የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1935 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ካህናትንና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ዘመናዊውንና የአብነት ትምህርታቸውን አስተባብረው እንዲይዙና ማኅበረሰባቸው በዕውቀት እንዲያገለግሉበት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንደ ነበር ያስረዳል፡፡ ኮሌጁ በዚህም ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፣ በመቀጠል ደግሞ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕረግ በማስተማር ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ዕጩዎችን ሲያበቃ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የኮሌጅን ደረጃ በ1960 ዓ.ም. ካገኘ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፋኩልቲ አካል ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል፡፡ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ፋኩልቲው ሲዘጋ በወቅቱ በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት በሚፈልጉት የትምህርት መስክ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ መደረጉ ይወሳል፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጁም ተወርሶ አራት ኪሎ ከጎኑ የሚገኘው የሳይንስ ፋኩልቲ ለራሱ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲጠቀምበት ተደረገ፡፡ በ18 ዓመቱ (በ1987 ዓ.ም.) ጀምሮ ኮሌጁ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመልሶ በነበረው ዕውቅናና ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሒደት ቀጥሏል፡፡ በሁለት አሠርታት ጉዞው ከመጀመርያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲሪ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ዓምና ባደረገው ተከታታይ ጥናትም አሁን ካለው የትምህርተ መለኮት ኮሌጅ በተጨማሪ የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሚያተኩሩ አራት ኮሌጆችን በማቋቋም ወደ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለማደግ በሽግግር ላይ ይገኛል፡፡ በተቋሙ ተግባራት ዙሪያ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል አካዴሚክ ዲን መምርህ ግርማ ባቱን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከ75 ዓመታት በላይ ያስቆረጠው መንፈሳዊ ኮሌጁ ጉዞው እንዴት ይገለጻል?
መምህር ግርማ፡- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እስካሁን ያለውን መጠሪያውን ከመያዙ በፊት የተለያዩ አደረጃጀቶችን አሳልፏል፡፡ በ1935 ዓ.ም. ሲጀመር የካህናት ማሠልጠኛ ሆኖ ሲሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንም አካቶ ነበር፡፡ በቀጣይም ኮሌጅ ከሆነ በኋላ በ1961 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቴኦሎጂ ፋኩልቲ ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል፡፡ በ1967 ዓ.ም. ደርግ ሥልጣኑን መያዙን ተከትሎም ለ17 ዓመታት ተዘግቷል፡፡ ከ1984 እስከ 1987 ዓ.ም. በተደረጉ ጥረቶች ዳግም ኮሌጁ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው የዲፕሎማ መርሐ ግብር ወደ ዲግሪ በማሳደግ፣ በመደበኛ ብቻ የነበረው በተከታታይ ትምህርት (ማታ) የጀመረ ሲሆን፣ ሴቶችንም ማካተት ጀምሯል፡፡ በትምህርተ መለኮት (ቴኦሎጂ) ብቻ ተወስኖ የነበረውን የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት እየተሰጠም ነው፡፡ የርቀት ትምህርት ተጀምሯል፡፡ በ2001 ዓ.ም. የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ ከጀመረ በኋላ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የማስትሬት ፕሮግራም ጀምረናል፡፡ የሥራ አመራር ቦርድ ባፀደቀው መሠረትም ዘንድሮ በ2011 ዓ.ም. የሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ይጀመራል፡፡ ይህም ጠንካራ የትምህርት መሠረት ካላት የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋርም ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ በከፍተኛ የማስተማር ደረጃ በደረሱ ፕሮፌሰሮች ለመተጋገዝም ከስምምነት ተደርሷል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች መነሻቸው ገዳማት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት መሠረት መሆኗ የመታወቁን ያህል ተቋማቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲያድጉ አይታይም፡፡
መምህር ግርማ፡- መንፈሳዊ ኮሌጁ በመጀመርያው ምዕራፍ ከማሠልጠኛነት ወደ ኮሌጅነት ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፋኩልቲ ሆኖ በርካታ ምሩቃንን በማስመረቅ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን አገልግሎት ማሰማራት ችሏል፡፡ ለሁለት ሺሕ ዘመናት ጠንካራ የትምህርትና የባህል ማዕከል ሆና ያገለገለችውን ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ይህን አስተዋጽኦዋን አጠናክራም ለመቀጠል ብዙ የሆነ የጥናትና የምርምር ማዕከል ያስፈልጋታል፡፡ አሁን ካለው ኮሌጅ በተጨማሪ በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ኮሌጆችን በማቋቋም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር አምስት ኮሌጆች ይኖራሉ፡፡ እነሱም የትምህርት መለኮት ኮሌጅ (College of Theology)፣ ቅዱስ ያሬድ የዜማና የሥነ ጥበብ ኮሌጅ (St. Yared College of Zema and Fine Arts)፣ የማኅበራዊ ጥናትና የነገረ ሰብእና ኮሌጅ (College of Social Sciences and Humanities)፣ የሥራ አመራርና የሕዝብ አስተዳደር ኮሌጅ (College of Management and Public Administration) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤት (School of Higher Ethiopian Studies) ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው አምስት ኮሌጅ ይዞ በከፊል ሥራውን በ2011 ዓ.ም. ይጀምራል፡፡ በተለይ ቲኦሎጂውና ከፍተኛ ጥናት ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ ሲጀምሩ የተቀሩት ለአንድ ዓመት በጥናትና በዝግጅት ቆይተው በ2012 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚለየው ነገር ምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ መነሻ ያደረገው ነገር አለ፡፡ አንዳንዶቹ ዘርፎች በሌሎች የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነሱን ወስዶ መተግበር ነው? ልዩነቱ ምንድነው? በሚል በርካታ የሐሳብ ልውውጦች ነበሩ፡፡ መጨረሻ ላይ የተደረሰበት ስምምነት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌሎች ኮሌጆች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ ሊያስተምሩ ቢችሉም በዚህ የምናስተምረው ኢትዮጵያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዕይታ ነው፡፡ በውጭ መሥፈርት ሳይሆን በራሳችን፣ ቋንቋውን በቋንቋው ተናጋሪዎች ዓይን ማየት ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው ክፍተት ነበረበት፡፡ ከተለያየ ፍላጎት ተነስተው ስለኛ በግምት፣ በችኩል በርቀት ሆነው የሚሠሩ ጥናቶች አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አይደለም የውጭ ሰው፣ በውስጥ የምንገኘው እኛ እንኳ ጠንቅቀን አላወቅናትም፡፡ ትምህርቷ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሀብት የበዛላት፣ ፀጋ የተትረፈረፈላት ናት፡፡ ምን ያህል ተጠንቷል፣ ተጽፏልና ተዘግቧል ቢባል ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ ዘዴዎችን ከውጭ ልንዋስ እንችላለን፡፡ አቀናጅተን የተለየ ነገርም መፍጠር እንችላለን፡፡ በዚህም ሌሎችም ሊጠቀሙበት ይችላል፡፡ የኛ ታሪክ፣ የኛ ቋንቋ፣ የኛ ባህል ብለን የትምህርቱ ባለቤቶች ግን ሌሎች መሆናቸው ሊበቃው ይገባል የሚል ትልቅ ሐሳብ ያለበት ነው፡፡ ዜማና ሥነ ጥበብን በተመለከተ በቅድመ ምረቃም ሆነ በድኅረ ምረቃ ትኩረት የሚሰጥበት ነው፡፡ በዜማ ረገድ የመጀመርያ ትኩረቱ አድርጎ ቅድመ ምረቃ ላይ አቋቋም፣ ድጓና ሌሎች የዜማ መጻሕፍትና የዜማ ዕድገቶችን ያስተምራል፡፡ ለሁለተኛ ዲግሪ ስፔሻላይዝ ለማድረግ የቅዱስ ያሬድ መጻሕፍት ከይዘት አንፃር፣ የቲኦሎጂ፣ የታሪክና የባህል አንድምታዎችን ያጠናሉ፡፡ ያሬዳዊ ሥነ ጽሑፍን ይመረምራሉ፡፡ ወደ ሥነ ጥበብ ስንመጣ ኢትዮጵያዊ የአሣሣል ጥበብ አለ፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትን ብናይ ከቀለም ምርጫ፣ ከቀለም አዘገጃጀት ራሱን የቻለ አሻራ አለው፡፡ በምዕራባዊው ጥበብ ቀለማቱ ቶክሲስ ናቸው በብዙ ጥንቃቄ በብዙ ችግር ነው የሚጠቀሙት፡፡ የኛ ትራዲሽናል የአሣሣል ዘይቤ ስናይ ለጤና ለዓይንም ሆነ ለመተንፈሻ አካላት አደጋን አይፈጥርም፡፡ ሥጋት የለውም፡፡ ይህ ጥበብ እንዴት ነው ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ የሚችለው ትኩረት ይሆናል፡፡ የሥነ ጥበብ ታሪክና የጥበብ ንድፈ ሐሳብን በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር የሚመጣ ሰፊ ጥናት አለው፡፡ ኪነ ቅቡን፣ አይከኑን፣ ጠልሰሙን ከእያንዳንዱ ተምሳሌት (ሲምቦል) ታሪክ ጋር የሚጠናበት ነው፡፡ በሥነ ጥበቡ ውስጥ የመጽሐፍ (የብራና) አዘገጃጀትም አለ፡፡ ብራና እንዴት ይዘጋጃል? የቀለም አጠቃቀም፣ የቁም ጽሕፈት፣ ድጉሰት፣ አጠራረዝ ወዘተ. በዝርዝር ይዳሰስበታል፡፡ የመስቀል ዓይነቶች (የአክሱም፣ የላሊበላና የጎንደር) የሚጠናበት፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን (አርክቴክቸር) በተመለከተ ኢትዮጵያዊ የምንለው የቱ እንደሆነም ይጠናበታል፡፡ ብዙ ሐተታ አለው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት ውስጥ የተለያዩ የትምህርት አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በውጪውም እንዲሁ፡፡ እነዚህ በምልዐት ይስተናገዳሉ?
መምህር ግርማ፡- ትምህርት ሌላውን አግሎ አንዱን ይዞ አይደለም፡፡ ሁሉንም መያዝ አለበት፡፡ ምዕራቡ ላይ የኢትዮጵያ ብለው የተወሰነውን ብቻ የሚያሳዩበት አካሄድ መደገም የለበትም፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ባህል ውጪ ቢሆኑም በሥነ ጥበብ ደረጃ ለንፅፅር ይጠናል፡፡ የጥንት ሊቃውንት ቁርዓንን በግዕዝ ተርጉመው ይዘዋል፡፡ መጠናት አለበት፡፡ የራስን ባህል ለማወቅ ማነፃፀር ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- የተቋማችሁን አገራዊ አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?
መምህር ግርማ፡- ሰፊና የረዥም ዓመታት አስተዋጽኦ አለው፡፡ በንጉሡ ዘመን ከለውጡ በፊት የነበረው አስተዋጽኦ ቀጥተኛ ነበር፡፡ በርካታ ምሁራንን በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን በተለያየ ደረጃ የነበሩትን አፍርቷል፡፡ የ1960ዎቹን ለውጥ ተከትሎ ቢቀዛቀዝም አስተዋጽኦው በቀጥታ ላይታይ ይችላል፡፡ የኮሌጁን ትምህርት የሚፈልገው እየበዛ መጥቷል፡፡ በተከታታይ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰሮችን ጨምሮ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው ምሁራንም ተምረው እየተመረቁበት ነው፡፡ ይህም ከተለያየ ዳራ የሚመጡትን ባንድ ላይ የሚያገናኝ በመሆኑ ሰላምና አንድነት ፍቅርን የሚያመጣ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ በየዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ግዕዝም ሆነ ሥነ ምግባር ሌሎች ትምህርቶችንም እያስተማሩ ነው፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትርጉም በጣም ሰፊ ነው፡፡ እኛም እየተንቀሳቀስን፣ ኮሌጁም እየደከመ ያለው አንዱ ጠንካራ የኢትዮጵያ የትምህርትና ምርምር ማዕከል ለመፍጠር ነው፡፡ ይህም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሆን ነው፡፡ በተለይ በመማር ማስተማር ሒደት በልዩ ልዩ ነገር ዩኒቨርሲቲውን እንዲደግፉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡