Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአሰብና የምፅዋ ወደብ ጠቃሚነት የገባቸው ሁለተኛው መሪ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአሰብና የምፅዋ ወደብ ጠቃሚነት የገባቸው ሁለተኛው መሪ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከቻይና ጉብኝታቸው በቀጥታ የሄዱት ወደ አሰብና ምፅዋ ወደብ መሆኑን ስሰማ እጅግ ገረመኝ፡፡ የአሰብና የምፅዋ ወደብ መልሶ የማቋቋሙና ሁኔታዎችን የማመቻቸቱ ጉዳዩ ምን ያህል እንዳሳሰባቸውና ዕረፍት እንደነሳቸው እንዳስብ፣ ከዚያም ታሪኩን በመጀመርያ ወዳለፉት 54 ዓመታት ወደ ኋላ ዞሬ እንዳስተነትን፣ ቀጥሎም ኢትዮጵያንና ኤርትራን ወደሚጨምረው ወደ ጥንታዊ የመርከብ ንግድ ታሪካችን በትዝታ ፈረስ እንድነጉድ አስገደደኝ፡፡ ሠርቶ የሚያሠራ ሰው ሲመጣ እንዲህ ያለው ትዝታ ደርቦ ደራርቦ እንደሚያስከትል የታወቀ ስለሆነ፡፡ ‹‹አድርባይ›› መስዬ ከሆነ አትታዘቡኝ፡፡ ዳሩ ለጥሩ ነገር ማደር ምን አለበት? ጥሩን ማድነቅ፣ መጥፎን መኮነንና እንዲስተካከል ማድረግ የሁላችን ተግባር ሊሆን ይገባዋል እኮ!

እና ዛሬ በአዋጅ ቁጥር 255/2005 የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የሚሰማራባቸው የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ሥራ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዕረፍት የለሽ ክትትል ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ከታሪክ ገጾች እንደምናገኘው ንጉሠ ነገሥቱ ሁለቱ ወደቦች እንደገና ተገንብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ መርከቦች እስኪሰማሩ ድረስ ዕረፍት አልነበራቸውም፡፡

ታሪኩ እንዲህ ነው

ጊዜው ከ1956 እስከ 1966 ዓ.ም. ውስጥ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎቶች (ጀልባና መርከብ) ሥራቸውን የጀመሩት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በተዋሀደች በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በምፅዋ አካባቢ ይሠሩ የነበሩ ግሪኮች በሁለት አነስተኛ ጀልባዎች በቀይ ባህር፣ በሜዲትራኒያን ባህርና በዓረብ ባህረ ሰላጤ አካባቢ ይሠሩ ነበር፡፡ እነዚህም ነጋዴዎች በወቅቱ በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ዕውቅና የነበራቸው ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሀድ ሰፊ የንግድ በር ይከፍታል ብለው ያመኑ የባህር ንግድ ማኅበረሰብ አባላት፣ ከባህር ትራንስፖርትና ከባህር ንግድ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያዋጣ አምነው አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማከናወን ጀመሩ፡፡

  በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ቁጥራቸው በርከት ያሉ መርከቦችን በማንቀሳቀስ በተለይም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ የባህር ንግድ ለማንቀሳቀስ የተነሱት የቀይ ባህር የልማት ማኅበር የተባለው ኩባንያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ድምፅ/አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 1956 ዓ.ም. እንደ ዘገበው፣ መጋቢት 7 እና 8 1956 ዓ.ም. የቀይ ባህር የልማት ማኅበር ንብረት የሆኑ ኤርትራ፣ ጎንደር፣  አክሱምና ሐረር ተብለው የሚጠሩ አራት የንግድ መርከቦች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ አገልግሎት ጀመሩ፡፡ እነሱም እንደ ቅደም ተከተላቸው 3,410 ቶን፣ 700 ቶንና 2,200 ቶን ክብደት ያለውን ዕቃ የመጫን አቅም እንደነበራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በወቅቱ ከማኅበረኞቹ አንዱ የሆኑት አቶ ኃይሉ መከታ እንደገለጹት፣ አራቱም መርከቦች መጋቢት 7 እና 8 ቀን 1956 ዓ.ም. የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ባለሥልጣናትና በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑት የቡልጋሪያ አምባሳደር፣ እንዲሁም የማኅበሩ አባላት በተገኙበት በምፅዋ ወደብ ተመርቀዋል፡፡ መርከቦቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የሚያውለበልቡት የቡልጋሪያ ሰንደቅ ዓላማ እንደነበር ሲታወቅ፣ ምፅዋ ከደረሱ በኋላ ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ የቀይ ባህር ልማት ማኅበር ካፒታል አራት ሚሊዮን ኢትዮጵያ ብር ሲሆን፣ ማኅበርተኞቹም ሁለት ኢትዮጵያዊያንና ሦስት ቡልጋሪያዊያን ነበሩ፡፡

አቶ ጌታቸው በቀለ ግን «ዘ ኢምፐረርስ ክሎዝ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት ደግሞ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደተዋሀደች በምፅዋና በአሰብ አንድ ሁለት መናኛ ጀልባዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህም ጀልባዎች ከኤርትራው እንደራሴ ከራስ አንዳርጋቸው ጋር በመተባበር የሚነግዱት ግሪካውያን ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (ኢንነመ) የባህር ክፍል መሣሪያ ቤት እንዳቋቋመ ግን ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ፡፡ ወደቦችንና መርከቦችን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል በጎረቤት አገሮችና በአውሮፓ አገሮች ከትምህርት ጋር የተያያዘ የሥራ ጉብኝት መደረግ ተጀመረ፡፡

በኤደንና በሌሎች ሥፍራዎች የነበሩና በባህር ትራንስፖርት ዕውቀት የነበራቸው ባለሙያዎች ከየቦታው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል አበበ ወልደ ሥላሴ፣ አድማስ ተሰማ፣ ደምሴ አበበ፣ ነጋሽ ጋረደው፣ ወልዴ አረጋይ፣ ተክኤ ገብረ የሱስ፣ መሃሪ ተወልደ ማርያም፣ በረከት ምሕረት፣ አፈወርቅ ይስሐቅ፣ ተስፋ እግዚ ወልደ ሐዋርያ፣ መላኩና ዮሐንስ ኪዳነ ማርያም (ብርሃኑ ሀብተ ማርያም) የሚባሉ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ የባህር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ምንም እንኳን በሙያው ቢሠለጠኑም፣ አዲስ አበባ ውስጥ በልዩ ልዩ የግል ድርጅቶች ተበታትነው ይሠሩ ነበር፡፡ ከዚያም እነሱ ካሉበት ቦታ እንዲሰበሰቡ በተደረገው ጥረት ስምንት ያህሉ ተገኙና በባህር ክፍል መሥሪያ ቤት ተመድበው እንዲሠሩ ተደረገ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኤደን ወደብ በመርከብ ጥገና ቺፍ መካኒክ ሆኖ ይሠራ የነበረው የ28 ዓመት ወጣት ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሠራ ሲጋበዝ ፈቃደኛ ሆኖ መጣና ሥራው ተጀመረ፡፡ ይህም በ1945 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡

በ1948 ዓ.ም. ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ (ዶ/ር) የባህር መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው ተሾሙ፡፡ የደጃዝማች ዘውዴ መሾምም እንቅስቃሴውን የበለጠ ከፍ አደረገው፡፡ ይልቁንም በራስ አንዳርጋቸው መሳይ ሥር አስመራ የነበረው የባህር ክፍል ከዋናው መሥሪያ ቤት ሥር እንዲሆን በር ከፈተ፡፡

በ1950 ዓ.ም. ደጃዝማች ዘውዴ በልጅ ሚካኤል እምሩ ተተኩ፡፡ ልጅ ሚካኤል እምሩም እንደ ደጃዝማች ዘውዴ ሁሉ በእንግሊዝ አገር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ አገራቸውን ለማሳደግ ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው ወጣቶች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የራሷ መርከብ ኖሯት፣ ኢኮኖሚዋን እንድታሳድግ ጠንክረው ይሠሩ ነበር፡፡ በዚህም የሰው ኃይል የማሠልጠኑ፣ የባህር መሥሪያ ቤትን የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ከተግባረ ዕድ ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑትን ስምንት ተማሪዎችን በመምረጥም ሆላንድ ሄደው የመርከብ ቴክኒክ እንዲሠለጥኑ ተደረገ፡፡ እነዚህም ተማሪዎች ተሰማ ግዛው፣ ዓለማየሁ በትሩ፣ ጽጌ አብርሃ፣ ከበደ ጥላሁን፣ ሡልጣን ኃይሉ፣ ብርሃኑ ወልደ ሰማያት፣ ማንበግሮህ አደራና ከበደ …. ይባላሉ፡፡ ምልምል ወጣቶቹ ሆላንድ ሄደው ከሠለጠኑ በኋላ እዚያው ይሠሩ የነበሩትን መርከቦችን የሚገፉና የሚጎትቱ አራት ታግቦቶችን እየነዱ መጡ፡፡

እርግጥ ነው ስምንቱ ወጣቶች ታግቦቶቹን፣ አትላንቲክ ውቅያኖስን፣ ሜዲትራንያን ባህርንና ቀይ ባህርን አቋርጠው እንዲመጡ ለማድረግ የተከፈለውን 2.5 ሚሊዮን ዶላር ውኃ ውስጥ የመክተት ያህል ስለሚሆን በፍፁም መደረግ እንደሌለበት፣ በምትኩም ፈረንጆች ሊያመጧቸው እንደሚገባ የሚያሳስብ ተቃውሞ ነበር፡፡ ነገር ግን መልምሎ የላካቸው አካል በተለይም ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ኢትዮጵያዊያኑ ሊያመጧቸው እንደሚችሉ በማሳመናቸው ስምንቱ ኢትዮጵያዊያን ከታግቦታቸው ጋር ከስድስት ወራት በኋላ ምፅዋ ከተፍ አሉ፡፡

በ1952 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው ሦስት ሚሊዮን ብር 1,000 ቶን ክብደት ያላት መርከብ «ዲ ዳብሊው ክሬመርና ሶህን» በተባለ የጀርመን መርከብ ሠሪ ኩባንያ እንድትሠራ የኮንትራት ውል ተፈጸመ፡፡ በኮንትራቱም መሠረት መርከቧ ተሠርታ እ.ኤ.አ. ሜይ 31 ቀን 1961 ርክክብ እንዲፈጸም ነበር፡፡ ይህች «አጥቢያ ኮከብ» የተባለችው የመጀመርያ ዘመናዊ መርከብ መሆኗ ነው፡፡

በወቅቱ የንግድ መርከብ አስፈላጊነት ከምንጊዜም ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ የባህር ክፍል ረዳት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው በቀለ በዩጎዝላቪያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ጥቅምት 12 ቀን 1953 ዓ.ም. ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ «ያለውን ችግር ለማስወገድና የአገራችንን ሀብት ለማልማት በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ከቀረው ዓለም ጋር ልትወዳደር የምትችልበት ደረጃ ለመድረስ፣ የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ቢሆን የዩጎዝላቭያ መንግሥት በዚህ ሥራ ችሎታ ያላቸው አንድ ሁለት ሰዎች እንዲያውሱንና ኢትዮጵያዊያን በሥራው በማሠልጠን ኩባንያው ሊያዳብርና ማንኛውንም የመጫንና የማራገፍ ሥራ ጠቅልሎ እንዲይዝ ማድረግ ይቻላል፤›› ሲሉ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም፣ «ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች ጋር ያላት ንግድ ሳይቋረጥ እንዲያድግ መንገድ መክፈታችን የመላውን ኢትዮጵያን ሀብት ለተወዳጁ ሕዝባችን አሟላንለት ማለት ነው፤» ብለዋል (ሰንደቅ ዓላማችን 195ዐ ዓ.ም.፣ 18ኛ ዓመት ቁጥር 4 ገጽ 2)፡፡

‹አጥቢያ ኮከብ› የተባለችው መርከብና አራቱ ታግቦቶች ተገዝተው ከመጡ፣ እንዲሁም የአሰብ ወደብ በዘመናዊ መንገድ ከተሠራ በኋላ በ1950 እስከ 1951 ዓ.ም. የወጪና ገቢው ዕቃው መጠን ከፍ እያለ በመሄዱ የንግድ መርከብ አስፈላጊነት እየጎላ መጣ፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማኅበርን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (ኢንነመ) አመነበት፡፡ ጥናቱም ተካሄደ፡፡ በተካሄደው ጥናት መሠረትም የንግድ መርከብ ማኅበር ተቋቋመ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ቦርድን ማቋቋም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ይህንን አካል የሚያቋቁም አካል ተመሠረተ፡፡ አካሉም የሥራ መመርያ በማውጣት ቦርዱን አቋቋመ፡፡ ቦርዱ ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ካካሄደ በኋላ የሚከተለውን ማስታወሻ ግንቦት 17 ቀን 1956 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ፀደቀ፡፡

በዚህም መሠረት መጋቢት 18 ቀን 1956 ዓ.ም. በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መዝገብ ቁጥር 4551/56 ተመዝግቦ ሲቋቋም የነበረው ካፒታል ብር 50,000 ብር ሲሆን፣ በዚህም ይዞታ ውስጥ 49 በመቶ የኢትዮጵያ ድርሻ፣ 51 በመቶ ደግሞ በውጭ አገር ከበርቴዎች የተያዘ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንደተቋቋመ ቪሮለመ ከተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ ጋር የስምምነት ውል ተፈራርሞ ሁለት ደረቅ ዕቃ ጫኝ መርከቦች እያንዳንዳቸው 6,550 ቶን የመሸከም ችሎታ ያላቸው «የይሁዳ አንበሳ» (በኋላ «የኢትዮጵያ አንበሳ»)፣ «ንግሥት ሳባ» የተባሉት አንድ 34,075 ቶን የመሸከም ችሎታ ያላትና «ላሊበላ» የተባለች ነዳጅ ጫኚ መርከብ በጠቅላላው ሦስት መርከቦች በ31.6 ሚሊዮን ብር እንዲሠሩ ታዘዘና ተሠሩ፡፡ ቀጥሎም «አዱሊስ»፣ «ጣና ሐይቅ»፣ «አሸንጌ ሐይቅ» እና «ዝዋይ ሐይቅ» ይባሉ የነበሩትን ያገለገሉ መርከቦች ገዝቶ አሰማራ፡፡ በዚህ ጊዜም በአንድ አገር የራሱ የሆነ የንግድ መርከብ አገልግሎት መኖር አስፈላጊና አስተማማኝ መሆኑን በተግባር አረጋገጠ፡፡

በ1961 ዓ.ም. ወደ ወደቦች ሄዶ የነበረው ‹‹ሚረር›› የተባለው መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 4 አዘጋጅ «ንግሥት ሳባ» ስለተባለችው መርከብ ካፒቴን ቫንደር በረግ፣ ኢንጂነር ዓምደ መስቀል ግደይ፣ ቺፍ ኢንጂነር ኤል ፒ ሆኬ፣ ቺፍ ኢንጂነር ሁጌንዶክ ብክል፣ ወርዶፋ ተስፋዬና ኪዳኔ ገልጾ የተባሉትን አነጋግሮ ነበር፡፡ በተለይም ካፒቴን ቫንደር በረግ፣ ስለ «ንግሥት ሳባ» ሲገልጽ፣ «ንግሥት ሳባ በጣም ውብ የባህር መርከብ ናት፡፡ ዘመናዊ የሆኑ መሣሪያዎችና የሬድዮ ቴሌ አላት፡፡ ሁሉም ነገሯ የተሟላ ነው፡፡ ይህቺ 6,500 ቶን የመጫን አቅምና 300,000 ኪዩቢክ ይዘት፣ 54,000 የፈረስ ጉልበት ያለው ሞተር ያላት መርከብ 40 ቶን ክብደት የሚያነሳ ሸበል አላት፡፡ የአየር ሙቀቷንም እስከ 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ዝቅ ማድረግ ይቻላል፤» ብሏል፡፡

አትዮጵያ ሔራልድ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1960 ዕትሙ ደግሞ፣ ‹‹ለብዙ ጊዜያት የወደብ መርከቦች መሀል አገርን በስልክ የማገናኘት ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህንንም ችግር ለማስወገድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ቴሌኮሙዩኒኬሽንና የባህር መምርያ በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይኼውም ጥረት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 1 ቀን 1959 ጀምሮ በመጠናቀቁ በስልክም ሆነ በቴሌግራም ለመገናኘት ተችሏል፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

ቺፍ ኢንጂነር አርሲኤል ሆገን ደግሞ ማሽኗ እጅግ ዘመናዊ ሲሆን፣ በቀላሉ መጠገን ይቻላል ብሏል፡፡ በተጠቀሰው መጽሔት እንዳሰፈረው ሁሉ ምንም እንኳን መርከቧ የምትንቀሳቀሰው በፈረንጆች እንደነበር ባይካድም፣ ፈረንጆቹን በኢትዮጵያውያን ለመተካት የሚደረገው ጥረት ፈጣን ነበር፡፡ ስለሆነም መርከቦች በተገዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሆላንድ ውስጥ የሠለጠኑ ካዴቶች የሥራ ሥልጠና አግኝተው መኰንኖች ሆነዋል፡፡ ሌሎች ባህረኞችና በምግብ ዝግጅት ኃላፊነቱን በብቃት ለመውሰድ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን እየተተኩ ነው፡፡ ምንም እንኳን አንድን የባህረኛ ቡድን በተሟላ ሁኔታ ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ግን ሥራቸውን ስለሚወዱና ራሳቸውን ለማሻሻል ብርቱ ፍላጐት ስላላቸው በቀላሉ ይማራሉ ሲል ቺፍ ኢንጂነሩ ያረጋግጣል፡፡

መነን የተሰኘው መጽሔት ቁጥር 6 መጋቢት 1956 ዓ.ም. በወጣው ዕትሙም የባህር ክፍል መምርያ ቤትና ተግባሮቹ በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ አቶ ከተማ አበበን የተባሉ የባህር ክፍል መምርያ ኃላፊን፣ የመቶ አለቃ መስፍን ብርሃኔ የተባሉ የንግድ መርከብ የንግድ ኃላፊን፣ አቶ መስፍን ፋንታ የተባሉ የበጀትና የኢኮኖሚ መምርያ ኃላፊን፣ አቶ ወልደ ሰንበት ይርጌ የማስታወቂያ መምርያ ኃላፊንና አቶ ደመቀ መታፈሪያ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊን በማነጋገር በወቅቱ የነበረውን እንቅስቃሴ በሰፊው አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ሦስቱን መርከቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹አዶሊስ› የተባለችውን 4,700 ቶን ገዛ፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አማካይነት ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ያለ ችግር የማጓጓዙ ሒደት በመቀጠሉም አድናቆትን እያገኘ መጣ፡፡ ይልቁንም የባህሩ ሥራ የበለጠ ጠንካራ የሚሆነው አዲስ አበባና ሮተርዳም በነበሩት ጽሕፈት ቤቶች ስለነበር የእነዚህ ጽሕፈት ቤቶች መጠናከር ብቃት የሚመሠገን ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም.

እርግጥ ነው እስከ 1966 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የሚሰጠውን ጠቃሚ አገልግሎት እንጂ፣ የደረሰበትን ኪሳራ የሚያሳይ መረጃ በቅርቡ አይገኝም፡፡ ከ1966 ዓ.ም. በቀረበው ጥናት ግን ኪሳራው እየተጠናከረ መጥቶ ከተመሠረተ ከሰባት ዓመት በኋላ ማለትም በ1965 ዓ.ም. ላይ 23 ሚሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሞት ሥራውን ለማቆም ተቃርቦ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለኪሳራ ተዳረገ ተብሎ ከቀረበው ምክንያት ጥቂቱም፣ ለኪሳራው ወይም ለውድመቱ ዋና መንስዔ የአደረጃጀት ጉድለት ያለበት መሆኑ፣ የመርከቦችና የውክልና ሥራው በውጭ አገር ሰዎች በመያዙ፣ ካለው የዓለም መርከብ ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ሊሆን አለመቻሉ፣ በዱቤ የተገዙ መርከቦች ዋጋ ውድነትና የወለዱ ከፍተኛነት፣ በስዊዝ ካናል መዘጋት ምክንያት የተገዙት አዱሊስ፣ ጣና ሐይቅ፣ ዝዋይ ሐይቅና አሸንጌ ሐይቅ የተባሉት መርከቦች ያረጁ በመሆናቸው፣ የስዊዝ ካናል ሲዘጋ ከአውሮፓ የሚመጣው በደቡብ አፍሪካ ዞሮ እንዲሄድና በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ በመዳረጉ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ለኪሳራ የዳረጉት አሮጌ መርከቦች እንዲሸጡ ተደረገ፡፡ በ1970 ዓ.ም. የመንግሥት ልዩ ልዩ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ጋር እንዲተባበሩ የሚያስችል ፖሊሲ ወጣ፡፡ ከቀይ ባህር እስከ ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ተወስኖ የነበረው የንግድ መስመር ወደ ምሥራቅ አውሮፓም ተስፋፋ፡፡ የስዊዝ ካናልም በመከፈቱ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ኩባንያ ማትረፍ ጀመረ፡፡

እስከ 1966 ዓ.ም. የነበሩት ሦስት ደረቅ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ዕድገት እያሳየ ለመጣው የአገሪቱ የወጪ ንግድ በቂ ካለመሆናቸው በላይ፣ በዓይነታቸውና በጭነት ችሎታቸውም በቂና በንግዱ ዘርፍ የሚታየውንም ከፍተኛ ውድድር ለመቋቋም የሚያስችሉ አልነበሩም፡፡ የዘመኑን የቴክኖሎጂ ዕድገት አቅም በፈቀደ መጠን ለመከተልና የአገሪቱ ዓለም አቀፍና የጠረፍ አካባቢ ንግድ እንቅስቃሴ በሚጠይቀው መሠረት፣ ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ አሥር መርከቦች በመጨመር የአገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ለማዳበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ቀጠለ፡፡

በ1966 ዓ.ም. የነበሩት የኮርፖሬሽኑ ጠቅላላ የመጫን ችሎታ 22,525 ቶን በክብደትና 36,716 ኪሎ ሜትር በይዘት መጠን ብቻ ሲሆን፣ አገሪቱ ለአውሮፓ ገበያ ከምታቀርባቸው ወጪ ንግድና ከዚያ ከሚመጣ ልዩ ልዩ የልማትና የንግድ ሸቀጥ ብዛት አንድ አራተኛውን እንኳን ለማጓጓዝ በቂ ስላልነበሩ፣ ኮርፖሬሽኑ አገልግሎቱን ያሟላ የነበረው በቀን እስከ 25,000 ዶላር በውጭ ምንዛሪ እየከፈለ እስከ አምስት የሚደርሱ የደረቅ ዕቃ ጫኝ መርከቦችን በማከራየት ነበር፡፡

ከ1969 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1979 ዓ.ም. ድረስ በየጊዜው ተገዝተው በአገልግሎት ላይ የተሰማሩት ያገለገሉና አዳዲስ መርከቦች ጠቅላላ የመጫን ችሎታ ወደ 92,767 ቶን በክብደት፣ 137,792 ኪሎ ሜትር በይዘት ከፍ ብሏል፡፡  ይህም የ312 በመቶ በክብደት የ275 በመቶ በይዘት ዕድገት ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ኮርፖሬሽን እየተባለ ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 196/1986 የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ተብሎ በ122 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከሐምሌ 1 ቀን 1986 ዓ.ም. አንስቶ በመንግሥት ልማት ድርጅትነት እንደገና ተቋቁሞ መሥራት ጀመረ፡፡ ያኔም ዓባይ ወንዝ፣ አንድነት፣ ነፃነት፣ አብዮት፣ አድማስና ተከዜ የተባሉ የደረቅ ጭነትና ኮንቴይነር መርከቦች፣ ካራማራና ኦሞ ወንዝ የመኪናና የደረቅ ጭነት መጫኛ መርከቦች፣ አዋሽ የተባለች የነዳጅ ጫኝ መርከብ ነበረው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በ1998 ዓ.ም. ዋቢ ሸበሌና ጊቤ የተባሉ እያንዳንዳቸው 25,000 ቶን የሚጭኑ መርከቦች ተሠርተው አገልግሎት ላይ ዋሉ፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ አሶሳ 27,926 ቶን፣ ሐረር 28,000 ቶን፣ ፊንፊኔ 28,140 ቶን፣ ጋምቤላ 281,119 ቶን፣ ጂግጂጋ 28,000 ቶን፣ መቀሌ 28,000 ቶን፣ ሰመራ 28,000 ቶን፣ ባህር ዳር 41,000 ቶን፣ ሐዋሳ 41, 500 ቶን (የነዳጅ) መርከብ ተገዝተው በሥራ ላይ ዋሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ከዋቢ ሸበሌ ጀምሮ ያሉት መርከቦች ናቸው፡፡   

ጥንታዊ የመርከብ ንግድ ታሪክ በጨረፍታ

ታሪክን ታሪክ ያነሳዋል እንዲሉ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክን ስንመለከተው ከጥንት ፊንቃውያን፣ ግሪካውያን፣ ሮማውያን፣ ግብፃዊያንና ሩቅ ምሥራቃውያን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተመሳሳይ የሥልጣኔ አቅጣጫን እንደሚከተል አያጠያይቅም፡፡ የታሪክ መረጃዎቹ የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ለወጣቱ ትውልድ መረጃ ይሆን ዘንድም በዚህ አጋጣሚ ከብዙ በጥቂት የሚከተሉትን መረጃዎች እንመልከት፡፡

ሪቻርድ ፓንክረስት ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ ከገጽ ሦስት እስከ 21 እንዳሰፈሩት፣ ‹‹በአፄ አሜን ሆቴፕ ዳግማዊ ዘመነ መንግሥት (1447-1420 ዓመተ ዓለም) ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ወደ ግብፅ ሄደዋል፡፡ የዚያን ጊዜ የነበሩት የኢትዮጵያ መርከቦች ከኋላና ከፊት ክብ ቀለማቸው ሐምራዊና ምሰሷቸው ትልቅ ነበሩ፡፡ የጥንት ግብፃውያን ታሪክ እንደሚነግረን የንጉሥ ሰለሞን (973 – 930) መርከቦች ከርቤ፣ ዕጣን፣ የከርቤ ዛፍና የከበረ ድንጋይ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ (አፋር) መጥተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሳልሳዊ ፕቲለሚ (305 – 285 ዓመተ ዓለም)፣ በቀዳማዊ ኢርገተስ (246 -221 ዓመተ ዓለም) ግብፃውያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር ይነግዱ ነበር፡፡

ዴቪድ ሐሚልተን የተባሉት የታሪክ ተመራማራ እ.ኤ.አ. በጁላይ 1967፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 2 ላይ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም ኤንሸንት ኤንድ ሞደርን›› በሚል ርዕስ እንዲህ በማለት አስፍረዋል፡፡

በሦስተኛውና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአክሱም አፄያዊ መንግሥት ግዛቱን እስከ ደቡባዊ ምዕራብ ድረስ አስፋፍቶ ነበር፡፡ በዚህም ዘመን አይላ ወይም አዩላስት የተባሉት ግዛቶች በዚያን የአክሱም መንግሥት ሥር እንደ ነበሩ ሪቻርድ በርተን ‹‹ፈርስት ፋትስቴፕ ኤንድ ሊስት አፍሪካ›› (ለንደን 1856) በተሰኘ መጽሐፉ በገጽ 66 ላይ አስፍሯል፡፡ በዚህ ጊዜ የአክሱም መንግሥት ሥልጣኑን እስከተጠቀሰው ግዛት ሲያስፋፋ በመርከብ እየተጓጓዘና የንግድ ሥራ እያካሄደ እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡ ኤም ፐርሐም የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ‹‹ዘ ገቨንርመንት ኦፍ ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1948 ባሳተመው መጽሐፍ እንደገለጸው፣ በስድስተኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ (ዓ.ም.) በኋላም የአክሱም መንግሥት ሠራዊት ደቡብ ዓረቢያን በመያዝ፣ ክርስትናን እንዳስፋፋና ለመንግሥቱ ተጠሪ የሆነ አካል አስቀምጦ ነበር፡፡ ሆኖም በስምንተኛው ክፍለ ዘመን እስልምና እየገነነ ሲመጣ የደቡብ ዓረቢያ ግዛት ብቻ ሳይሆን፣ አዱሊስን በዚህም ጊዜ ቢሆን የዓረቦችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመርከቦች ንግድ ልውውጥ ማድረግ መቀጠሉ አልቀረም፡፡

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት (ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ ገጽ 168 – 169) የሐረር ሡልጣኔቶች እንደ ወረሲ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ ዝባድና የመሳሰሉትን ሸቀጣ ሸቀጦች በዘይላ በኩል አድርገው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመንና ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ሲልኩ በምትኩም ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመርከብ ያስመጡ እንደነበር፣ በወቅቱ ሐረርን ከየመን ከነጋዴዎች ጋር ገብቶ የጎበኘው ሪቻርድ በርተን በሰፊው ያስረዳ ነበር፡፡ ዕውቁ የታሪክ ምሁር ስፔንሰር ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 1965 ለንደን ባሳተመው መጽሐፉም በመርከብ በኩል ነበረውን ግንኙነት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ከ1874 ዓ.ም. ጀምሮ ቱርክ ሐረርን ስትይዝም የመርከብ ንግዱ ከዚህ አንፃር ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ቱርኮች፣ እንግሊዞችና ፈረንሣዮች ኃያል የነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም ይዞታቸውን በቀይ ባህር አካባቢ አስፋፍተው የንግድ መርከብ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ በዲሴምበር ወር በ1859 (እ.ኤ.አ.) ‹‹ለየመን››  በተባለች መርከብ ዘይላንና ምፅዋን የጎበኟት ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበረ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የግብፁ ራዑፍ ፓሻ መረጃ ደርሶት ከሥፍራው አባረራቸው እንጂ ‹‹ሩባቲኖ ስቲም ፓኬት›› የተባለ የጣሊያን ኩባንያ በ1870 ዓ.ም. መርከቡን በአሰብ ወደብ ለማሳረፍና ራሂታ የተባለውን ግዛት በ8,200 ዶላር ለመግዛት ችለው ነበር፡፡ ከዚያም ከአሥር ዓመታት በኋላ ማለትም በ1880 ዓ.ም. ግን የሩባቲኖ ኩባንያ የንግድ መርከብ በአሰብ ላይ ነበረች፡፡

ባንያውያን ከአዱሊስ እስከ ዘይላና በርበራ ተንሰራፍተው ይነግዱ የነበሩ ሲሆን፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያም ሐረር ድረስ በመግባት ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ያመጡ እንደ ነበር ሮበቺ ብሪቸሪ የተባለው ኢጣሊያዊ ተጓዥ «ኔል ሐሪር» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1896 (ሚላን) ባሳተመው መጽሐፉ ይጠቅሳል፡፡ ፒ ፖሊቲስኪ የተባለው ጀርመናዊ የታሪክ ተመራማሪም «ሐረር» በሚል ርዕስ በ1888 ዓ.ም. (ላየ ፕዚሽ) ባሳተመው መጽሐፉ፣ «ህንዳዊያን በሐረር ከፍተኛ ንግድ ያንቀሳቅሱና ሸቀጣቸውን ሸጠው ከኦጋዴንና ከሸዋ በርካታ የዝሆን ጥርስ በመግዛት በንግድ መርከቦቻቸው ወደ ሌላ ገበያ ይወስዱ ነበር፤» ብሏል፡፡  

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ብትሆንም በሌሎች ወደቦች የመጠቀም መብት አላት

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በርካታ አገሮች ወደብ አልባ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የእነዚህም ወደብ አልባ አገሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደብ የሌላቸውን አገሮች በሚመለከት በጠራው መጀመርያ አሥር የነበሩት አገሮች በሦስተኛው ጉባዔ ይኼው ቁጥር ወደ 42 ከፍ ማለቱም ይህንን እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ከእነዚህም ወደብ አልባ አገሮች ውስጥ 15 በአፍሪካ፣ 13 በአውሮፓ፣ 12 በእስያ ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ፡፡

የወደብ አልባ አገሮች ቁጥር ወደፊትም እየጨመረ ይሄዳል የሚል ግምት ሲኖር፣ በጎረቤት አገሮች ወደቦች የመጠቀም መብታቸው እየተጠናከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለ፡፡ በዲሴምበር 10 ቀን 1982 (እ.ኤ.አ.) ባህርን በሚመለከት የወጣው የተመድ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡

ማጠቃለያ

አዎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ ፈጣን ልማት አስፈላጊ መሆናቸውን አምነው እምነታቸውን ይፋ ያደረጉት፣ ሥልጣን በያዙ በሦስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ እጅግ በጣም ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህ አሰብንና ምፅዋን ላለመጠቀም በእልህ የሄድንበት መንገድ ምን ያህል እንዳስከፈለን ታሪክ በሰፊው በዝርዝር ያቀርበዋል፡፡ ምን ያህል እንዳንከራተተንም እንዲሁ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ባለፈው መኖር አይደለም፡፡ አዲስ ተስፋ ሰንቆ መጓዝ ነው፡፡ በአዲስ ተስፋ ስንጓዝ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በቅርቡ ኤርትራ ሄጀ በጎበኘሁበት ጊዜ ተመልክቼ ከቆጩን ነገሮች መካከል ከአስመራ እስከ ምፅዋ በመኪና ስጓዝ ያየሁት አንድ የጭነት መኪና፣ ያውም የማዕድን ኮንቴይነር የተጫነ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ውስጤን እየበላኝ ስሄድ ከአስመራ ወደ ከረን ስጓዝም ያየሁትም ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ የአሰብም ወደብ ተመሳሳይ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ያለፈው አለፈ ወደፊት ግን የምፅዋና የአሰብ ወደቦች እንደ ሎሎች አገሮች በወረፋ የሚገባባቸው ይሆናሉ፡፡ ከምፅዋና ከአሰብ፣ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች ስምምነት ወደ ፊት በቀይ ባህር ድንበር በሚሠሩ ወደቦች ምክንያት በሚገነቡ አቋራጭ መንገዶች በርካታ የጭነት መኪኖች ይርመሰመሳሉ፡፡ አሰብና ምፅዋ ካሸለቡበት ይነቃሉ፡፡ መላው የኤርትራ መንገዶች እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ሁሉ በጭነት መኪኖች ይጨናነቃሉ፡፡ ሚናውም ስለማይበቃ የባቡር መስመሮች በቅርቡ ይዘረጋሉ፡፡ መንገድና የባቡር መንገድ ስለማይበቃቸው በየወደቦቹ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ሥራ ይበዛባቸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ትልቅና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያላት አገር በመሆኗ አሰብና ምፅዋ ብቻ አይበቋትም፡፡ ጂቡቲም፣ በርበራም፣ ኪሲማዮም፣ ሞቃዲሾም፣ ሞምባሳም፣ ፖርት ሱዳንም ያስፈልጓታል፡፡ ትክክለኛ ራዕይ ካለን በሁሉም ወደቦች እየተጠቀምን ኢኮኖሚያችንን ለማፋጠን እንችላለን፡፡ የዶ/ር ዓብይ ከቻይና በቀጥታ ወደ አሰብና ምፅዋ የተደረገ ጉዞም ከዚህ የመነጨ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም፡፡ ሆኖም ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲህ ያለ ቅን ሐሳብና ጉጉት በውስጡ ሊያጎነቁል፣ ሊያድግ፣ ሊያብብና ሊያፈራ ይገባል፡፡ ለመገንባት አቅዶ መገንባት፣ ግንባታውን መከታተል፣ ግንባታውን ከፍፃሜ ማድረስ፡፡ በተገነባው መጠቀም፡፡

‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ

ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ!›› ማለት መቻል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪና የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...