የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጠቅላላ ጉባዔውን ከመስከረም 8 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በጅማ ከተማ ለማካሄድ መወሰኑ ተሰማ። ለተከታታይ ሦስት ቀናት በጅማ ከተማ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ኦሕዴድ መተዳደሪያ ደንቡን፣ በአሁኑ ወቅት የሚታወቅበትን መጠሪያውን እንዲሁም ዓርማውን ለመቀየር በሚቀርቡ የውሳኔ ሐሳቦች ላይ በመምከር ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅሞች የተደራጀ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ከመሥራት ውህደት መፍጠር እስከሚቻልበት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮችና በኢሕአዴግ እህት ድርጀቶች መካከል ሊኖር የሚገባውን ፖለቲካዊ ግንኙነት በተመለከተ መሪ አቅጣጫ ጠቅላላ ጉባዔው ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ከኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ ቀደም የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ ኦሕዴድ የሚለውን የድርጅቱን ስያሜ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚል ስያሜ ለመተካት የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል። ከመጠሪያው በተጨማሪም የሚገለገልበትን ዓርማ ለመለወጥ ሦስት ዓርማዎች ለውሳኔ ያቀረበ መሆኑን፣ የፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ የማያስፈልግ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበት ዓርማና መጠሪያ የፖለቲካ ተልዕኮን የማያመለክት፣ በግለሰብ ደረጃም ለተለያዩ የንግድ ተግባራት ለሚቋቋሙ መገልገያ በመሆኑ፣ ይኼንን መጠሪያ ለመቀየር አንደኛው ምክንያቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ድርጅት የሚለውን ስያሜ ለመተካት የተለመዱት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜዎች ማለትም ንቅናቄ፣ ትግልና ግንባር የሚሉት መጠሪያዎች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተግባራትን ከመግለጽ ይልቅ፣ ውስን የሆነ የፖለቲካ ተግባርንና የትጥቅ ትግልን የሚያመላክቱ በመሆናቸው ፓርቲ የሚለውን መጠሪያ መታሰቡ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበትን ዓርማ ለመቀየር ሦስት አማራጭ ዓርማዎች ሲቀርቡ፣ የአባ ገዳ ሥርዓት መገለጫ የሆኑትን ጥቁር፣ ቀይና ነጭ ቀለማት ከኦዳ ምልክት ጋር በተለያዩ ሦስት አቀማመጦች ለውሳኔ አቅርቧል፡፡ ይኼንኑ የውሳኔ ሐሳቦች ሰሞኑን የተሰበሰበው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመቀበል ለጠቅላላ ጉባዔው እንዲቀርብ ወስኗል።
የስያሜ ለውጡ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገሉ ሌሎች ፓርቲዎችን በአንድ ጥላ ሥር ለማምጣት የሚያስችል ቅድመ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሕዴድ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ኦሕዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ ለዓመታት ሲታገሉ ከነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ እንዳለው፣ ከተወሰኑት ጋርም የመጀመርያ ምዕራፍ ውይይቶችን ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ከነዚህም መካከል በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ተጠቃሽ ነው። በተለያዩ አገሮች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ሕዝብን የሚወክሉ ፓርቲዎች በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘት የምዝገባ ጥያቄ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለማቅረባቸውን ሪፖርተር ከቦርዱ ጽሕፈት ቤት ማረጋገጥ ችሏል።
በተያያዘ ዜና የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ጠቅላላ ጉባዔውን እንደሚያካሂድ ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ብአዴን በተመሳሳይ የመተዳደሪያ ደንቡን የማሻሻልና ዓርማውን የመቀየር፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለመለወጥ በቀረቡ የውሳኔ ሐሳቦች ላይ መክሮ የመጨረሻ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።
ቀሪዎቹ ሁለት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናቸው።