በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ክለቦች ከዋንጫ ይልቅ ወደ ከፍተኛው (ሱፐር) ሊጉ ላለመውረድ የሚያደርጉት ፉክክር የብዙዎችን ቀልብ በመግዛት ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛው ሊግ በሁለት ምድብ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ተከፍሎ የሚከናወን የውድድር መርሐ ግብር በመሆኑና ከየምድቡ አንድ አንድ ቡድን በቀጥታ የየምድቡ ሁለተኛ ቡድኖች ደግሞ በጥሎ ማለፍ በሚያደርጉት አንድ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን ሦስተኛ ሆኖ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉት ቡድኖች የሚለዩበት ጠንካራ ፉክክር የሚስተናገድበት በመሆኑ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት በ2011 የውድድር ዓመት ከከፍተኛው ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደጉት ባህር ዳር ከተማና ደቡብ ፖሊስን ተከትሎ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀሉት ክለቦች አንዱ የሆነው የሽረ ስሑል እግር ኳስ ቡድን መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደሚታወቀው ቡድኖች በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ የሚኖራቸው ቆይታ የሚረጋገጠው ደግሞ በሚኖራቸው የፋይናንስና የተጨዋች መጠንና ጥራት ልክ እንደሆነም ይታመናል፡፡
ለትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ፣ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና ከደደቢት እግር ኳስ ክለቦች ቀጥሎ ስሑል ሽረ አራተኛው የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት ተከትሎ ከተለያየ አቅጣጫ ማበረታቻ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር የ30 ሚሊዮን ብር፣ የክልሉ መንግሥት ደግሞ የ15 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሱር ኮንስትራክሽንና ሌሎችም የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ ክለቡ የሚጠናከርበትን መንገድ እያፈላለጉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡