የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በሚሠሩ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ተይዘው የነበሩ 199 ቤቶችን ቁልፍ፣ ለቤት አልባ ችግረኞች ዓርብ ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም. አስረከቡ፡፡
ቤቶቹ የተገኙት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡ የራሳቸውን ቤት በማከራየት በቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው አከራይተው ከሚኖሩ ነዋሪዎች ማጣራት ተደርጎ የተወሰዱ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
ቤቶቹ ለቤት አልባዎቹ የተሰጡት በዕጣ ሲሆን፣ ይህ አሠራር በሁሉም ክፍላተ ከተሞች እንደሚቀጥልም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡ ቤቶቹ በነባርና ታዋቂ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ስለሺ ስህን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባና በሌሎች አትሌቶችም እንደታደሱ ተገልጿል፡፡
አትሌት ደራርቱ፣ ‹‹የደሃ ደሃ ሰዎችን ተባብረን ቢያንስ ወደ ደሃ እንቀይራቸው፤›› በማለት ሁሉም ተባብሮ ወገኑን መደገፍ መርዳት እንዳለበት አሳስባለች፡፡
በእንቅስቃሴው ይሳተፋሉ ተብሎ የተጠበቁት በርካታ ባለሀብቶች ቢሆኑም፣ በሥፍራው የተገኙት ታዋቂው ነጋዴና ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ 500,000 ብር ለመስጠት በሕዝብ ፊት ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹እንደዚህ ያለ ጥርት ያለ አሠራር ከተጀመረ ጃኬቴን አውልቄ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ፤›› ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በፍል ውኃ አስተዳደር ፊንፊኔ አዳራሽ በተደረገው የቁልፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡