Wednesday, April 17, 2024

ባለመንታ ገጽታው ተሰናባቹ ዓመት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያውያን ዓምና ብለው ሊጠሩት የተቃረቡትን 2010 ዓ.ም. በመስከረም ወር የተቀበሉት በአገሪቱ በበርካታ አካባቢዎች ይከሰቱ በነበሩ አሰቃቂ የእርስ በእርስ ግድያዎች፣ በጎጠኝነት ምክንያት ብቻ ዜጎች ከትውልድ ቀዬዎቻቸው ያፈሩትን ጥሪት ተነጥቀው እንዲፈናቀሉና አሰቃቂ ሕይወትን በመጠለያ ካምፖች መግፋት በጀመሩበት፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታና ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ባልታወቀበት ጨለማ ውስጥ ሆነው ነበር። በዚህ አስከፊ ሁኔታ የጀመረው 2010 ዓ.ም. በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ፣ ጭካኔ በተሞላበት የእርስ በርስ ግጭትና መጠፋፋት ወደ ገደል አፋፍ ወስዶ ካቆየ በኋላ፣ መልሶ ኢትዮጵውያን ተስፋቸውን አልያም ዳግም ወደ ገደሉ አፋፍ የሚመለሱበትን የመንታ መንገድ አማራጭ በማቅረብ ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ አድርሷል።

የተጠናቀቀው ዓመት በአንድ በኩል ማኅበረሰቡን በአስጨናቂ የፖለቲካ ጎዳና፣ በሌላ በኩል እንዲሁ የአገሪቱን ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ ህልውና በፈተነ የውስጥ ትግል እስከ ሰባተኛው ወር መጋቢት ዘልቋል። ከወርኃ መጋቢት መልስ ደግሞ ሌላውን የተስፋና የሥጋት መንታ መንገድ አሳይቷል። ቅድመ ወርኃ መጋቢት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሐምሌ ወር 2009 .. የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት፣ ከሁለቱም ወገን በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው 2010 ዓ.ም. የመጀመርያ ምዕራፍ (ቅድመ መጋቢት) ለነበረው አስጨናቂ የፖለቲካ ድባብ መሠረታዊ ምክንያት ባይሆንም፣ ገፊ ምክንያት እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል።

ይኼንን ገፊ ምክንያት ይዞ የፖለቲካ ፍልሚያው በአንድ በኩል ማኅበረሰቡን በሌላ በኩል በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል መፋፋም የጀመረው 2010 በመስከረም ወር ላይ ነበር። በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው አሰቃቂ ግጭት፣ የእርስ በርስ መጠፋፋትና መፈናቀል ሳቢያ ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዙ አድርጓቸዋል። በዚህም የተነሳ ከአፈ ጉባዔነታቸው የመልቀቅ ጥያቄ ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም. ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የፖለቲካ ቅራኔ ከመስከረም ወር አንስቶ እንዲቀጣጠል ሌላው ምክንያት ሆኗል። ‹‹የምወክለው ሕዝብና የድርጅቴ ክብር ተረግጦ በሥልጣን ላይ መቆየቱን አልመረጥኩም፤›› በማለት ምክንያታቸውን በይፋ የተናገሩት የቀድሞው አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ‹‹የሕዝብና የድርጅቴን ክብር ለማስመለስ እታገላለሁ፡፡ ከአፈ ጉባዔነት ብለቅም በምክር ቤት አባልነት እቀጥላለሁ፤›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡

አቶ አባዱላ ይኼንን በይፋ በመናገራቸው ምክንያት ምክር ቤቱ 2010 .. የሥራ ዘመኑን ለመጀመር በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ቀን ማለትም መስከረም 29 ቀን የሚካሄደውን ስብሰባ በአፈ ጉባዔነት ላይመሩት እንደሚችሉ በርካቶች ገምተው ነበር፡፡ ምክር ቤቱም በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ በመገመት በጉጉት የተጠበቀ ዕለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄያቸው በኢሕአዴግ ምላሽ ባለማግኘቱ የፓርላማውን የሥራ ዘመን በአፈ ጉባዔነት መርተዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ የመጀመርያ የምክር ቤቱ ስብሰባ በኃላ የነበሩትን ተከታታይ ስብሰባዎች የተመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ / ሽታዬ ምናለ ነበሩ። ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የዓመቱን የሥራ ዘመናቸውን ለመጀመር በጋራ የሚያካሂዱትን ስብሰባ በመክፈትና በዓመቱ ትኩረቱ እንዲደረግባቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ለምክር ቤቶቹ ለማሳሰብ፣ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (/) የተገኙበትን የጋራ ጉባዔ አቶ አባዱላ በአፈ ጉባዔነት መርተውታል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄና መነሻ ምክንያቱ በኢሕአዴግ ውስጥ የፖለቲካ ውዝግብ ለመቀስቀሱ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የመንግሥታቸውን የዓመቱ ፕሮግራሞች ለማቅረብ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ወቅት፣ አቶ አባዱላ በምክር ቤቱ ጨርሶ አለመገኘታቸው ይገኝበታል። በኦሮሚያናሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈጠረው አሰቃቂ ግጭትና መፈናቀል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የአስተዳደር ወሰን አለመካለልን በምክንያትነት ለሕዝብ ሲገልጹ ከቆዩ በኃላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቅምት 16 ቀን የፓርላማ ቆይታቸው የግጭቱን ምክንያት ሌላ መሆኑን መናገራቸው አቶ አባዱላ ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄና ምክንያቱ በኢሕአዴግ ውስጥ የፈጠረው ጫና ውጤት እንደሆነ ይነገራል።

አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይኼ ግጭት የወሰን ግጭት አይደለም፤›› ሲሉ ለፓርላማው ማብራሪያ አቅርበው ነበር። በማብራሪያቸውም በአካባቢው ያለውን የጫት ንግድ ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫና በዚሁ አካባቢ የነገሠውን ከፍተኛ ሕገወጥ የዶላር ዝውውርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የብሔር ግጭት አዋጭ እንደሆነ ያመኑ፣ በኢሕአዴግ ውስጥና በውጭ ያሉ ጥገኞች የቀሰቀሱት መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። አክለውም፣ ‹‹የዚህ ግጭት መፍትሔም ፖለቲካዊ ነው፡፡ እነዚህን ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች በመድፈቅ መፍትሔ ካልተሰጠ በስተቀር መቼም ቢሆን ግጭቱን ለማስቆም አይቻልም፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይኼም በኢሕአዴግ ውስጥ ትግል መቀጣጠሉን አመላካች ነበር።

አቶ አባዱላ ‹‹የሕዝባቸው ክብር›› እንዲመለስ እንደሚታገሉ ገልጸው መልቀቂያ መጠየቃቸውን ተከትሎ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በመቀሌ ረጅም ቀናትን የወሰደ ስብሰባ ውስጥ መቀመጡ፣ እንዲሁም አቶ የኃይለ ማርያም የግጭቶቹ መንስዔም ሆነ መፍትሔ ፖለቲካዊ መሆኑን መግለጻቸው፣ የመፍቻውን ቁልፍ ከሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በወቅቱ እንዲጠበቅ አድርጓል። ሕወሓት እረፍት እየወሰደ ያደረገው ስብሰባ 35 ቀናትን ፈጅቶ ከተጠናቀቀ በኃላ ያወጣው መግለጫም፣ በአገሪቱ በወቅቱ ለሚስተዋሉት ግጭቶችና አጠቃላይ የፖለቲካ ቀውስ የራሱን ድርሻ በግልጽ የወሰደ ነበር።

ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ ‹‹በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች ዋነኛው ተጠያቂነት ለየድርጅቱ አመራር የሚተው ቢሆንም፣ በሕወሓት አመራር ውስጥ ይታዩ የነበሩ አዝማሚያዎች ለብዙ አሥርት ዓመታት በእሳት ጭምር ተፈትኖ የመጣውንና ለአገራችን ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ ዕውን መሆን ምክንያት የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በመሸርሸር ረገድ የማይናቅ ድርሻ እንደነበረው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ አረጋግጧል፤›› በማለት ገልጿል። ይህ መግለጫ የገዥው ፓርቲ አመራሮች ወደ ውስጣቸው መመልከት ከጀመሩ የአገሪቱን ቀውስ ለመቅረፍ አንድ ዕርምጃ ነው የሚል ስሜትን በወቅቱ ፈጥሮ በር።

ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ግጭቶችና የእርስ በርስ መጠፋፋቶች ከመርገብ ይልቅ መስፋፋታቸውን ቀጠሉ፡፡ በተለይ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኞችን አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት ተሰማርተውም ቢሆን፣ ዘርን መሠረት ያደረገው መጠፋፋት በጅምላ የመተላለቅ ባህሪን መላበስ ጀመረ፡፡ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በተለይ በቦረና፣ በጉጂና በባሌ የዘር ጥቃትና መጠፋፋትን መቆጣጠር ባለመቻሉ በአካባቢው ሰላም ጠፋ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ዘርን መሠረት አድርገው መጠፋፋት ውስጥ መግባታቸው፣ በኢሕአዴግ ውስጥ በወቅቱ ከነበረው ውስጣዊ ትግልና ሽኩቻ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቁርኝት ታይቶበታል፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ብቅ ያሉ የለውጥ ኃይሎች ለረዥም ጊዜ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ከሚገኘው የጎምቱ ፖለቲከኞች ስብስብና ከዚህ ጋር ግንኙነት ካለው ሥልጣኑን ማስጠበቅ ከሚፈልግ ቡድን ጋር የጀመሩት ትግል ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው እየተተነፈሰ፣ የኢሕአዴግ የውስጥ ሽኩቻ ወደ ማኅበረሰቡ ወርዶ ተመሳሳይ ሽኩቻ መቀጣጠሉን ተያያዘው፡፡

ለዚህ ምቹ የሆኑት ደግሞ የአገሪቱ ብሔረሰቦችን አሰባጥረው የያዙት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሆኑ፣ ግጭትና ዘርን መሠረት ያደረገ መጠቃቃት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መቀጣጠል ጀመረ፡፡

በትግራይ ክልል በሚገኘው አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ ወጣት ተማሪ ሞቶ መገኘቱ በቅፅበት ፖለቲካዊ ትርጉም ይዞ ተማሪውን የወከለው ብሔር አባላትን አስቆጥቶ ግጭት ቀሰቀሰ፡፡ ይህም በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ምላሽ እየተሰጠው በበርካታ አካባቢዎች ተቀጣጠለ፡፡

በአዲግራት፣ በጎንደር፣ በወለጋ፣ በደብረ ታቦር፣ በወልዲያ፣ በባህር ዳር፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ቀውስ ተቀስቅሶ የወጣት ተማሪዎች ሕይወት በከንቱ መጥፋቱ፣ በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲዎችን የትምህርት እንቅስቃሴ አስተጓጎለ፡፡

መንግሥትን አምነው ወደ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ልጆቻቸውን ለትምህርት ከላኩ ወላጆች የቻሉት ልጆቻቸውን ማውጣት ሲጀምሩ፣ ያልቻሉት ደግሞ በጭንቀት ተዋጡ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 50 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በ29 ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች በመቀስቀሳቸው የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋረጠ፡፡

ይህ ችግር በመንግሥት የሚተዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች መከሰቱ በአገሪቱ መንግሥት እንደሌለ የሚያስተላልፈው መልዕክት ከፍተኛ መሆኑ ያሠጋው  መንግሥት፣ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በዩኒቨርሲቲዎቹ የተከሰተውን ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማረጋጋት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በምሥራቁ አካባቢ ግጭቶችና የዘር መጠፋፋቶች ቀጠሉ፡፡

በታኅሳስ ወር መጀመርያ ላይ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአገሪቱ ቀውስ ላይ መምከር እንደጀመረ፣ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በጨለንቆ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው 15 የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸው የኦሮሚያ ክልልን ክፉኛ አስቆጣ፡፡ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ውስጥ የነበሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የወቅቱ የኦሕዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ስብሰባውን አቋርጠው የመከላከያ ሠራዊትን የኃይል ዕርምጃ ከማውገዝ ባለፈ፣ የሚመሩት ክልል የመከላከያ ሠራዊቱን ዕርዳታ ሳይጠይቅ ወደ ክልሉ ለፀጥታ ሥራ መሰማራቱ የሕግ ጥሰት እንደሆነ በይፋ ተናገሩ፡፡

ከዚህ የጨለንቆ ክስተት በኋላ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ቢቀጥልም፣ በዚሁ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ግጭቱን የሚያባብስ ሌላ አሰቃቂ ጥቃት በሶማሌ ተወላጆች ላይ ተፈጸመ፡፡ ‹‹ለደኅንነታቸው ተብሎ በፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ እንዲጠበቁ›› የተደረጉ የተባሉ 36 የሶማሌ ተወላጆች በጅምላ መገደላቸው ተሰማ፡፡

ይህ ክስተት በርካቶችን አስደነገጠ፡፡ በስብሰባ ላይ የነበረው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ ስብሰባውን አቋረጠ፡፡ የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በብሔራዊ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ድርጊቱን አወገዙ፡፡ በሌሎች አካባቢዎችና ዩኒቨርሲቲዎች የቀጠሉ ግጭቶችም ተገቢ እንዳልሆኑና ሕይወታቸውን ላጡት ሐዘናቸውን ገለጹ፡፡ በዚህ መግለጫቸው የሰጡት ማሳሰቢያ አገሪቱ ምን ላይ እንደደረሰች በግልጽ ያሳይ ነበር፡፡

‹‹በተለያዩ አካባቢዎች በግጭቶች ሳቢያ ክቡር የሰው ሕይወት መጥፋቱ፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውና የዜጎት ሀብትና ንብረት መውደሙ ብቻ ሳይሆን፣ ችግሮቹ ካልተወገዱ እንደ አገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን ይቻላል፤›› በማለት አገሪቱ የቆመችበትን የገደል ጫፍ አቶ ኃይለ ማርያም በመግለጫው ግልጽ አደረጉ፡፡

በአገሪቱ የተቀሰቀሱ ግጭቶች አንዴ ሰከን አንዴ ደግሞ በአስፈሪ ሁኔታ ሲቀጥሉ፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በአገሪቱ ቀውሶችና ይኼንኑ መነሻ ባደረገው የውስጥ ፖለቲካዊ ትግል በመናጥ ላይ ነው፡፡ በዝግ ከሚካሄደው ከዚህ ስብሰባ የሚወጣ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ኦሕዴድ በዚህ የውስጥ ትግል ግንባር ቀደሙ ብቻ ሳይሆን የትግሉ አቀጣጣይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ከመጀመሩ አስቀድሞ በአገራዊው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም መወረርን በድንገት ትኩረት የሰጡ በጎ ፈቃደኛ የኦሮሚያ ወጣቶች፣ የጣና ሐይቅ ሕመም የኦሮሚያ ሕዝብም ሕመም እንደሆነ በመግለጽ ‹‹ጣና ኬኛ›› ወይም ‹‹ጣና የእኛ›› በሚል መሪ ቃል ጣና ሐይቅን የወረሰውን የእምቦጭ አረም ለመንቀል ወደ ሥፍራው ማቅናታቸው፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ማርሽ ቀያሪ ውጤት አስከትሏል፡፡

ይህ የወጣቶቹ ዕርምጃ ከማኅበራዊ ፋይዳው ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታው ገኖ በመውጣት፣ የኦሮሚያና የአማራ ብሔሮችን ጥምረት (ኦሮማራ) በመውለድ በውጤቱም ሁለቱን ብሔሮች በሚመሩት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች (ኦሕዴድና ብአዴን) መካከል የታክቲክ የፖለቲካ ጥምረትን በኢሕአዴግ ውስጥ አበረከተ፡፡

ይኼንንም ፍንትው አድርጎ ያሳየው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 17 ቀናት ከፈጀ ስብሰባ በኋላ ውሳኔዎቹን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹‹ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመሥርቶ ከመተጋገል ይልቅ፣ መርህ አልባ ግንኙነትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ሥልት ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይኼንን የመሰለ ጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ መርህ አልባ ግንኙነት፣ ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹን በማዳከም ውጤት አስከትሏል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመግለጫው ያነሳው ሌላው ነገር፣ በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ምክንያት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ችግር እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በታኅሳስ ወር ስብሰባው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሥራች ፓርቲዎቹ በየፓርቲያቸው ለመተግበር ተስማምተው ቢወጡም፣ ወደ ቀደመው ሽኩቻቸው ለመመለስ አፍታም አልቆዩም፡፡

የስብሰባውን ውሳኔዎች ሁሉም በየፊናው በተለያየ መልክ መተርጎም ጀመረ፡፡ በተለይ ‹‹መርህ አልባ ግንኙነት›› የሚለው በመግለጫ ውስጥ የገባው ሐረግ ትርጓሜ የአማራና የኦሮሞ ብሔሮች አዲስ የግንኙነት ጅማሮን ለመውቀስ እንደሆነ በሕዝብ ዘንድ በመታሰቡ፣ ሁለቱን ብሔሮች የሚወክሉት ኦሕዴድና ብአዴን እንደዚያ ዓይነት ትርጓሜ እንደሌለው፣ ይልቅም ሕወሓት የድርጅቶቹን ነፃነት የማሳጣትና ኔትወርክ የመመሥረት አባዜው መርህ አልባ ግንኙነት ማለት እንደሆነ በየፊናቸው ገለጹ፡፡ አክለውም የተጀመረውን የኦሮሚያና የአማራን ሕዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር በባህር ዳር ከተማ የሕዝብ ግንኙነት በማድረግ፣ በፊት በነበሩ ታሪኮቻቸው ምክንያት የተጋረደባቸውን መጋረጃ ቀደው ተቀራረቡ፡፡

ይህ ተግባር በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ከያዙት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሌላው የታኅሳሱን ስብሰባ ተከትሎ የአራቱ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት መግለጫ ከሰጡ በኋላ ለየት ያለ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና  ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸው ሌላው በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የሥልጣን ፍልሚያ ወደ መጨረሻው ፍፃሜ ያደረሰው ነው፡፡ በርካቶችም ኢትዮጵያን ከማጥ ውስጥ ማውጣት የቻለ ውሳኔ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በየካቲት ወር ውስጥ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ባያቀርቡ ኖሮ፣ በፓርቲው ውስጥ ያለው የሥልጣን ሽኩቻ ተባብሶ በመቀጠል ለአገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ይፈጥር እንደነበር በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያምም ሥልጣናቸውን ለመልቀቅና የመፍትሔው አካል ለመሆን የሚል ምክንያት የማስቀመጣቸውን ትርጓሜ በርካቶች የተረዱት፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው የሥልጣን ትግል ተጠናቆ በአቶ ኃይለ ማርያም ምትክ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመረጠ በኋላ ነው፡፡

የአቶ ኃይለ ማርያም የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄን ለመመለስ ኢሕአዴግ ወደ ሁለት ወራት ገደማ ፈጅቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ የአቶ ኃይለ ማርያምን የሥልጣን መልቀቂያ ማቅረብ ተከትሎ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ቢወስኑም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መሰንዘራቸው ግን አልቀረም፡፡ በዚህ ምክንያት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በመወሰኑ፣ በየካቲት ወር ለእረፍት ተበትኖ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ተጠራ፡፡ ፓርላማው ተሰብስቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንደሆነ በውዝግብ ውስጥ ወሰነ፡፡ የውዝግቡ ምንጭ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ ከምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማግኘትን የሚጠይቅ እንደሆነና በዕለቱ የተገኘው ድምፅ አነስተኛ መሆኑ አንደኛው ምክንያት ሲሆን፣ በኢሕአዴግ ጫና ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ አንስተው ወደ ኃላፊነታቸው የተመለሱት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔውን የገለጹበት ሁኔታ ነው፡፡ በ346 ድምፅ፣ በ88 ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ መፅደቁን ይፋ አድርገው ስብሰባውን ከዘጉ በኋላ በመገናኛ ብዙኃን የገለጹት ቁጥር የድምር ስህተት እንደነበረበት፣ ትክክለኛውም ቁጥር በ88 ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፀ ተአቅቦና በ395 የይሁንታ ድምፅ የፀደቀ መሆኑን መናገራቸው፣ በበርካቶች ዘንድ የአስቸኳይ አዋጁ ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ አደረገው፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት በአቶ ኃይለ ማርያም ምትክ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርን ከመምረጡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መታወጁ፣ በርካቶችን ለሴራ ትንታኔ ከመዳረጉ ባለፈ በአንፃሩ ተረጋግቶ የነበረውን የአገሪቱ ፀጥታ በድጋሚ የማገርሸት ምልክት ማሳየት ጀመረ፡፡

በተለይ በታኅሳሱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት ዴሞክራሲን ለማስፋትና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስተካከል በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች በምሕረትና በይቅርታ እንዲፈቱ ያሳለፈው ውሳኔ ወጥነት በጎደለው መንገድ መፈጸሙ ቁጣ ወደ መቀስቀስ ተሸጋገረ፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተደራጁ ወጣቶች ንቅናቄ ‹‹ቄሮ›› የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ለማስፈታት ያደረገው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተለየ ሁኔታ ሰላም የነበረችው አዲስ አበባ ዙሪያ መጠጋቱ ከፍተኛ ሥጋት ፈጠረ፡፡ ይሁን እንጂ የወጣቶቹ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማግኘቱ ሥጋቱን ቀለበሰው፡፡ ሆኖም ይህ የተከሰተው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኑ የአቶ ኃይለ ማርያምን ተተኪ ለመምረጥ ለተዘጋጀው የኢሕአዴግ ምክር ቤት የብዙኃንን ድምፅ የመጠምዘዝ ፍላጎት ለማሳካት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስፈጸሚያ መሣሪያ ለማድረግ ታስቦ ከሆነ፣ እንደማይቻል መልዕክት የተላለፈበት መሆኑን በወቅቱ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡

የኢሕአዴግ የውስጥ ትግልም በሥልታዊ እንቅስቃሴ ወደ ኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት የመጡትን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እልህ አስጨራሽ በሆነው እስከ ዕኩለ ሌሊት ድረስ በተፈጸመ ሒደት መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፡፡

ድኅረ መጋቢት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ በኋላ ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡ አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት በተለይ አንድነት፣ ፍቅርና ይቅርታ ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ይፋ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሰፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ይህ ንግግራቸውም በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች አቅጣጫዎችን ያመላከቱበት ነበር፡፡ የመላውን ሕዝብ ትኩረትና ቀልብም ስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ‹‹ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት ዓበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው። ክስተቱ በአንድ በኩል በአገራችን ዘላቂ፣ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የሕገ መንግሥትታዊ ሥርዓት መሠረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በሕዝብ ፍላጎት ሕዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል፤›› በማለት፣ እያንዳንዱን የአገሪቱ ችግር እንዴት ለመፍታት እንደሚቻል አመላክተው የሌሎች ድርሻም ምን መሆን እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ ከንግግራቸው በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት በርካታ ጉብኝቶችንና ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ነዋሪዎች ጋር በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ጉብአቶችን በማድረግ በጎበኟቸው አገሮች ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያዊንን በማስፈታት ራሳቸው በተሳፈሩበት አውሮፕላን ጭምር ይዘው መመለሳቸው፣ በአገር ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

በኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ሥራ አስፈጻሚውን በመሰብሰብ የመንግሥት ግዙፍ የልማት ተቋማትን በሙሉና በከፊል ለግሉ ዘርፍ ለማዘዋወር ማስወሰናቸው፣ እንዲሁም የኢትዮ ኤርትራን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በቅድሚያ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መቀበል ያስፈልጋል በሚል ምክንያት፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ማስወሰናቸው ግራ መጋባትን ሲፈጥር የኢሕአዴግ መሥራችና አባል የሆነው ሕወሓት ውሳኔውን የተቻኮለ በማለት በጥርጣሬ ዓይቶታል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሳያቆማቸው የመጀመርያውን የሰላም ግንኙነት ምዕራፍ ወደ ኤርትራ በማቅናት፣ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስበዋል። ይኼንንም ተከትሎ የኤርትራ ፕሬዚዳንት በአዲስ አበባ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ የዕርቅ ጉዞው የይስሙላ ፖለቲካዊ ጨዋታ አለመሆኑን አረጋገጡ። በዚህም ምክንያት ለ20 ዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች መገናኘት ቻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩትን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በክብር በጡረታ እንዲሸኙ አድርገው፣ በእሳቸው ቦታ ጄኔራል ሰዓረ መኰንንን የሾሙ ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት ሲሠሩ የቆዩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን በጄኔራል አደም መሐመድ ተክተዋቸዋል፡፡ ይህም የሚነካ ተቋም አይደለም የሚል እምነትን የያዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስደማሚ ተግባር አድርገው ሲቆጥሩት፣ በዘርፉ ላይ የመጀመርያው የሪፎርም ተግባር ተደርጎም ተወስዷል። የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በገቡት ቃል መሠረት ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ጥሪ አቅርበው ወደ አገር እንዲገቡ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ አጭር ጊዜያት ያመጧቸውን ለውጦች በመደገፍ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የምሥጋና ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሠልፉ ላይ በመገኘት በተለይ በክልላዊ ወሰኖች ምክንያት የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በማውገዝ፣ ፍቅር እንዲሰፋና ኢትዮጵያዊነት እንዲነግሥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በሠልፉ ማብቂያ ላይ ግን ለምን ዓላማና በማን እንደሆነ ያልታወቀ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሞ 154 ሰዎች ጉዳት ሲደረሰባቸው፣ የሁለት ሰዎች ሕይወት ደግሞ አልፏል፡፡ ይህም የአገሪቱ ፖለቲካ ገና አለመስከኑን ብቻ ሳይሆን፣ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ያሳያል። ተገልሎና አኩርፎ የቆየውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አሜሪካ ድረስ በማቅናትና በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር ዕርቅ ፈጥረው ተመልሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ታይቶ የነበረው ሰፋ ያለ ግጭት የረገበ ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት በክልልና በዞን ወሰኖችና በሌሎች ምክንያቶች በየቦታው አዳዲስ ግጭቶች ታይተዋል፡፡

በምዕራብ ጉጂና በጌዴኦ፣ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በወልቂጤ፣ በቤንች ማጂና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳና በሌሎች ከተሞች የተከሰቱ ግጭቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳቶችን አስከትለዋል፡፡ እነዚህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶች የመጀመርያዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናዎች ሲሆኑ፣ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው ሥፍራዎች ከኅብረተሰብ ጋር ተወያይተው የዞኖችና የወረዳዎች አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲለቁም አሳስበዋል፡፡ በማሳሰቢያው መሠረት ከኃላፊነታቸው የለቀቁ አሉ፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ዳግም ግጭት በስፋት የተከሰተ ቢሆንም፣ በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ጣልቃ ገብነት የግጭቱ ምክንያት የተባሉትን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት በማንሳት በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ መፍትሔ ያበጁለት ይመስላሉ።

ኢሕአዴግ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ድርጅታዊ ጉባዔውን ማድረግ የነበረበት የመጨረሻ ወቅት ነሐሴ ወር ቢሆንም፣ ጉባዔው መደረግ አልቻለም። በኢሕአዴግ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የወጣቶች የሪፎርም ቡድን የበላይነትን እየያዘ ቢመጣም፣ ፍጥጫው ግን ገና አለየለትም። በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት የተቀበሉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና እየታየ የሚገኘው የፖለቲካ ለውጥ ዘዋሪ አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያ አሁንም ከተንኮል ፖለቲካ አለመላቀቋን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ለውጡ ቢጀመርም አሁንም በመሰቀለኛ መንገድ ላይ ነን፤›› ሲሉ ያለውን ሁኔታ አጠቃለው ገልጸውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከቻይና መልስ ወደ ኤርትራ ጎራ በማለት ከሶማሊያ ጋር በመሆን ከመጠፋፋት በመውጣት፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ትብብር ለመፍጠር ስምምነት አድርገዋል፡፡ ጂቡቲም የትብብሩ አካል እንድትሆን ከኤርትራ ጋር ስምምነት እንድትፈጥር አስችለዋል፡፡ የዓመቱን መጨረሻ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት ጅማሬ አሳይተውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -