Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት ሪፖርት እያነጋገረ ነው

የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት ሪፖርት እያነጋገረ ነው

ቀን:

የመላ ኢትዮጵያውያን አሻራ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) አሟሟት ሪፖርት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን እንደሚያመላክት ፖሊስ ከገለጸ በኋላ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ በመስቀል አደባባይ በሚያሽከረክሩት መኪና ውስጥ ሞተው ከተገኙ በኋላ፣ የአሟሟታቸውን ዝርዝር ሪፖርት በሕዝብ ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ፣ ዓርብ ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በፖሊስ ይፋ የተደረገው ሪፖርት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የሚያመላክት በመሆኑ፣ በሕዝቡ ዘንድ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል፡፡ መንግሥት ቀጣይ ምርመራዎችን በማድረግ ስመኘው (ኢንጂነር) ራሳቸውን ያጠፉበትን ምክንያት እንደሚያሳውቅ ቃል ተገብቷል፡፡

በጠራራ ፀሐይ በመስቀል አደባባይ ሞተው የተገኙት ስመኘው (ኢንጂነር)፣ የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ የሚሠራው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥራ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆንና ሳሊኒ የጠየቀው ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ካሳ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር፣ የጻፏቸው ደብዳቤዎች አመላካች መሆናቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላለፉት 43 ቀናት (እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ) ‹‹ኢንጂነር ስመኘውን ማን ገደላቸው? ገዳያቸው በአስቸኳይ መነገር አለበት፣ ለምን ዘገየ?›› እና ሌሎች ጥያቄዎችን ሲያነሱ የከረሙ ቢሆንም፣ የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ራሳቸውን በራሳቸው መግደላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል፣ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ተኮላ አይፎክሩና የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ በጋራ እንደተናገሩት፣ ስመኘው (ኢንጂነር) የሞቱበትን ምክንያት ፖሊስ መጣራት ያለባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች፣ ጊዜ ወስዶ በማጣራትና አስፈላጊውን ትንታኔ በመስጠት ወደፊት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ቃል ይገባል ብለዋል፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ባደረገው ምርመራ፣ ኢንጂነሩ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ከሚመሩት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የግድቡን ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ የሚሠራው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የሥራ አፈጻጸሙ ግን በጣም ዝቅተኛ መሆኑ መሰንበቻውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ተደርጓል፡፡

የሥራ አፈጻጸሙን በመከታተል ክፍያ እንዲፈጸምለት ትዕዛዝ የሚሰጡት እሳቸው ከመሆናቸው አንፃርና የግድቡን ሲቪል ሥራ ሠርቶ ማጠናቀቁን የሚናገረው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የጠየቀው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ክፍያ ጭንቀት ውስጥ የከተታቸው መሆኑን፣ ከጻፉት ደብዳቤና ከመሞታቸው በፊት ያሳዩ የነበረው ባህሪ አመላካች እንደሆነ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ራሳቸውን መግደላቸው ከታወቀ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ለምን እንደዘገየ? በጥይት የተመቱበት የሰውነታቸው ክፍል በግራ ሆኖ ሳለ ሽጉጡ ወድቆ የተገኘው በስተቀኝ እንዴት ሊሆን እንደቻለ? እንዲሁም በመኪናው ውስጥ የተፈናጠቀ ደም ካለመታየቱም በተጨማሪ፣ የተወሰነ ጠብታ እንጂ በብዛት የፈሰሰ ደም ያልታየበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ኃላፊዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የደረሰው የሞት አደጋ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዎቹ፣ ምርመራውን በጥራትና በጥንቃቄ እንዲሁም በባለሙያዎች የታገዘ አድርጎ እውነተኛ መረጃ ከመስጠት አንፃር ዘገየ ሊባል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ጊዜ ተወስዶ ካልተሠራ እውነቱ ሊገኝ ስለማይችል የተለያዩ ምርመራዎች ሲደረጉ እንደነበርና ጊዜው ሲደርስ መገለጹን አክለዋል፡፡ ኢንጂነሩ ስለተመቱበትና ስለአወዳደቃቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለ የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ በቀኝ እጃቸው ተኩሰው የጥይቱ እርሳስ በግራ በኩል ወድቆ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ በመኪናው ውስጥ ደም ፈስሶ መገኘቱና ምቱ ወደ ውስጥ ስለሆነ ስለማያስታውቅ እንጂ ያለውን ቦታ ማዳረሱን ጠቁመዋል፡፡

በምርመራው ላይ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (FBI) የተሳተፈው ጉዳዩ ክብደት ስላለውና በኢትዮጵያ የምርመራ ኃይሎች ሊደረስበት ስለማይችል ስለመሆኑ ተጠይቀው፣ ኃላፊዎቹ የሰጡት ምላሽ ‹‹አይደለም›› የሚል ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የጣት አሻራ መመርመሪያ ማሽን አጠራጣሪ ውጤት ይሰጥ ስለነበር፣ ያንን በጥራት ለማወቅ ብቻ እንዲረዱ ተጠይቀው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሌላ የሠሩት ነገር እንደሌለ ግን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ በስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) አሟሟትና የምርመራ ሒደትን በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎች እንዳስረዱት፣ ኢንጂነሩ ራሳቸውን ያጠፉበት ሰርቲኤይት ኮልት ሽጉጥ፣ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስፈቅደው የተሰጣቸው ነው፡፡ በዚሁ ሽጉጥ ለመሞታቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተደረገ የአስከሬን ምርመራ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የእርሳስና የቀለህ ምርመራውም የሽጉጡ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በመኪናው ውስጥ ሁለት ሞባይሎችና ሁለት የታሸጉ የካኪ ፖስታዎች መገኘታቸውንና ተሽከርካሪውም በሾፌሩ ብቻ የሚቆለፍ (ሴንትራል ሎክ) እንደሆነ መረጋገጡንም  አክለዋል፡፡ ስመኘው (ኢንጂነር) በመኪናው ውስጥ ሞተው በታዩበት ወቅት ፖሊሶች ምናልባት ሕይወታቸው ካለ በማለት በቀኝ በኩል የምትገኝ ቀጭን መስታወት ሰብረው፣ መኪናውን በመክፈት ገብተው ሲያዩዋቸው ሕይወታቸው ማለፉን በማረጋገጣቸው፣ ባሉበት እንደተዋቸውና ቀጣይ ምርመራዎችን መቀጠላቸውንም አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነሩ ከመሞታቸው አንድ ቀን በፊት በመስቀል አደባባይ (የሞቱበት ቦታ ላይ) መምጣታቸውንና በዕለቱም እንዳገኛቸው የተናገረ ሕፃን ልጅ፣ ለጊዜው ያየው ነገር ካለ በሚል በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ ቢደረግበትም፣ እሳቸውን ከማየቱ ውጪ ሌላ ያየው ነገር እንደሌለ በመናገሩ መለቀቁን አስረድተዋል፡፡ ስመኘው (ኢንጂነር) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ በመገንባት ላይ ከሚገኘው የህዳሴ ግድብ ወደ አዲስ አበባ የመጡት፣ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. መሆኑንም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በተደረገ ስብሰባ ላይ መካፈላቸውን፣ ሐምሌ 18 ቀን ደግሞ ንፋስ ስልክ አካባቢ በሚገኘው የሜቴክ ጽሕፈት ቤት ሄደው እንደነበር ፖሊስ በምርመራ ማወቁን አስረድተዋል፡፡

በዚያው ቀን ወደ ቤታቸው የገቡት ከምሽቱ አራት ሰዓት መሆኑንና ትልቁን ልጃቸውን፣ ትምህርቱን እንዲያጠናና ጎበዝ እንዲሆን የስንብት ምክር መለገሳቸውንም ከልጁ መረዳታቸውን አክለዋል፡፡ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት ላይ አንድ ስኒ ቡና ጠጥተውና ልጆቻቸውን ተሰናብተው ከቤታቸው የወጡት ኢንጂነሩ፣ በማለዳ አንድ ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ወደ ቢሮአቸው መግባታቸውንም ከጥበቃ ሠራተኞች መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ስመኘው (ኢንጂነር) ሁለት ሾፌሮች እንዳሏቸው ኃላፊዎቹ ጠቁመው፣ አንደኛውን ሾፌር ጠርተው የታሸገ ፖስታ በመስጠት፣ ‹‹ለማን እንደምትሰጥ እነግርሃለሁ፤›› እንዳሉት፣ ነገር ግን ሳይነግሩት መቅረቱን እንደገለጸ ተናግረዋል፡፡ የመሥሪያ ቤታቸውን አትክልተኛም በመጥራት ሌላ ፖስታ ሰጥተው ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንዲያደርስ እንደላኩት፣ በሥፍራው ሲደርስ 2፡20 ሰዓት ላይ ደውሎ፣ ‹‹ለማን ልስጠው?›› ሲላቸው፣ ‹‹ጠብቅ እነግርሃለሁ፤›› እንዳሉትም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት 2፡21 ሰዓት ላይ ለጸሐፊያቸው ደውለው ወደ ቢሮ መምጣት አለመምጣቷን ሲጠይቋት፣ እንደምትመጣ ስታረጋግጥላቸው ሁለት የታሸገ ፖስታ እንዳስቀመጡላትና አንደኛውን ለልጃቸው ደውላ እንድትሰጥላቸው፣ አንደኛውን ለሷ መሆኑን እንደነገሯት ኃላፊዎቹ በምርመራ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነሩ ወደ መስቀል አደባባይ 2፡24 ሰዓት ላይ ተመልሰው ራሳቸውን ማጥፋታቸውንና መረጃው ለፖሊስ ከስድስት ደቂቃ በኋላ 2፡30 ሰዓት ላይ እንደተነገረም አክለዋል፡፡

መኪናው ውስጥ ከተገኘው ሁለት እሽግ ፖስታ ጋር በድምሩ ሰባት እሽግ ፖስታ መገኘቱንም አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ስመኘው (ኢንጂነር) ከጉባ ከመጡ ጀምሮ ያሳዩት የነበረው አለመረጋጋትና በደብዳቤው ውስጥ ካሰፈሩት የህዳሴው ግድብ ግንባታ አፈጻጸምና የወጣበት ከፍተኛ ወጪ  ሕዝብ ከሚጠበቀው ውጤት አንፃር ጭንቀት ውስጥ እንደገቡና ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደቻሉ አመላካች ነገር መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በተውት ደብዳቤ ላይ የጠቀሱት የሰው ስም ስለመኖሩ ተጠይቀው ማንንም እንዳልጠቀሱ፣ ነገር ግን በግድቡ ጭንቀት ወደ ውጭ ሊወጡ አስበው፣ በሁሉም ቦታ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ ‹‹ምን ምላሽ እሰጣለሁ?›› በማለት እንደተውት የሚጠቁሙ መረጃዎች መተዋቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ ቦምብ ፍንዳታን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ችግሩ ሲከሰት ቀላል ቢመስልም፣ ነገሩ ውስብስብ በመሆኑ እስካሁን ምርመራ በማድረግ የተገኘው ውጤት በፍርድ ቤት በኩል እየገለጹ መሆኑንና ምርመራው እስከሚጠናቀቅ እንደሚቀጥሉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ፣ ሾፌራቸውና ጸሐፊያቸው ግድያን በተመለከተም ተጠይቀው፣ ፍንጭ ከመገኘቱ በስተቀር ምርመራው ገና አለመጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...