Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄን በመጀመሪያ ለክልል ማቅረብ እንደ ግዴታ ሊቀመጥ ነው

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄን በመጀመሪያ ለክልል ማቅረብ እንደ ግዴታ ሊቀመጥ ነው

ቀን:

– የጠያቂውን ማኅበረሰብ አምስት በመቶ ፊርማ ማሰባሰብ ያስፈልጋል

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት፣ የክልል መፍትሔን አሟጦ የመጨረስ ሕጋዊ ግዴታ ሊቀመጥ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባርን ለመዘርዘር ተሻሽሎ የተረቀቀው አዋጅ እንደሚያስረዳው፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የመብት ጥያቄ በማንኛውም ማኅበረሰብ ሊቀርብ እንደሚችል፣ ነገር ግን ይህ ጥያቄ ለፌዴሬሽን ከመቅረቡ በፊት የክልል መፍትሔዎችን መጠቀም ግዴታ መሆኑን በረቂቁ አዋጅ አንቀጽ 27 ላይ ሠፍሯል፡፡

‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የመብት ጥያቄ ወደ ምክር ቤቱ የሚቀርበው በክልሉ በሚገኙት የተለያዩ የመስተዳደር እርከኖች ቀርቦ አጥጋቢ መፍትሔ ያልተሰጠው መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፤›› ይላል የረቂቁ ድንጋጌ፡፡ ክልሎችም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የተመለከቱ ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መወሰን እንደሚኖርባቸውም የሚገልጽ የጊዜ ገደብ በረቂቁ ተቀምጧል፡፡

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የመብት ጥያቄዎች የሚባሉትም ማንኛውም ማኅበረሰብ ማንነቴ አልታወቀልኝም ብሎ የሚያነሳው ወይም ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ቋንቋዬን፣ ባህሌንና ታሪኬን የማሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልኝም፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብቴ አልተከበረም፣ ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት አድልኦ ተፈጽሞብኛል የሚል እምነት ካደረበት ክልላዊ አስተዳደሩን ጠብቆ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሊቀርብ የሚችል መሆኑን ይገልጻል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ለክልል አስተዳደር አካላት መቅረብ የሚችል ቢሆንም፣ እንደ ጥያቄ አቅራቢው አካል ፍላጎት እንጂ በሕግ የተገደበ አልነበረም፡፡

ይህንን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትም የተጭበረበረ ወይም እውነተኛ ያልሆነ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በአሁኑ ወቅት እየተበራከተ መምጣቱ እንደሆነ፣ ሕጉን ካመነጨው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡

የክልል መስተዳድር አካላት ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች ከኃላፊነት በሚነሱበት ጊዜ እውነተኛ ያልሆነ የማንነት ጥያቄን በማንሳት አገርን የማወክ፣ ማኅበረሰቦችንም የመበጥበጥ ሁኔታ እየተለመደ መምጣቱ ሌላኛው ምክንያት ተደርጐ ተወስዷል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ኃላፊነትም በሕገ መንግሥቱ የተጣለበት በመሆኑ፣ ሁለቱንም ኃላፊነቶች ለመወጣት እንደሚያስችለው ተገልጿል፡፡

የክልል መፍትሔን አሟጦ መፍትሔ ያላገኘ ወይም ለክልል መስተዳደር አካላት ቀርቦ በሁለት ዓመት ውስጥ መፍትሔ ያላገኘ ጥያቄ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀርብ እንደሚችል በረቂቁ ላይ ተቀምጧል፡፡

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርበው ጥያቄ በጽሑፍ መሆን እንደሚገባው፣ ጥያቄውም የነዋሪው ማኅበረሰብ መሆኑን ለማመልከት እንዳስፈላጊነቱ ከነዋሪው ወይም ከማኅበረሰቡ አባላት ቢያንስ አምስት በመቶ የስም ዝርዝር ፊርማና አድራሻ የያዘ፣ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ጠያቂውን ማኅበረሰብ በመወከል ጥያቄ ባቀረበው የመስተዳድር አካል ባለሥልጣን የተፈረመና ማኅተም ያረፈበት መሆን እንደሚገባውም በረቂቁ ተካቷል፡፡

በተጨማሪም ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ የሚመጡ ከጠያቂው ማኅበረሰብ ስለመወከላቸው በቂ ማረጋገጫ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሚያደርገው ጥናት ውጤት መሠረት ጠያቂው ማኅበረሰብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) የሠፈሩትን የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ የተዛመደ ህልውና፣ በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ መሆናቸውን የመሳሰሉት መሟላታቸውን ካረጋገጠ፣ የሕዝቡ ፍላጎት በሕዝብ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንደሚያስፈጽም በረቂቁ ተገልጿል፡፡

በረቂቁ ላይ የተወያየው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ረቂቁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...