Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአዲሱ ዓመት ነባር ችግሮች

የ2010 ዓ.ም. ለሸማቾች በርካታ ፈተናዎች የጋረጡበትና በብዙ ውጣውረዶች የታለፈ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከስኳርና ዘይት አንስቶ በበርካታ የሸቀጥ ምርቶች ላይ የተፈጠረው የአቅርቦት ዕጥረት ሸማቹን ፈትኖታል፡፡ ሸመታን ስናስብ ልንዘነጋው የማንችለውና ችግሩ ያልተቀረፈው የስንዴ ዕጥረት ነው፡፡ ዕጥረቱን ተከትሎ የተፈጠረው የዳቦ አቅርቦት ችግርም አይዘነጋም፡፡

ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ ሲያቀርቡ የነበሩ ዳቦ ቤቶች በዱቄት ዕጦት የተነሳ ሆድ ጠብ የማይል ዳቦ የሸጡበት ዓመት ነበር፡፡ መጠኑን ቀንሰው ያቀረቡት ዳቦም ቢሆን በቅጡ ለበላተኛ ያልተዳረሰበት፣ የዳቦ ወረፋ መንገድ ያጣበበት ዓመት ነበር፡፡ ነጋዴዎቹም አይፈረድባቸውም፡፡ በድጎማ ሲቀርብላቸው የቆየው ስንዴ፣ በገበያ ዋጋ ካልገዙ በቀር እንደወትሮው ማግኘት ስላልቻሉ በገበያ ዋጋ ስንዴ ገዝተውና ዱቄት ፈጭተው ዳቦ የሚጋግሩበትን ሁኔታ በመፈጠሩ፣ መንግሥት በዚህን ያህል ዋጋ ዳቦ ሽጡ ብሎ ማስገደድ የሚችልበት አቅም አልነበረውም፡፡ በመሆኑም ዳቦ ቤቶቹ 1.50 ብርና ሁለት ብር ይሸጡት የነበውን ዳቦ በሦስት ብር እንድንገዛ አስገድደውናል፡፡

 የተፈጠረውን የስንዴ እጥረት ለመቅረፍ ከውጭ ስንዴ ለመግዛት ጨረታ ወጥቶ በተደጋጋሚ ሲሰረዝ እንደከረመ እናስታውሳለን፡፡ ይህም የስንዴ ዋጋንና የዳቦውን ዕጥረት አባብሷል፡፡ ይህ ችግር አሁንም አልተፈታም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማበጀት ምን እንደታሰበ ግልጽ አይደለም፡፡ ለሸማቾች ዱብ ዕዳ ሆኖ ለከረመው ችግር መንስዔነት የሚቀርበው ማብራሪያ በተለያየ መንገድ የሚገልጽ ቢሆንም የኅብረተሰቡን ፍላጎት ጠብቆ፣ ቀድሞ አስቦና አቅዶ የመሥራት ችግር የፈጠረው ጣጣ ስለመሆኑ ግን ተገንዝበናል፡፡ የሚያሳዝነው ግን አሁንም ችግሩ ሳይቀረፍ መዝለቁ ነው፡፡ ሰሞኑን እንደ ሰማነውም ለበዓል ዕጥረት እንዲፈጠር ተብሎ የተገዛው ዱቄት ገና ከወደብ ወደ መሐል አገር አልደረሰም፡፡ ይህ በመሆኑም ዱቄቱ እስኪደርስ መጠበቅ ግድ ሆኗል፡፡ በየቦታው አቅርቦት የለም የሚለው ቤተኛ ጩኸት የሰሚ ያለህ እያለ ነው፡፡ ከስህተቱ ተምሮና አርሞ የሚሠራ አካል ማየት የሚናፍቅ ዘርፍ ሆኗል፡፡

የምንዛሪ ለውጥ ከተደረገበት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ሸማቹ በዋጋም በአቅርቦትም እንደተበደለ ዓመቱን ለመግፋት ተገዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀር የምንዛሪ ለውጡ የሚያመጣው መዘዝ ለሁሉም ግልጽ ነበር፡፡ እንደተፈራረሙም ለውጡን ተከትሎ የፍጆታ ሸቀጦች ብቻም ሳይሆን የሁሉም ምርትና አገልግሎት ዋጋ ገሸበ፡፡ ልጓም አጣ፡፡ የዋጋ ጭማሪው የብር ምንዛሪ ለውጥ በተደረገ በማግሥቱ መታየት የጀመረ ነው፡፡ በገበያው ውስጥ የተፈጠረው የዋጋ ለውጥ ግን የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ ከመቀነስ በላይ ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ የዋጋ ጭማሪው ገቢው ተወስኖ በሚኖረው፣ በተለይም በደመወዝተኛውና በጡረተኛው ዜጋ ላይ የፈጠረው የኑሮ ጫና ቀላል ባይሆንም፣ የወቅቱ አገራዊ ጉዳይ የሰነቀው ተስፋ የኑሮ ክብደቱን ብዙም ትኩረት እንዳያገኝ ሸፋፍኖት ካልሆነ በቀር አብዛኛው ነዋሪ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል፡፡

ከዋጋ ግሽበት ባሻገር በአገልግሎት አሰጣጥና መስተንግዶ ላይ የሚታየው መጉላላት በተሸኘው ዓመት ብዙም መሻሻል ያልታየበት ነው፡፡ የሕዝብ ተቋማት ስማቸው እንጂ ግብራቸው ያልተቀየረበት ዓመት ነበር፡፡ የተለያዩ ምርቶችን ከባዕድና ከጎጂ ነገሮች ጋር በመቀላለቀል ለሸማቹ የማቅረብ ስግብግብነት በ2010 ዓ.ም. በሰፊው ሲታይ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ እንጀራን ከጀሶ ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ የተገኘ ተጠርጣሪ ስለመያዙና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወደበት ብንሰማም፣ ግፉበት በርቱ ተበራቱ የተባሉ ይመስል ከሰጋቱራ ጋር እየቀላቀሉ የሚጋግሩትንም ጉድ ሰምተን አረፍነው፡፡ ነገሩ ግን የአንድ ሰሞን ጩኸት ስለመሆን ሥራዬ ብሎ የሚያስቆመው አካል አለማግኘቱን ያሳያል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰቆቃዎች የሸማቹ አበሳ የሆኑበት ዓመት አብቅቶ ሌላኛው እየተተካ ነው፡፡ ስለዚህ አሮጌው ዓመት ከሸመታና ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የነበሩ ችግሮች ያልተፈቱበት ነው ማለት ነው፡፡

በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ መልካም ዜና የተሰማው ከኢትዮ ቴሌኮም ሳይሆን አይቀርም፡፡ በአገልግሎት ጥራት ጉድለት ሲያበግነን የኖረው ኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ መወሰኑ ለተገልጋዩ እሰየው የሚያስብል ነበር፡፡ አንደውም የዱቤ አገልግሎት መጀመሩ በዓመቱ ቴሌን አበጀህ ይልመድብህ ያስባለው በጎ ጅምሩ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡

ቴሌ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉንና አዳዲስ አገልግሎቶችን እንዳስተዋወቀ በነገረን ሰሞን፣ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ አሻሽላለሁ፣ ዋጋ እጨምራለሁ ማለቱ ሕዝቡን ‹‹የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል›› አሰኝቶታል፡፡  የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ አስተካክላለሁ ያለበት ምክንያት ተገቢነት ሊኖረው ቢችል እንኳ፣ አነሳሱ ግን የሕዝቡን ወቅታዊ አቅምና የኑሮ ሁኔታ ከግምት ያስገባ አይመስልም፡፡ ምናልባትም ፖለቲካዊ መረጋጋቱ እንዳያገረሽ ሊያደርገው እንደሚችልም መታሰብ ነበረበት ያሰኛል፡፡ በዚያም ላይ አሁን የሚከፈለው ታሪፍ ከአገልግሎቱ አንፃር ከበቂ በላይ ነው፡፡ ታሪፍ ከጨመረም አገልግሎቱን ማስተካከልና ማዘመን ይኖርበታል፡፡ ባሻው ጊዜ መብራት እያጠፋ እንዳሻው ታሪፍ እጨምራለሁ ማለቱም ከመንግሥት ተቋም የማይጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ የታሪፍ ለውጡ በኤሌክትሪክ ማምረቻ ወጪና ለአገልግሎቱ የሚሸጥበት ዋጋ በድጎማ የሚሸፈን በመሆኑ፣ ይህን ማቻቻል በማስፈለጉ ለውጥ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በጥቅሉ በ2010 ዓ.ም. የተመለከትናቸው በርካታ ክስተቶች ሸማቹን የተፈታተኑ ነበሩ፡፡ በአዲሱ ዓመት የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ይሆን ዘንድ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ የሸማቹን መብት ከማስጠበቅ አንፃር በመንግሥት ሊወሰዱ ከሚገባቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ፣ በሕገወጥ መንገድ እየተመረቱ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማስቆም፣ ጥራትን መቆጣጠር፣ ያልተገባ ውድድርና አላግባብ ዋጋ የሚያንሩትን አደብ ለማስገዛት የሚያስችል አቅም መፍጠር የመንግሥት ሚና ነው፡፡

አዲሱ ዓመት፣ እስካሁን የተጓዝንበትን ያልተገባ የግብይት ሥርዓት የምንዋጋበት፣ ጨዋ፣ ሕግ አክባሪና ምሥጉን የግብይት ተዋናዮችን የምናይበት እንዲሆን፣ ሁሉም በየፊናው ተባብሮ የሚሠራበት ዓመት እንዲሆን እንመኛለን፡፡ መልካም ዓውደ ዓመት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት