Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየፀሐይና የጨረቃ የዓመት መባቻ የገጠመበት መስከረም 1

የፀሐይና የጨረቃ የዓመት መባቻ የገጠመበት መስከረም 1

ቀን:

ቤተ እስራኤልና የእስልምና አዲስ ዓመትም በመስከረም 1 ላይ ውሏል

ዘመን ከሚሞሸርባት ዓመት ወደሚቀመርባት ወደኛዋ እንቁጣጣሽ ወደ አደይዋ ንስናሽ ተብሎ በመደበኛው ፀሐያዊው የኢትዮጵያ አቆጣጠር መሠረት መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. (የቁጥር ድርደራውም በተመሳሳይ 1111 ሆኗል) አዲሱ ዓመት ገብቶ ሁለተኛው ቀን ላይ እንገኛለን፡፡ ዘንድሮ ልዩ ግጥምጥም በአዲስ ዓመት መባቻ የተፈጠረው በጨረቃ ላይ የተመሠረተው የእስልምና እና የቤተ እስራኤል/የአይሁድ አዲስ ዓመትም ከፀሐያዊው መስከረም 1 ቀን ጋር መገናኘቱ ነው፡፡  

 ይህም የኢትዮጵያባሕረ ሐሳብ ብዙኃነትን ያሳያል፡፡ በሲቪል ካሌንደርም በኢትዮጵያ ክርስትና ቀመርም መስከረም 1 ቀን 2011 ..፣ 7511 ዓመተ ዓለም፣ በፀሓይና በጨረቃ ጥምር ቁጥር የኢትዮጵያ 2019 ..፣ እንዲሁም በቤተ እስራኤሎች/አይሁድ አዲስ ዓመት ሮሽ ሃሻና (ርዕሰ ዓመት) 5779 ዓመተ ዓለም ገብቷል። በዓሉ እስከ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓም ይዘልቃል።

ዓመተ ሒጅራ

በዓለም ዙርያ የእስልምና አዲስ ዓመት ሙሃረም 1 ቀን 1440 ዓመተ ሒጅራ ሰኞ ማታ ጳጉሜን 5 ቀን 2010 ዓም ገብቶ መስከረም 1 ቀን 2011 ሲከበር ውሏል።  የዋሽግተን የዳር አል ሒጅራ እስላማዊ ማዕከል ባልደረባ ኢማም ጆሃሪ አብዱል መሊክ ለዋሽንግተን ታይምስ እንደገለጹት፣ ‹‹የሙስሊም አዲስ ዓመት የሚከበረው በባህላዊ መልኩ ነው›› በሌሎቹ እስላማዊ በዓላት እንዳለው የበዓሉ ዕለት በየዓመቱ የሚቀያየረው መሠረቱ በጨረቃ ሂደት ላይ በመመሥረቱ ነው፡፡ በዓሉ ነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ሒጅራ/የተሰደዱበትን መሠረት ያደርጋል፡፡ ፀሐያዊው መስከረም 1 ቀን፣ ከሙሃረም 1 ቀን (በሐሳበ እስልምና) እና ከጨረቃ ጥቅምት 1 (ሐሳበ ክርስትና) ጋር ገጥሟል፡፡ ሙሃረም እንደ ዐበይት በዓላቱ ኢድ አልፈጥርና ኢድ አልአድሃ ባይሆንም እንደየአገሩ ባህልና ትውፊት ሲከበር የጸሎትና ከቤተሰብ ጋር ጊዜን ማሳለፍ መልካም ተግባራት ይፈጸምበታል፡፡

ዓመተ አይሁድ

ቤተ እስራኤሎች/ አይሁዶች በአቆጣጠራቸው መሠረት እሑድ ጳጉሜን 5 ቀን 2010 .. ማታ አዲሱን ዓመት 5779 ማክበር የጀመሩ ሲሆን እስከ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. አክብረዋል፡፡ ትሽሪ 1 (ጥቅምት 1) ‹‹ሮሽ ሃሻናህ›› ሲባል ፍችውም የዓመት መነሻ፣ የብርሃን መውጫ ነው፡፡ ትሽሪ ወር አዳም የተፈጠረበት ወር ይባላል፡፡ አዳም ከተፈጠረ 5779 ዓመት በሌላ አነጋገርም የዓለም የልደት ቀን ተብሎም ይታሰባል፡፡  በምሽቱም መለከት (ሾፋር) የሚነፋበት  ነው፡፡

በዕለቱ የጣፈጡ ምግቦች ይበሉበታል፡፡ ‹‹የጣፈጡ ነገሮች ማር በአፕል እየነከርን የምንበላው ዓመቱና ቀሪው ዘመን ያማረና የጣፈጠ እንዲሆን ነው፡፡ ሮሽ ሃሻናህ ከአራቱ የአይሁድ አዲስ ዓመቶች አንዱ ሲሆን፣ የመጀመርያው በኒሳን ወር (የጨረቃ ሚያዝያ) የሚከበረው አይሁድ ከግብፅ የወጡበት ዕለት የሚታሰብበት ነው፡፡ በቶራህዘሌዋውያን እንደተጻፈው፣ ሮሽ ሃሻናህ የመጥቅዕ (ደወል/ቀንደ መለከት) በዓል በመባል ይታወቃል፡፡ በዕብራይስጥ በርእሰ ዓመቱ ሮሽ ሃሻናህ መልካም ምኞት ሲገለፅ ‹‹ሻና ቶቫህ ዑመቱካህ›› ማለትም መልካምና የተስማማ ጣፋጭ አዲስ ዓመት ይሁን! ይላል፡፡

ሐሳበ ክርስትና

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ  በትውፊታዊው የመልካም ምኞት መግለጫ መሠረት እንኳን ከ2010 ዘመነ ማርቆስ ወደ 2011 ዓ.ም. ዘመነ ሉቃስ አሸጋገራችሁ የተባለው መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡

ርእሰ ዐውደ ዓመት (የዓመት ዙር ዋና መነሻ) በፀሐይ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር ኢትዮጵያዊ አቆጣጠር 2019 ዓ.ም. ብቷል፡፡ ዘመኑም ተሞሸረ፣ ዓመቱም ተቀመረ፡፡ በባህላዊውና ዓለማዊው ትውፊት ‹‹እንቁጣጣሽ››፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊቷ ቤተክርስቲያን እያንዳንዱን ዓመት ለአራቱ ወንጌላውያን በመስጠቷ ምእመኖቿና ካህኖቿ የተረኛውን ወንጌላዊ ስም በመጥራት መልካም ምኞታቸውን ይገላለጹበታል፡፡

እያንዳንዱ ዓመት ለአራት እያካፈሉ ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ የማቴዎስ፣ ሁለት የማርቆስ፣ ሦስት የሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ እያሉ ይጠሩታል፡፡ የተሸኘው ዓምናው ዘመነ ማርቆስ ሲሆን፣አዲሱን ዓመት  የተረከበው ደግሞ ዘመነ ሉቃስ ነው፡፡

የቤተክርስቲያን ዘመን አቆጣጠር በሦስቱ የብርሃን መለኪያዎች በፀሐይ (Solar)፣ በፀሐይና ጨረቃ (Luni-Solar)፣ በጨረቃ (Lunar) ይቆጥራል፡፡

ከክርስቶስ ልደት በመነሳት 2011 ዓ.ም. የተባለው መሬት በፀሐይ ዙርያ ያደረገችውን የ365 ቀኖች ዙረት በመፈጸሟ ነው፡፡ ይህ አቆጣጠር ከቤተክርስቲያን ሌላ በዓለማዊ (Civil Calendar) አቆጣጠርም አገልግሎት አለው፡፡ ሌላው ከአዳም ተነሥቶ በሚቆጥረውም 7511 ዓመተ ዓለም ገብቷል፡፡ ይህም ስምንተኛ ሺሕ ከገባ 511ኛ ዓመት መሆኑንም ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል ትናንት ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም. ገብቷል፡፡ ይኸኛው አቆጣጠር ደግሞ የፀሐይና የጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤን (ፋሲካ) እና ዐቢይ ጾም (ሁዳዴ) መሰል ተዘዋዋሪ በዓሎችና ጾሞች ለማግኘት የሚያስችላት አቆጣጠር ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም የሚያዘው የካቲት 25 ቀን፣  ፋሲካ የሚከበረው ሚያዝያ 20 ቀን  ተብሎ መስከረም 1 ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ዕለት የታወጀው በፀሐይ 2011 ዓ.ም. ሳይሆን፣ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር 2019 ዓ.ም. ነው፡፡

ሦስተኛው አቈጣጠር ደግሞ 354 ቀኖች ባለው የጨረቃ አቆጣጠር የሚቆጥረው ነው፡፡ አይሁድ፣ ክርስቲያንና እስላም በዚህ አቆጣጠር ይጠቀማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሌሊቱን የምትቆጥርበት መንገድ አላት፡፡ ዓመታቱንም በጨረቃ 354 ቀን ልኬት ታሰላለች፡፡ አዲሱ ዓመትም ከክርስቶስ ልደት ሲነሣ 2073 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህም መሠረት የመስከረም 1 ቀን ሰኞ ሌሊት 27፣ ጨረቃ  ደግሞ 1 ነው፡፡ ይህም የጨረቃ ጥቅምት 1 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ከአይሁድም ሆነ ከእስላም (ሒጅራ) ቀመር ጋር ይመሳሰላል፡፡

በአገር ውስጥና በዓለም ዙርያ በሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በዕለተ ማክሰኞ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡ በየዓመቱ የሚውሉትን ተዘዋዋሪዎቹን አጽዋማትና በዓላት ሁዳዴንና ፋሲካን የመሳሰሉትን በዓዋጅ ተገልጾበታል፡፡

‹‹ውስተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተጽሕፈ ተዝካርከ ባርከኒ እንሣእ በረከትከ›› ማለትም፣ የስምህ መታሰቢያ በዓመቱ መጀመርያ ተጽፏል፤ በረከትህን አገኝ ዘንድ ባርከኝ መርቀኝ እያሉም አወድሰዋል፡፡

የዘንድሮው መጨረሻ ጳጉሜን 6 የሚሆንበት ዓመቱም ከ366 ቀናት በኋላ የሚጠናቀቅበት ነው፡፡ የክረምት የጨለማው ወራት ተፈጽሞ የበጋው፣ የመፀው (አበባ)፣ የጥቢው ብርሃን የሚፈነጥቅባት መስከረም፣ ኢትዮጵያዊው እንደ ሃይማኖቱ በየቤተ አምልኮው እየተገኘ፣ ለዚህች ዕለት ላደረስከኝ አምላኬ ተመስገን፣ የከርሞ ሰው በለኝ፣ ተርፎ ለሚቀረው ዕድሜ አትንፈገኝ ብሎ ፈጣሪውን የለመነበት ነው፡፡

አሮጌው ዘመን ከቀለበቱ ዐውድ ይውጣ፤ አዲሱ በተራው ወደቀለበቱ ይግባ፡፡ በቀለበቱ ውስጥ ሠግረ ክረምት ጥዑም ደወል ይሰማል፡፡ ሐሰት ክፋት ሐኬት ከቀለበቱ ይውጣ፤ ሐቅ ሰላም ቅንነት ትጋት ፍቅር ወደ ቀለበቱ ይግባ እንዲል ማስታወሻችን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...