Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሪያው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች በኢትዮጵያ የማምረቻ ቦታ ተረከበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በአዳማ 200 ሔክታር መሬት ላይ የሚንጣለል የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ ይገነባል ተብሏል

የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ያዋንግዋን ኮርፖሬሽን፣ በኢትዮጵያ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለማምረት የሚያስችለው ቦታ መረከቡን አስታወቀ፡፡ 

በባንግላዴሽ፣ በቬትናም እንዲሁም በኤልሳልቫዶር የማምረቻ ፋብሪካዎችን እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ በመትከል እየሠራ የሚገኘው ያንግዋን ኮርፖሬሽን፣ ከባንግላዴሽ ፋብሪካው ብቻ ኤክስፖርት በማድረግ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በማካበት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ የተጣራ ሀብት የኢትዮጵያን አጠቃላይ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚሸፍን ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ የሚገጠሙ ማሽነሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ትዕዛዝ መስጠቱን በተለይ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የያንግዋን ኮርፖሬሽንና የኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ኪያክ ሱንግ ፣ ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለማምረቻነት ከተረከበው በተጨማሪ፣ በአዳማ ከተማ የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ በ200 ሔክታር መሬት ላይ መገንባት ዋናው ዓላማው ነው፡፡ መንግሥት መሬቱን ለያንግዋን ቢያዘጋጅም፣ መደበኛና የመግባቢያ ስምምነቶችን ማድረግ ገና የሚከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን ሱንግ ተናግረዋል፡፡

በአዳማ እንዲገነባ የታቀደው የኢንዱስትሪ ፓርክ ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት እንደሚያስችለው አስታውቀው፣ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ለኮሪያ አምራቾች የማምረቻ ቦታ የሚያገልግል ይሆናል ብለዋል፡፡ ይኼም ለያንግዋን ከርፖሬሽን ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች እንዲያቀርብ ለማመቻቸት ታስቦ ነው፡፡

‹‹የምንከተለው ሞዴል በተቻለን መጠን ሁሉንም በራሳችን ለማምረት መቻል ነው፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ ማሽነሪዎች፣ አክሰሰሪዎችና ሌሎችም ጥሬ ዕቃዎች በኮሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚታቀፉ ኩባንያዎች ይመረታሉ ብለዋል፡፡ ይህ የሚደረገው በውጭ ጥሬ ዕቃዎችና መለዋወጫዎች ላይ ጥገኛ መሆን የኩባንያቸውን የማምረት አቅም የሚገድብ በመሆኑ ከዚህ ለመላቀቅ እንደሆነ ሱንግ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ማብራሪያ ከሆነ ያንግዋን ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማልማት ልምድም አለው፡፡ የራሳችንን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመገንባት ሞዴል እንከተላለን ያሉት ሱንግ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነው፡፡ ይኼም ሆኖ ትክክለኛው የኢንቨስትመንት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የኮሪያው ግዙፍ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ፣ ሌሎች ኩባንዎችም በራስ መተማመኑ ኖሯቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽናቸው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለንግድ ሥራ ቢሆንም ከዚህም በላይ ግን የኮሪያ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የበኩላቸውን ለማበርከት ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው መምጣት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ ኢትዮጵያውያን በኮሪያ ጦርነት ወቅት ለዋሉት ውለታና ለከፈሉት መስዋዕትነት መታሰቢያም እንዲሆን ጭምር ነው በማለት ሊቀመንበሩ አብራርተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በጠቅላላው በወጪ ንግድ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ስለዚህም ኤክስፖርት በሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያተኮረ የመንግሥት አገልግሎት ማቅረብ በጣም ወሳኝ ነው፤›› ያሉት የያንግዋን ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር፣ ፍጥነትና የዋጋ ተወዳዳሪነት ኤክስፖርት ለሚያደርግ አምራች ሁለቱ ቁልፍ ነገሮች ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ለወጪ ንግድ የሚውሉ ሸቀጦችን ለሚያመርቱ ኩባንያዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ወደ ባንግላዴሽ በገባንበት ጊዜ ወደ ውጭ ለመላክ ስንዘጋጅ የነበርነው እኛ ብቻ ነበርን፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የ25 ቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ ገንብታለች፡፡ እኛም በዚያ ካለው ፋብሪካ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ወደ ውጭ ለመላክ እየተቃረብን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ሲገልጹም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ያህል ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘት እንደቻሉና በኢትዮጵያ ለኮሪያ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚደረገው አቀባበል የሚያበረታታ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡ ከ80 ያላነሱ የኮሪያ ኩባንያዎች በሁለቱም ስብሰባዎች ወቅት መገኘታቸውንና እንዲህ ብዛት ያለው የንግድ ልዑክ ለመጀመርያ ጊዜ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ሲያሳይ አዲስ ክስተት ሆኖ እንዳገኙት አልሸሸጉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች