Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቄራ የቀንድ ከብቶች ገበያ ማዕከል ትኩረት እንደሚያሻው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የከተማው አስተዳደር ተጨማሪ የፍጆታ ሸቀጦች እንደሚቀርቡ አስታውቋል

በዓውደ ዓመት ገበያው ትልቅ ድርሻ ከያዙት መካከል የቀንድ ከብት ግብይት የሚካሄድበትና ከ60 ዓመታት በላይ እንዳገለገለ የሚነገርለት የቄራ የቀንድ ከብት ገበያ ማዕከል፣ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የመንግሥትን ትኩረት እንደሚፈልጉ ተገለጸ፡፡

የግብይት ማዕከሉ የበግ፣ የፍየልና የከብት ግብይት እንዲካሄድበት ታስቦ ቢገነባም፣ በብቸኝነት እያስተናገደ የሚገኘው የበሬና የላም ግብይት ብቻ እንደሆነ የቄራ የቀንድ ከብት ግብይት ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተክኤ ግደይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ተክኤ እንደገለጹት፣ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የቄራ ግብይት ማዕከል መሠረታዊ የመሠረተ ልማት ችግሮች ይታዩበታል፡፡ ከብቶች በግብይት ማዕከሉ ተገቢነት ባለው መንገድ ውለው የሚያድሩበት ዕድል የላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከወራት በፊት ለከብቶች ውኃ ማጠጫ የነበረው የውኃ ማጠራቀሚያ ጋን (ታንከር) ቢቀደድም መተካት አልተቻለም፡፡ ጥያቄው በተደጋጋሚ ቀርቦም ምላሽ አላገኘም ተብሏል፡፡

ወደ ግብይት ማዕከሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገቡት የቀንድ ከብቶች በማደሪያ ዕጦት በየግለሰቡ ቤት በኪራይ እንደሚያድሩም አቶ ተክኤ ገልጸዋል፡፡ ማደሪያ የሚያከራዩ ግለሰቦች በአንድ ከብት እስከ 30 ብር ማስከፈል እንደጀመሩም ተጠቁሟል፡፡ ለከብቶቹ የሚውል በቂ የመኖና የውኃ አቅርቦት ችግርም፣ የአንጋፋው የገበያ ማዕከል መገለጫዎች ናቸው፡፡ የትራንስፖርት ችግር ብሎም ከብቶቹን በየቀኑ ከገበያ ማዕከሉ ወደ ግለሰቦቹ ማደሪያ በማጓጓዝ ሒደት የትራፊክ አደጋ እንደሚያጋጥም ተጠቁሟል፡፡ ትኩረት የተነፈገው የቄራ የገበያ ማዕከል ለዋጋ ጭማሪ የሚያጋልጡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ላይ ማስተካከያዎች ይፈልጋል፡፡

ይሁንና መንግሥት በአንድ ከብት የሚያስከፍለው ቀረጥ አሥር ብር እንደሆነና ከእያንዳንዱ ከብት ሽያጭ የ15 በመቶ ቫት እንደሚሰበስብ ታውቋል፡፡ በአንድ ቀን ገበያም በአማካይ ከሁለት ሺሕ ከብቶች እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበስብ አቶ ተክኤ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለማዕከሉ ተገቢው ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በ20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው የቄራ ገበያ ማዕከል በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ ሁለት ሺሕ የቀንድ ከብቶች ለግብይት እያቀረበ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ተከስቶ በቆየው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ የቀንድ ከብት ምንጭ ከነበሩ አካባቢዎች ወደ ማዕከሉ ይገባ የነበረበት አካሄድ ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ባለፈው ዓመት የገና በዓልና ከዚያም በፊት በነበሩት በዓላት በአብዛኛው ይቀርብ የነበረው የጎንደር አካባቢ የቀንድ ከብት ሀብት ነበር፡፡ ይሁንና እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ ከጎንደርና ከሐረር በሚገባ ሰንጋ ይጥለቀለቅ የነበረው የቄራ ገበያ በአሁኑ ወቅት ከጂማ፣ ከወለጋ፣ ከክብረ መንግሥት፣ ከባሌ፣ ከወላይታና ከሌሎችም እየገባ እንደሚገኝ አቶ ተክኤ አብራርተዋል፡፡  

በዋጋ ረገድም የተስተካከለ ሁኔታ እንደሚታይ ሲያብራሩም ከዚህ ቀደም እስከ ስምንት ሺሕ ብር የሚያወጣ አነስተኛ ከብት ማግኘት ከባድ እንደነበር፣ በአሁኑ ገበያ ግን ከስምንት ሺሕ ጀምሮ እስከ 30 ሺሕ ብር እየቀረበ እንደሚገኝ  አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አነስተኛ ከብት ከስምንት እስከ አሥር ሺሕ ብር፣ መካከለኛው ከ13 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ትልቅ የሚባለው ከብትም ከ20 እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ ባለው የዋጋ ክልል ሲሸጥ እንደከረመ ተገልጿል፡፡ ከክረምቱ ወዲህ በአማካይ እስከ 1,500 ብር የዋጋ ቅናሽ መታየቱን አቶ ተክኤ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የፍየልና የበግ ግብይትም የተረጋጋ የዋጋና የአቅርቦት መጠን እንደታየበት ቢገለጽም፣ የግብይቱ ሥርዓት በድርድር በሚወሰን ዋጋ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ትክክለኛውን የገበያ ዋጋ ከነጋዴውም ሆነ ከአቅራቢው ማግኘት ከባድ ለመሆኑ አንደኛው ማሳያ የቄራው የፍየልና የበግ ግብይት ነው፡፡ ግብይቱ የሚካሄደው በአብዛኛው ዋጋ በሚጠሩና በሚያስማሙ ‹‹ደላሎች›› ሲሆን፣ የፍየልና የበግ አቅራቢዎች ወይም ባለንብረቶች ዳር ቆመው ሲመለከቱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በዋጋ ረገድ በግ ከ1,500 ብር እስከ 4,500 ብር እንደሚሸጥ ተገልጿል፡፡ ፍየልም እንደ ደረጃው ከ2,500 እስከ 7,000 ብር እንደሚያወጣ ሻጮች ይናገራሉ፡፡ ዓምና አንድ ደህና የተቀለበ የፍየል ሙክት እስከ አሥር ሺሕ ብር ማውጣቱንም በትንግርት ያስታውሳሉ፡፡

በዓውደ ዓመት ገበያው ጭማሪ ከታየባቸው የምግብ ሸቀጦች መካከል እንቁላልና ቅቤ፣ በርበሬና ቅቤ፣ ሽንኩርትና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች ትልቁን ቦታ ይዘዋል፡፡ ሪፖርተር ሐሙስ ጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም. መጠነኛ ቅኝት ካደረገባቸው ገበያዎች አንዱ ሾላ ገበያ ነው፡፡ በሾላ ገበያ ወ/ሮ እልፍነሽ በቀለ የተባሉ ሸማች እንደገለጹት፣ በዋዜማው ግብይት ወቅት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ሽንኩርት ሰሞኑን ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ በኪሎ እስከ 15 ብር ያወጣ ነበር፡፡ ሆኖም በሰሞኑ የገበያ ውሎ እስከ 17 ብር እንዳወጣ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ግብይት አክሲዮን ማኅበር (ኢትፍሩት) መሸጫ መደብሮች አንድ ኪሎ ሽንኩርት በ20 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በሚታይበት ከፍተኛ የዕርድ ፍላጎት በሚታይበት የዘመን መለወጫ በዓል፣ በዚህ ጥሩ ዋጋ እንደታየበት ገበያተኞች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዶሮ ጥሩ ነው፡፡  በ250 ብር ገዝተናል፤›› በማለት የዶሮ ገበያው መረጋጋት እንደሚታይበት ወ/ሮ እልፍነሽ ገልጸዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ እልፍነሽ ሁሉ ወ/ሮ ታደለች ገመቹም በሾላ ገበያ ዶሮ ሲገበዩ ነበር፡፡ ትልቅ የሚባለውን ዶሮ 350 እንደገዙ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሁለቱም ገበያተኞች በቅቤ ዋጋ መወደድ ቅሬታ ገብቷቸዋል፡፡ ‹‹ቅቤ እንደ ጥራቱ ዋጋውም ይለያል፡፡ ከ250 እስከ 300 ብር እየሸመትን ነው፡፡ ከምናው ጋር ሲተያይ ምን የቀነሰ ነገር የለም፤›› በማለት ወ/ሮ እልፍነሽ ሲገልጹ፣ ወ/ሮ ታደለች በበኩላቸው፣ ጊዜው ክረምት እንደ መሆኑ የቅቤ ዋጋ መጨመሩ አሳማኝ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደረጄ አደሬ በሾላ ገበያ ቅቤ ነጋዴ ሲሆኑ፣ ከሰሞኑ የግብይት ውሎ በኪሎ እስከ 20 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ ለጋ ቅቤ እስከ 300 ብር፣ መካከለኛው እስከ 280 ብር እንዲሁም፣ በሳል የሚባለው ከ250 ብር ጀምሮ እንደሚሸጥ አቶ ደረጄ ገልጸዋል፡፡ አቶ ወልዴ ኃይሉም በቅቤ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ የቅቤ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸው፣ ከአቅርቦቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ዋጋው ሊጨምር እንደቻለ ይገምታሉ፡፡ በሾላ ገበያም ሆነ በሌሎች የግብይት ሥፍራዎች በእንቁላል ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በ3.50 ይሸጥ የነበረውን እስከ አምስት ብር አሻቅቦት ታይቷል፡፡ በጀሞና በቄራ አካባቢ ተባራሪ ነጋዴዎች አንድ እንቁላል ከ3.75 ብር እስከ 4.50 ብር ሲሸጡ ታይተዋል፡፡

ምንም እንኳ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ወቅት ገበያው የአቅርቦት ችግር እንደማይታይበት ቢነገርም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም እጥረት እንዳይፈጠር በሚል መነሻ ለገበያ እየቀረቡ ስለሚገኙ ምርቶች መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በተለይም በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እየገቡ በመሆኑ ጭምር የምርት እጥረትም ሆነ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በማለት፣ በከተማዋ አሥሩም ክፍላተ ከተሞች 117 ወረዳዎች የስንዴ ዱቄት፣ ስኳርና ዘይት ላይ ሲቀርብ በከረመው የአቅርቦት መጠን ኮታ ላይ ጭማሪ መደረጉን የንግድ ቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ ዮሱፍ አስታውቀዋ፡፡ በመረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ ከነበረው ኮታ ላይ እስከ ሦስት ኩንታል ስኳርና የስንዴ ዱቄት ጭማሪ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል 165,657 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 120 ሺሕ ኩንታል ስኳር፣ ሰባት ዮን ሊትር ዘይት 28 በላይ የሸቀጣ ሸቀጥ ቸርቻሪዎች አማካይነት ለከተማዋ ነዋሪዎች በየወሩ ሲሠራጭ እንደነበር ተገልጿል፡፡

(ለዚህ ዘገባ ዳዊት ቶሎሳ አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች