Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለጊዜው መታገድ ከናካቴው መወገድ አይደለም

ለጊዜው መታገድ ከናካቴው መወገድ አይደለም

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

በአንድ በሆነ ጊዜና ሥፍራ ተፈጽሟል ተብሎ የተገመተን ጥፋት በወጉ ለማጣራት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በአጥፊነት የተጠረጠረውን ግለሰብ ለተወሰነ ጊዜ ከያዘው ኃላፊነት ወይም ከተመዘገበበት አባልነት አግዶ ማቆየት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ በክርክር ላይ ያለ ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይዛወር ወይም እንዳይተላለፍ ከአንደኛው ተከራካሪ ወገን በኩል ጥያቄ የቀረበ እንደሆነ፣ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት አሳማኝ ሆኖ ሲያገኘው አግባብ ያለው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌ በሚፈቅደው መሠረት ከመሸጥም ሆነ ከመለወጥ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ የሚፀና ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

ደረጃውና አተገባበሩ ለየቅል ይሁን እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ ይኼ ለፍርድ ቤቶች ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም፡፡ አስቀድሞ በተቋቋመበት ሕግ ወይም መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሥልጣን የተሰጠው የትኛውም አካል ሊበይነው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የተለመደና እንግድነት የማይታይበት አሠራር ሆኖ ሳለ ሰሞኑን አማራ ክልልን የሚያስተዳድረውና ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ድርጅት በማዕከላዊ ኮሚቴው አማካይነት ሁለት ነባር አባላቱን፣ ‹‹ምግባረ ብልሹዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፤›› በማለት እስከ ተከታዩ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ከአባልነት አግዶ ለማቆየት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ለምን ከፍተኛ ጩኸት እንዳስከተለና ከጫፍ እስከ ጫፍ ማነጋገሩን እንደቀጠለ ለመረዳት አዳጋች ነው፡፡

ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡ በስም ተጠቃሹ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከነሐሴ 17 እስከ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ቅድመ ጉባዔ ስብሰባ ሌሎች በርካታ አጀንዳዎች ቀርበው የተመከረባቸው ቢሆንም፣ ከእነዚሁ ውስጥ ዋነኛ ሆኖ የወጣውና እስካሁን ድረስ ጎራ ለይቶ የሚያነታርከው በአቶ በረከት ስምዖንና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የተላለፈው ዕገዳ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በእርግጥም ማዕከላዊ ኮሚቴው እነዚህን ቀደምትና አንጋፋ ታጋዮች የራሴ ነው ባለው ምክንያት በሌሉበት አግዷቸዋል፡፡

እነ አቶ በረከት በበኩላቸው የድፍረት ያህል የቆጠሩትንና በሰበር ዜና መልክ የተሠራጨውን ይህንኑ ዕግድ አጥብቀው ለመኮነንና የድርጅታቸውን ዕርምጃ ክፉኛ ለማጥላላት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በተለይ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ በረከት ስምዖን የተባለውን ዕገዳ ተከትሎ በወቅቱ የድርጅቱ አመራሮች ላይ የከፈቱት የሚዲያ ዘመቻ ግር የሚያሰኝ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ተከታታይነት ባለውና መንገብገብ በሚታይበት በዚህ ዘመቻ የታገዱት ወገኖች፣ በዚያ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ይሳተፉ ዘንድ በይፋ መጋበዛቸውን ሰውየው አልካዱም፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እየቀረቡ በተፃራሪው የሚነግሩን ወትሮ እንደሚያደርጉት ሁሉ ወደ ባህር ዳር ከተማ ለመንቀሳቀስና በስብሰባው ላይ ለመገኘት የግል ደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ከበላይ አመራሩ በኩል በወቅቱ አዎንታዊ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ነው፡፡

በበኩሌ እንዲህ ያለውን ዋስትና በአሁኑ ወቅት መስጠትም ሆነ ማግኘት ቀላል ነው ብዬ አላምንም፡፡ በአገራችን የተቀጣጠለውን የለውጥ ማዕበል ተከትሎ ክፉኛ በሚናጠውና አለመረጋጋት በሚታይበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለራሱ እንኳ የተረጋገጠ ዋስትና የሌለው ድርጅትና መንግሥት፣ አቶ በረከት የጠየቁትን ዓይነት የደኅንነት ዋስትና የመስጠት አቅም አለው ለማለት ይከብዳል፡፡ ይህ ሲታሰብ ከእነ ሥጋታቸውም ቢሆን ጥሪውን አክብረው በስብሰባው ላይ መታደም የነበረባቸው ይመስለኛል፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ለኮሚቴው ውሳኔዎች ጥራትና ምሉዕነት የራሳቸውን ድርሻ ከማበርከታቸው በዘለለ፣ በራሳቸው ላይ የቀረበውን ክስ በግንባር ተገኝተው በአጥጋቢ ሁኔታ የመከላከል ዕድልና አጋጣሚ ይኖራቸው ነበር፡፡

እነሆ ጥሪው በሚገባ የደረሳቸው ቢሆንም ያለበቂና ሕጋዊ ምክንያት ስብሰባውን አልተሳተፉም፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ እርሳቸው ባላከበሩት መርሐ ግብር ማዕከላዊ ኮሚቴው ያሳለፈውን የትኛውንም ውሳኔና ያወጣውን መግለጫ በዚህ ደረጃ አሳንሶ የመመልከትና አጥላልቶ የመንቀፍ መብት አይኖራቸውም፡፡ ‹ወንድ ወደሽ ፂም ጠልተሽ› እንዲሉ፡፡

በስመ ጥር ፖለቲከኞቹ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ ዕገዳን እንጂ ስንብትን አያመለክትም፡፡ በተወሰደው ዕርምጃ የተሰማቸው ቅሬታ ቢኖር እንኳ፣ ይህንኑ በመስከረም አጋማሽ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ የማቅረብና የማስመርመር መብት እንዳላቸው ይስቱታል ተብሎ አይገመትም፡፡ በእኔ ግምት ሕጋዊና ተቀባይነት ያለው መፍትሔ እርሱ ብቻ ነው፡፡

ለዚህ ያመች ዘንድ ታዲያ ንፁሁን አየር አብዝቶ እየበከለ የመጣውን የሚዲያ ላይ መወራረፍና ክብረ ነክ እንካ ስላንቲያ ውሎ ሳያድር ማቆም ይገባቸዋል፡፡ ‹ዝምታ ለበግም አልበጃት› የሚለው የአቶ በረከት ፈሊጣዊ አነጋገር በተቃራኒው ‹ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል› እንዳይሆንባቸው ሁለት ጊዜ ማሰብ የሚኖርባቸው ይመስለኛል፡፡

የዕገዳ ዕርምጃው ከተወሰደባቸው በኋላ አቶ በረከት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ የመገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ ያለ ይሉኝታ ካስማሟቸው ክሶች መካከል፣ አሁን ያሉት የብአዴን መሪዎች ችሎታ የሌላቸውና የተበላሹ ናቸው፣ ሕዝቡን (የአማራ ክልልን ማለታቸው ነው) አጎራባቾቹ ከሆኑት ከትግራይ፣ ከአፋርና አብሶም ከሱዳን ሕዝቦች ጋር ለሚደረግ ጦርነት እያዘጋጁት ነው የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

በመሠረቱ አካፋን አካፋ ማለት በቁሙ የተወሰደ እንደሆነ ያን ያህል ላይነቀፍ ይችል ይሆናል፡፡ ሌሎች የሥራ ባልደረቦችንና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ተባባሪዎችን ያለ በቂ ማስረጃና ይሉኝታ ዝቅ አድርጎ መመልከትና ይልቁንም በችሎታ ቢስነት መወንጀል ግን፣ የራስን ችሎታ በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ይሆናል፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም አቶ ንጉሡ ጥላሁን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ ሰውየው መምህራችን ሆነው ቆይተዋልና እኛን በችሎታ ቢስነት ለመክሰስ ከደፈሩ፣ እሳቸውም በተመሳሳይ የብቃት ጉድለት ከመጠየቅ አይድኑም ሲሉ በቅርቡ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ምፀት በተላበሰ አነጋገር ሸንቆጥ ያደረጓቸው፡፡

የጦርነት መሰናዶውን አስመልክቶም ቢሆን ወዳጄ አቶ በረከት ያሰሙትን ክፉ ሟርት ፈጽሞ አልወደድኩላቸውም፡፡ በመሠረቱ የግፍና የመከራው ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ በሁኔታዎች ተገፍቶ ከሚገባባቸው በስተቀር ጦርነትና ግጭቶችን የሚወድ ሕዝብ የለም፣ ኖሮም አያውቅም፡፡ በእርግጥ የአማራ ክልል ሕዝብ ለነፃነቱ፣ ለአንድነቱና ለሉዓላዊነቱ ቀናኢ መሆኑ አይካድም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በውል ተመርምረውና ተጣርተው ያልተመለሱለት አያሌ የአስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄዎች እንዳሉት የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ለምሳሌ ከወልቃይት ፀገዴና ከራያ ግዛቶች አከላለልና ከነባር ነዋሪዎቻቸው ማንነት ጋር የትግራይን ክልል ከሚያስተዳድረው የፖለቲካ ድርጅት ጋር በብርቱ ሲወዛገብ እንደቆየና አሁንም ችግሩ እንዳልተፈታ፣ ከማንም በላይ አቶ በረከት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ክልሉ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ደግሞ በጉደኛው መንግሥታችን አማካይነት በየጊዜው ተጨማሪ የእርሻ መሬቶችንና የጦር ሠፈሮችን ያለ ፍላጎታችን እየገበርን እንኳ ሰላም ልናገኝ እንዳልቻልን ከእሳቸው የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡

ያም ሆኖ እነዚህን አለመግባባቶች ሊፈታ የሚፈልገውና የሚገባው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከአጎራባች ወንድሞቹም ሆነ ከድንበር ተዋሳኝ ወዳጆቹ ጋር ሰይፍ ለመማዘዝና ደም ለመፋሰስ አይመኝም፡፡ ጦርነትም ሆነ የእርስ በርስ ግጭት አክሳሪ እንጂ አትራፊ እንዳልሆነ ከልብ ይረዳል፡፡

ዘግይተው የመጡት ተተኪ የብአዴን መሪዎች ከዚህ በተቃራኒው አስበው ከሆነ፣ ይኼንን የሚያውቁት አቶ በረከት ብቻ ናቸው፡፡ ምልዓተ ሕዝቡ ለማየትና ለመለማመድ ከሚመኘው የነፃነት ድባብ ጋር አብረው ለመራመድ መሞከራቸው ግን እጅግ የሚበረታታ እውነታ ይመስለኛል፡፡ ይህ አቋማቸው ዕውን ከሆነ አበጃችሁ የሚያሰኛቸው እንጂ፣ በአቅመ ቢስነት የሚያስከስሳቸው ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡

በመጨረሻም እኔ የብአዴን አባል አይደለሁም፡፡ ሆኖም የድርጅቱን መንግሥታዊ ቅርፅ በከፍተኛ ደረጃ ለረዥም ጊዜ በሙያዬ አገልግያለሁ፡፡ ወዳጆቼን አቶ በረከትንና አቶ ታደሰ ካሳን በዚህ አጋጣሚ የምመክራቸው የሚከተለውን እንዲፈጽሙ ነው፡፡ የሚዲያ እሰጥ አገባውን ባፋጣኝ ያቋርጡ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ይቅርታ ይጠይቁ፣ መጪውን ጉባዔ ያለማመንታት ይቀላቀሉና የተላለፈባቸውን የዕገዳ ዕርምጃ ሕጋዊነትና ፍትሐዊነት በመከላከያ ማስረጃ ይሞግቱ፡፡ ለጊዜው መታገድ ጨርሶ ከመወገድ የተለየ ነውና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...