Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሃን ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለመቀየር የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል አለ

ኢሃን ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለመቀየር የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል አለ

ቀን:

ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ መመዝገቡን አስታወቀ

የተለየ ሐሳብ ይዞ መቅረቡን የሚናገረው የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) የፖለቲካ ፓርቲ፣ ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ከቆየችበት የአገዛዝ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለማሸጋገር፣ የሽግግር ጊዜና ተቋማት ያስፈልጓታል አለ፡፡

የኢሃን መሥራችና ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ፓርቲያቸው መላ ኢትዮጵያዊያንን ያስማማል ያለውን የሽግግር ሐሳብ አዘጋጅቷል፡፡ ከአገዛዝ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለመሸጋገር አራት ዋና ዋና ነገሮች እንደሚያስፈልጉ የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ በእውነት ይቅር ለመባባል የእርቅና የሽግግር ምክር ቤት፣ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ፣ የሽግግር ምክር ቤትና የባላደራ መንግሥት ወይም አስተዳደር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት ለተሠሩ የፖለቲካ ወንጀሎች ሒሳብ እየተወራረደ የሚሄድ ከሆነ የትም እንደማይደርስ የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ አገራዊና እውነተኛ እርቅ በመፈጸም ለጥፋተኞች የማያርያም መንገድ ሰጥቶ፣ አገሪቱ ወደፊት የምትሄድበትን የዕድገት ልማት ላይ መረባረቡ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የእርቅና ይቅር መባባል ምክር ቤት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› በማለት ሲጀምር፣ ‹‹ዜጎች ቦታ እንደሌላቸው ያሳያል›› የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ሌላው የተዛባ ግንኙነታችንን ለማረም›› ማለቱም የሚያሳየው የትግል ሰነድ መሆኑን ስለሆነ፣ ሕዝቦች ተስማምተውበት እንደ ቃል ኪዳን ሰነድ የሚጠቀሙበት ሕገ መንግሥት ለማድረግ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ምክር ቤት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥት ከመግቢያው ጀምሮ እንዴት እንደተቀረፀ መመልከቱም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሚቋቋሙትን ምክር ቤቶች የሚመራና የሚቆጣጠር እንደ ፓርላማ 547 መቀመጫ ያለው፣ ከሁሉም መዋቅሮች ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ከማንኛውም አድልኦና እኩይ ተግባር ነፃ የሆኑ ሰዎች ተመርጠው፣ ሕዝቡን በመወከል እንዲሠሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ይልቃል አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ፣ የአገር ደኅንነትና ሌሎች ሥራዎችን መሠራት ስላለባቸው ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ተመርጠው የባላደራ መንግሥት ወይም አስተዳደር መመሥረትም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተውታል፡፡

የሽግግር ተቋማቱ ‹‹እንዴት ይመረጡ?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሊቀመንበሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሰጥቶ በመቀበል መርህ ተነጋግረው ማቋቋምና የሚቆዩበትን ጊዜ አስቀምጦ እንዲሠራ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ተሳታፊ ያገባኛል ባይ ሆኖ መነሻ ሐሳብ ይዞ መቅረብ እንዳለበት ግን አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ይልቃል ፓርቲያቸው ኢሃን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመመዝገቢያ መሥፈርት አስፈላጊውን ሁሉ አሟልቶ ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አቅርቧል ብለዋል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 9(5) መሠረት ቦርዱ በደረሰው ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም፣ ምላሽ እንደነፈጋቸው ተናግረዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 9(7) መሠረት ደግሞ ቦርዱ ምላሽ ሳይሰጥ ሦስት ወራት ካለፈው ‹‹እንደተመዘገበ ይቆጠራል›› ስለሚል ከነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሃን ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ መመዝገቡን ሊቀመንበሩ አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳን ፓርቲው ሕጋዊ ሆኖ መመዝገቡ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ሰርተፊኬት ስላልተሰጣቸው በፓርቲው ስም የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ ማኅተም ማስቀረፅ፣ የተለያዩ ደረሰኞችን ማሳተምና ሕጋዊ ደብዳቤዎችን መጻጻፍ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ሕጋዊነታቸውን የሚያረጋግጠውን ሰርተፊኬት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...