መርካቶ በርበሬ ተራ አካባቢ የሚገኘው ከረዩ ሠፈር አብዛኞቹ የሚገኙ ቤቶች እንደ መጋዘን በቆርቆሮ የተሠሩና እርስ በርስ ተደጋግፈው የቆሙ ናቸው፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች ወዲያና ወዲህ የሚሉባቸው ከአንድ ሰው በላይ ማሳለፍ የማይችሉ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎች ኮሪደሮች ብዙ ጉድ የያዙ ናቸው፡፡ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ሳይቀር ደለል ሠርቶ የሚተኛባቸው እንደ ልብ ለመረማመድ የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡
መፈናፈኛ ቦታ በማታውቀው ጠባብ መተላለፊያ መንገድ ላይ ወ/ሮ አፀደ ደሳለኝ ቁጢጥ እንዳሉ በሳፋ ልብስ ያጥባሉ፡፡ 60 ዓመቴ ነው ቢሉም ኑሮ የፈተነው ገፃቸው የ90 ዓመት አዛውንት አስመስሏቸዋል፡፡ እንደልባቸው መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ አንዳንዴ በቆሙበት የወደቁባቸው ጊዜያትም ብዙ ናቸው፡፡ ዓይናቸውም ደክሟል፡፡ በአንድ ወቅት የሰባት ልጆች እናት የነበሩት ወ/ሮ አፀደ፣ ከድፍን አገር ሰው ሞት በእሳቸው ልጆች የፈረደ ይመስል አንዲት ልጅ ብቻ እስክትቀር ተመላልሶ ልጆቻቸውን ነጥቋቸዋል፡፡
የሚተዳደሩበት ይህ ነው የሚባል ገቢ ባይኖራቸውም ልጆቻቸው ይደግፏቸው ስለነበር ኑሮ እንዳሁኑ ከባድ አልነበረም፡፡ ተንቀሳቅሰው መሥራት በማይችሉበት በዚህ ወቅት ኑሮ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲከብዳቸው አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉም አራት የልጅ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት ወድቆባቸዋል፡፡ እንደ ማድቤት ባረጀ ቆርቆሮ በተሠራው ቤታቸው ተጫውተው ያልጠገቡ፣ ገና ድክ ድክ የሚሉ ሕፃናት ውርውር ይላሉ፡፡
አዲስ ዓመት ሊገባ አምስት ቀናት ብቻ የቀሩት ቢሆንም (ያነጋገርናቸው ነሐሴ 30 ነው) ቤት እንኳ ለማዘጋጀት አቅሙ ሞራሉም አልነበራቸውም፡፡ ከወለሉ ብዙም በማይርቀው ጣራው ላይ የተለጣጠፈው የሶፍትና የፊኛ ጋጋታም አዋራ ጠጥቷል፡፡ እሱኑ ላለፈው የገና በዓል የተዘጋጀ መሆኑን ዓይቶ መገመት አይከብድም፡፡ በአዲስ ዓመት ሌላ ዲኮሬሽን ማዘጋጀት አይጠበቅኝም ያሉ ይመስላል፡፡
መተላለፊያ ላይ መንገድ ዘግተው እንደተቀመጡ የሚያንጨፈጭፉት ልብስ አጠገብ በዛ ያለ የሚጥሚጣ ቃሪያ አስጥተዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ ዓውደ ዓመትን ደግሰው መቀበል እንደማይችሉ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በዓውደ ዓመት መቃረቢያ የለመዱትና ተስፋ ያደረጉት አንድ ነገር አለ፡፡ መርካቶ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በየቀኑ ከሚያገኙት ገንዘብ አንድ ብር ወደ መዋጮ ሳጥን ይወረውራሉ፡፡ ይህ የሚሰበሰበው አንድ ብር ተጠራቅሞ በተወሰኑ ጊዜያት በተለይም በዓውደ ዓመት ከሰው እኩል ሆነው እንዲያሳልፉ እንደ ወይዘሮ አፀደ ያሉ አቅመ ደካሞችን ይረዷቸዋል፡፡
በአንድ ወቅት ዓውደ ዓመትን የሚያሳልፉበት ሁኔታ በድህነት ምክንያት ቢቀየርም የለመዱት እንዳይቀርባቸው ወጣቶቹ የቻሉትን ያህል ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ፕሮግራም ያስጀመረው እዚያው መርካቶ አካባቢ በርበሬ በረንዳ ተወልዶ ያደገው አርቲስት ዳንኤል ታምራት (ዳኒ ዳና) ነው፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ኑሯቸውን በከባድ ድህነት የሚመሩ ነገር ግን ለልመና ወደ ጎዳና ያልወጡ ምስኪኖችን እየመረጡ ይረዳሉ፡፡ በቋሚነት የሚረዱበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ጀምሮ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡
ይህ ፕሮግራም ከተጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በየበዓላቱ የሚረዱ ሰዎች ቁጥርም በዚሁ መጠን አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ እያለ መጥቶ አሁን 150 ደርሷል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች በተለይ አዛውንቶች በአብዛኛው ድጋፍ የሚሹ ቢሆንም የሚረዱት ከውስጥ እየመረጡ የባሰባቸውን ነው፡፡ ባለው የአቅም ውስንነት አንዳንድ ጊዜ የሆኑ በዓላትን ለመዝለል እስከ ማቅማማት ይደርሳሉ፡፡
እንቅስቃሴያቸውን የሚያውቁ አንዳንዶች እነሱን ሐሳብ በገባቸው ሰዓት ድንገት ደርሰው እጥፍ ድርብ አድርገው በዓይነት አልያም በገንዘብ ያንበሸብሿቸዋል፡፡ አንዱ ስልክ ደውሎ ኑ እንቁላል በካርቶን ውሰዱ ሲል፣ አንዱ ደግሞ ለወራት ያጠራቀሙትን ገንዘብ የሚስተካከል ብር እንኩ ይላቸዋል፡፡ አንዳንዴም ደግሞ በተቃራኒው ገንዘብ አጥሯቸው የሚያደርጉትን እስኪያጡ ይቸገራሉ፡፡ የከረዩ ሰፈር ነዋሪዎችን ችግር ዓይቶ ቤቱ የሞላም ሰው ቢሆኑ ማዘኑ አብሮ መቸገሩ አይቀርምና ዳንኤልና ጓደኞቹም እንዲሁ ይከፋቸዋል፡፡
ለሌሎች ችግር መድረስን ሥራዬ ያሉት የመርካቶ አካባቢ ወጣቶችም ከበዓላት ዋዜማ አንድ ቀን ቀደም ብለው ዘይት፣ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ እንቁላል፣ ዶሮ ሸምተው በየምስኪኖች ቤት ዘው ይላሉ፡፡ ለዓመታት የኖሩበትን የድህነት ሕይወት መቀየር ባይችሉም ከሰው እኩል የሚሆኑበትን አንድ ቀን ይሰጧቸዋል፡፡ ይህ የወጣቶቹ ቸርነት የወረት ሳይሆን ለዓመታት የዘለቀ በጎነት ነውና እንደ ወ/ሮ አፀደ ያሉ ችግርተኞች የበዓል ስጦታቸውን የሚጠብቁት ይቀርብናል ሥጋት ሳይገባቸው በሙሉ ተስፋ ነው፡፡
ብዙ አዳዲስ፣ አስደሳችም አሳዛኝ ክስተቶች የታዩበት፣ ብዙ ሰበር ዜናዎች የተስተናገዱበት፣ ወዲህ ታሪክ የሚጋሩ ነገር ግን አጋጣሚ እንደ ጠላት እንዲተያዩ ያደረጋቸው አንድ ሆነው በአብሮነት የደመቁበት፣ ወዲያ ደግሞ ጎረቤታሞች ጦር የተማዘዙበት ተቃርኖዎች የበዙበት በአሉታዊም ይሁን አወንታዊ ጎኑ ከሌሎቹ ዓመታት ደማቅ የሆነው 2010 ዓ.ም. ሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ያበቃል፡፡ መጪውን አዲሱን ዓመትም በጎ ተግባራትን በማከናወን ለመቀበል በተገባው ቃል ኪዳን መሠረት ሁሉም በየፊናው ላይ ታች እያለ ነው፡፡
13ኛው የጳጉሜን ወር ውስጥ የሚገኙትን ቀናትም የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመርና የአንድነት ቀን ተብለው ተሰይመዋል፡፡ በእነዚህ ቀናትና ቀደም ባሉት ልዩ ልዩ በጎ ተግባራት ሲከናወኑ ነው የከረሙት፡፡ በአንድ በኩል ከባድ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸውን ወገኖች መርጠው ቤታቸውን የሚያድሱ ወጣቶች ወዲያና ወዲህ ሲሉ ነበር፡፡
በከተማው ያለው የቤት ችግር በርካቶች የሚጋሩት ቢሆንም ካለው ውስን አቅም አንፃር እድሳት የተደረገላቸው ቤቶች በቁጥር ናቸው፡፡ ይኼንንም ለማድረግ ልዩ በጀት ተመድቦ አልያም የባለሀብቶች ጠንካራ ድጋፍ አግኝተው አይደለም፡፡ ቤቶቹ የታደሱት በየክፍለከተማው የሚገኙ ወጣቶች ማህበረሰቡን አስተባብረው ባገኙት መጠነኛ ድጋፍና ለሠራተኛ መክፈል ሳያስፈልጋቸው በደቦ ተጋግዘው እንጨት እያጋዙ፣ ሚስማር እየመቱ ነው፡፡ ዋናው አላማቸውም የተቸገሩን የመርዳት ባህል እንዲሰርፅ ማድረግ ነው፡፡
በአንድ ወገን ያሉት እንደዚህ ቤት ሲያድሱ ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ለሚቸገሩ ለችግርተኛ ቤተሰብ ልጆች ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ለማሟላት ይዘምታሉ፡፡ በአንድ ወገን ማጀታቸው እንዳይጎድል አስቤዛ ይሸምታሉ፡፡ አዲሱን ዓመት ምክንያት ያደረጉ በጎ ተግባራት የበዙበት የማኅበረሰቡን በተለይም የወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ልባምነትን ያጎሉ ‹‹የአሁን ጊዜ ትውልድ›› የሚለውን ወቀሳዊ ንግግር ትርጉም አልባ የሚያደርጉ ተግባራት እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡
‹‹የአዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት አገሬ›› በሚል መሪ ቃል በሚሌኒየም አዳራሽ የተዘጋጀው የመስጠት ፕሮግራምም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ያለፈው ሳምንት በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም የተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ማካፈል የቻሉ አዳራሹን በስጦታ ዕቃዎች ሞልተው ነበር፡፡ የሕፃናትና የአዋቂ ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች፣ ጥሬ ገንዘብ የለገሱ ብዙ ናቸው፡፡
ፕሮግራሙ በይፋ ከተከፈተ ሰኞ ማለዳ ጀምሮ ያላቸውን ጭነው እንኩ ሲሉ የሰነበቱት፡፡ በርካቶች ናቸው የሕፃናት ጫማዎች፣ ልዩ ልዩ የሕፃናት አልባሳት፣ የአዋቂ የአዘቦትና የክት አልባሳት፣ ቀበቶን ጨምሮ ሌሎች አዳራሹ ወለል ላይ ተዘርግተው በመልክ በመልካቸው እየተመረጡ እንደየ አግባባቸው ተደርድረዋል፡፡ ከላይ ደማቅ ሰማያዊ ካነቴራ የለበሱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የመጣውን እየተቀበሉ ባለው ላይ ይከምራሉ፡፡
የ22 ዓመቷ ወጣት ፅዮን ክንዴ ለተቸገሩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች አልባሳትን በማሰባሰብ ላይ ከነበሩት መካከል ነች፡፡ ‹‹ይኼንን ያህል ሰው መጥቷል ብሎ በቁጥር ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ ከጠዋት ጀምሮ በጣም ብዙ ሰው ነው የመጣው፤›› ትላለች፡፡ ለቀናት በሚቆየው በዚህ ዝግጅት ላይ ጊዜና ጉልበቷን ሰውታ ደፋ ቀና ስትል የሚከፈላት ባይኖርም በጎ በማድረጓ ደስተኛ ነች፡፡ የተሰበሰቡት አልባሳት ለማን እንደሚሰጡ ባታውቅም ለችግርተኞች መሰጠቱን ማወቋ በራሱ በቂዋ እንደሆነ ትናገራለች፡፡
በአዳራሹ አንድ ጥግ ደግሞ ጋደም እንዳሉ ደም የሚሰጡ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ ደም ለግሰው ከሚሰጣቸው ሚሪንዳና ብስኩት በስተቀር ሌላ የማይፈልጉ ወጣቶች እየተፈራረቁ ደማቸውን ሳያቅማሙ ሲሰጡ ለተመለከተ ደም መለገስ ቀላል እንደሆነ መረዳት ይችላል፡፡
‹‹በመስጠትሽ የማይቀንስ ነገር ሰጥተሽ የሰው ሕይወት ማትረፍ ደስ ይላል፤›› አለ ሳላህዲን መሐመድ አልጋው ላይ ጋለል እንዳለ፡፡ የ29 ዓመቱ ሳላህዲን ደም መለገስ ልማቸው ካደረጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ደም መለገስ የጀመረው የኮሌጅ ተማሪ እያለ ሲሆን፣ ዘንድሮ ሲለግስ 12ኛው ነው፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽ የተከፈተው የበጎ አድራጎት ፕሮግራም በተከፈተበት ቀን ነበር የተገኘው፡፡ ‹‹ከማውቀው ልጀምር ብዬ ነው፤›› የሚለው ሳላህዲን ካለው ላይ ለማካፈል ወደ ኋላ እንደማይል ይናገራል፡፡
በጎ ማድረግ፣ የተቸገሩን መርዳት ጎልቶ በከረመበት በዚህ ወቅት ለመስጠት የሚሽቀዳደሙ በዝተዋል ቢባል ማጋገን አይሆንም፡፡ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅትም ሕመምተኞች በነፃ ሕክምና የሚያገኙበትን የአንድ ቀን ዕድል አመቻችቻለሁ ብሏል፡፡ በዚያ ዕለት የሚታከሙ ሁሉ ለዲያሊስስ የሚከፍሉትን ገንዘብ ለሌላ ነገር እንዲያውሉ ታስቦ የተዘጋጀላቸው ዕድል ድንገት ሳያስቡት ተሰጥቷቸው የሚደሰቱበት ይሆናል፡፡
ባለው የመኖሪያ ቤት ችግር በዶሮ ቤት ውስጥ መኖር ብቸኛው አማራጯ የነበረውና ታሪኳ በርካቶችን ያሳዘነው ታዳጊም አለሁ የሚላት ያገኘችበት መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ ያንን ከመሰለ ከባድ ኑሮ ነፃ የሚያደርጋት በአንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጣት ታውቋል፡፡ እንዲህ ያለው በጎ ጅምር የአንድ ወቅት አጀንዳ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቅንነት፣ መልካምነት የገነባው የመደጋገፍ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ድጋፍ በአገር ልጅ ክንድ መተካት የሚያስችል ይኼንን ጅምር በባለቤትነት ሊያስቀጥል የሚችል አካል ቢኖርም ያሰኛል፡፡