Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለ2009 በጀት ዓመት ለማከናወን ላቀዳቸው የተለያዩ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችና ለተያያዥ ክንውኖች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ጥያቄ ማቅረቡ ተጠቆመ፡፡

ከአገሪቱ የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የሚባለውን በጀት በማግኘት የሚታወቀው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ለ2009 በጀት ዓመት አቅርቧል የተባለው የበጀት ጥያቄ በ2008 በጀት ዓመት ከተፈቀደለት በጀት ጋር በንፅፅር ሲታይ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ በ2009 በጀት ዓመት ከ69 በላይ የሚሆኑ ትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቋል፡፡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶችም በቅርቡ ጨረታ በማውጣት ወደ ሥራ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2008 በጀት ዓመት የተፈቀደለት በጀት 33 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለ2009 በጀት ዓመት ያስፈልገኛል ብሎ ያቀረበው በጀት ሊፈቀድ የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያፀድቀው ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የበጀት ጥያቄውን በመመልከት በቂ ነው ብሎ ያመነበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርበው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በጀቱን ሙሉ ለሙሉ ሊያፀድቀው ወይም ማስተካከያ ሊያደርግበት ይችላል፡፡

ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው በአሁን ወቅት በአጠቃላይ የ171 ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን እያስተዳደረ ነው፡፡

ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የ20 ፕሮጀክቶች ግንባታዎች በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት የ15,183 ኪሎ ሜትር መንገዶች ግንባታና የጥገና ሥራዎችን ማከናወኑንም ባለሥልጣኑ ይገልጻል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች