በኢትዮጵያ ከስፖርት ሕክምና ጋር የተያያዘ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች እምብዛም በመሆኑ በስፖርት ማዘውተሪዎች የሚከሰቱ ጉዳቶች በዛው መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እስፓይን የተሰኘ የስፖርት አማካሪ ድርጅት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በስፖርቱ ዘርፍ የመጀመርያ የሕክምና ዕርዳታ ሥልጠና ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ሰጥቷል፡፡
በስፖርት ውድድር ወቅት እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ሊከሰት የሚችል አደጋና ስፖርታዊ ጉዳቶችን በሙያው ብቃት ባላቸው የጥቁር አንበሳ የድንገተኛ ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህራን አማካይነት መሆኑ ሥልጠናውን በበላይነት የሚመራው እስፓይን የስፖርት አማካሪ ድርጅት አስታውቋል፡፡ እንደ አማካሪ ድርጅቱ ከሆነ ሥልጠናው ሲሰጥ ይህ ለሰባተኛ ጊዜ እንደሆነ፣ የመጀመርያው ለሁሉም ክለቦች ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህኛው ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር፣ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት የስፖርት ክለብ፣ ለትራንስ ኢትዮጵያ፣ ለወልዋሎ አዲግራት ስፖርት ክለብ፣ ለትግራይ ውኃ ሥራ ክለብ፣ ለክብደት ማንሳት ባለሙያዎች ማኅበርና ለሌሎችም ሥልጠናውን ለመውሰድ ፍላጎቱ ላላቸው ሙያተኞች ነው፡፡
የመጀመርያ የሕክምና ዕርዳታ አሰጣጥ ዕውቀት በተለይ በስፖርት ሙያ ለሚሠሩ ባለሙያዎች በተለይም የስፖርታዊ ሥልጠናና ውድድር ከሚኖረው እንቅስቃሴና ግጭት አንፃር አትሌቶችን ጨምሮ ሁሉም ሙያተኛ መሠልጠን እንዳለባቸው፣ ይህም ለሰው ልጆች መሠረታዊ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ሥልጠናውን የወሰዱ መናገራቸው ታውቋል፡፡ ሥልጠናው በተጨማሪም የመጀመርያ ሕክምና አሰጣጥ ላይ የነበረውን ብዥታ እንዲሁም በአብዛኛው በልማዳዊ መንገድ ይደረጉ የነበሩ ክፍተቶችን በትክክል ሳይንሱ የሚለውን እንዲያውቁ እንዳስቻላቸው ጭምር ሙያተኞቹ መናገራቸው ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
ሥልጠናው ከመጀመርያ ሕክምና አሰጣጥ በተጨማሪ ስፖርት ሕክምና፣ ሥነ አመጋገብ፣ የአካል ብቃትንና ሌሎችንም እንደሚያካትት፣ ይህንኑ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለሌሎችም ባለሙያዎች በቅርቡ ለመስጠት ዕቅድ እንዳለው የእስፓይን ስፖርት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡