከሦስት ወይም ከአራት አይበልጡም ነበር፡፡ በሐሙሱ የመንገድ ግንባታ የኮንትራት ስምምነቶች ግን በአንድ ጊዜ 5.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ኮንትራቶች ተፈርመዋል፡፡

የዕለቱን ኮንትራት ስምምነቶች የተለየ ያደረገው ዋነኛ ክስተት ደግሞ ሰባቱንም የመንገድ ፕሮጀክቶች ጨረታ ያሸነፉትና ግንባታውን ለማካሄድ ከባለሥልጣኑ ጋር ኮንትራት የተፈራረሙት የአገር በቀል ኮንትራክተሮች መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተከታታይ የሚፈረሙ ኮንትራክተሮች የውጭ ኮንትራክተሮች የሚካተቱበት የነበረና በሰባት ተከታታይ ጨረታዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች አሸናፊ ሆነው ስለማያውቁ የዕለቱን የግንባታ ስምምነቶች የተለየ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡

626 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸው እነዚህ ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሁለቱን የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ጨረታ አሸናፊ የሆነው የሱር ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ እንደገለጹት፣ በዕለቱ የተፈረሙት ኮንትራቶች እስከዛሬ ባልታየ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አሸናፊ በመሆናቸው ተደስተዋል፡፡ ከእርሳቸው ኩባንያ አሸናፊነት የበለጠ ይህንን ያህል አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሥራዎችን መረከብ መቻላቸው ልዩ ስሜት የፈጠረባቸውና ባለሥልጣኑ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ለማፍራት ያደረገው ጥረት ውጤት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይም ፕሮጀክቶች ያሸነፉት የአገር በቀል ድርጅቶች መሆናቸው መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ባለፉት 21 ዓመታት መንግሥት በመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ ለአገር በቀል የሥራ ተቋራጮችና ለባለሙያዎቻቸው በፈጠረው ዕድል ነው ብለዋል፡፡ በተከታታይነት በሰጠው የአቅም ግንባታ ፕሮግራም እንዲሁም የዕውቀትና የክህሎት ሽግግር ፕሮግራሞች ውጤታማነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ የአገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ድርጅቶችን ማሸነፍ መጀመራቸው አገራዊው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የማስፈጸም አቅም አድጎና የአገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን አሟልቶ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለማየት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በር የከፈተ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡  

በአጠቃላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ነግሰውበታል በተባለው የሐሙሱ የሰባት መንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ስምምነቶች ውስጥ ሱር ኮንስትራክሽን ከሰባቱ ፕሮጀክቶች ሁለቱን ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመገንባት የሚያስችለውን ውል ተፈራርሟል፡፡

ሱር ኮንስትራክሽን በጨረታ አሸናፊ የሆነባቸው ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች በአማራ ክልል የሚገኘው ከሶሮቃ-አብረሃጂራ-አብደራፊ እና ከአይከል-ዙፋን-አንገረብ ድረስ ያለውን መንገድ ነው፡፡ ሱር 92 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን የሶሮቃ-አብረሃጂራ-አብደራፊ መንገድን ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 1.43 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ለሱር ኮንስትራክሽን የተሰጠው ሌላው የመንገድ ሥራ ደግሞ ከአይከል-ዙፋን-አንገርብ ድረስ ያለው 69 ኪሎ ሜትር መንገድ 1.95 ቢሊዮን ብር ዋጋ በመስጠት የጨረታ አሸናፊ ሆኖ የኮንትራት ስምምነት ሊፈጽም ችሏል፡፡

እንደ ሱር ሁሉ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ጨረታን አሸናፊ የሆነው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ በአማራ ክልል ውስጥ የሚያልፈውን የበለስ-መካነ ብርሃን 39 ኪሎ ሜትር መንገድና በአፋር ክልል የሚገነባውን የአዋሽ-ሚሌ (ኮንትራት አራት) 74 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ የአዋሽ ሚሌን መንገድ በ381.8 ሚሊዮን ብር፤ የበለስ-መካነ ብርሃንን መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ደግሞ በ1.01 ቢሊዮን ብር ለመገንባት የኮንትራት ውል ፈርሟል፡፡

መንግሥታዊው አገር በቀል ኩባንያ ሆኖ የተመዘገበውና እንደ አዲስ ተዋቅሮ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን ኮንትራት ፈርሟል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንዲገነባ የተሰጠው መንገድ ከአዋሽ ሚሌ (ኮንትራት ሦስት) የሚዘልቀውን 75 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ይህንንም መንገድ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 440 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

የኮንትራት ስምምነቱን የፈረሙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለመስቀል ተፈራ ኮርፖሬሽናቸው ወደ ሥራ ከገባ በሦስት ወር ልዩነት የመጀመሪያቸው የሆነውን የመንገድ ሥራ መረከባቸው በኮርፖሬሽናቸው መልካም ዕድል ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ቀሪዎቹን ሁለት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ለመገንባት አሸናፊ የሆኑት ደግሞ ማርካን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ዮናታን አብይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የተባሉ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡

ሁለቱም ኮንትራክተሮች ከባለሥልጣኑ የመንገድ ሥራ ግንባታ ኮንትራት ውል በሚፈጸምበት የባለሥልጣኑ አዳራሽ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ይህም ከባለሥልጣኑ የመንገድ ሥራ ግንባታ ለማከናወን ይችላሉ ተብለው ከተመረጡ ወደ መቶ ከሚጠጉ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ሰንጠረዥ ውስጥ የመግባት ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡

በዕለቱ የፈረሙት ኮንትራት በጨረታ አሸናፊ የሆኑበት ሥራና ማሸነፊያ ዋጋም ለሥራው የመጀመሪያቸው መሆኑን ያመላከተም ይመስላል፡፡ ማርካን ከባለሥልጣኑ የተረከበው የመጀመሪያው ሥራ ከአዲስ-ሞጆ-መቂ ድረስ የሚዘልቀውን የ131 ኪሎ ሜትር መንገድ ከባድ የጥገና ሥራ ነው፡፡

ማርካን ይህንን ከባድ የጥገና ሥራ ለማከናወን የጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 210.31 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ማርካንን ወክለው የኮንስትራት ስምምነቱን የፈረሙት የማርካን ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ግዛው፣ ይህ ዕድል ለኩባንያቸው ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ሰብ ኮንትራት ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ አሁን አሸናፊ የሆኑበትን ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡  ለባለሥልጣኑ ሥራ የመጀመሪያ የሆነው ዮናታን አብይ ጠቅላላ ሥራ የተባለው ድርጅት አሸናፊ የሆነው የመቂ ሻሸመኔ-ሐዋሳ ድረስ ያለውን 146 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ መንገዱን በ197.1 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ውል ፈጽሟል፡፡ በዕለቱ የኮንትራት ውል የፈጸሙት ኮንትራክተሮች የተረከቡትን ሥራ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች