Monday, February 26, 2024

ብሔራዊ ዕርቅና መግባባትን ብሔራዊ አጀንዳ የማድረግ ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ የፖለቲካ ከባቢ በተለይም ደግሞ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በተወሰኑ የሲቪክ ማኅበራት ሠፈር በተደጋጋሚ ለውይይት ወደ ጠረጴዛ ከሚቀርቡት አጀንዳዎች መካከል፣ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የሚለው ይገኝበታል፡፡

ሐሳቡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አገሪቱ ለምታከናውነው ማንኛውም ዓይነት የዴሞክራሲ፣ የሰላምና የዕድገት እንቅስቃሴዎች መሠረታዊውና አንገብጋቢው ነው በሚል አመክንዮ በተደጋጋሚ የውይይትና የድርድር ሐሳብ እንዲሆን የሚነሳ ሲሆን፣ ገዥው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ደግሞ፣  ‹‹ማን ከማን ጋር ተጣላና ነው ዕርቅ የሚደረገው?›› በሚል ሙግት ምክንያት ጉዳዩ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በአገሪቱ ተከስተው በነበሩ ታሪካዊ ክስተቶች ሳቢያ የተፈጠሩ መቃቃሮች ያለ ምንም መቋጫ፣ የፖለቲካዊም ሆነ የኅብረተሰባዊ ግንኙነቶች አካል ሆነው ዘልቀዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች የብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ላይ የሚደረግ ውይይትን የማስቀደም ውትወታና ገዥው ፓርቲ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በሚያሳየው ቸልታ የተነሳ፣ መሠረታዊ በሚባሉ የአገሪቱ ታሪካዊ ክስተቶች ላይ እንኳን ልዩነቶች ጎልተው እየወጡ እንደሆነ፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ የተለያዩ ጸሐፍት በተለያዩ ጊዜያት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚዋልለውን ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ ለማቅረብ እየሠራ እንደሆነ አምስት የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ እንዲሁም ስድስት የሚሆኑ በአውሮፓና በአሜሪካ መቀመጫቸውን ያደረጉ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት ጉባዔም አጀንዳው እንደ አዲስ ነፍስ እንዲዘራና ለውይይት እንዲቀርብ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ይህ የኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ (ብሔራዊ መግባባት ኮሚቴ)፣ የአገር ውስጥ ወኪል ፓርቲዎች ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ እንዲሁም የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኦሕዴኅ) ናቸው፡፡

እነዚህ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ ዓላማ የተመረጡት ደግሞ ከአምስት ወራት በፊት በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ለአራት ቀናት በተካሄው 26 የተለያዩ ፓርቲዎች በተካፈሉበት ስብሰባ መሆኑን፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ቅዳሜ ጳጉሜን 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ‹ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ግብዓት ማስገኛ› በሚል መሪ ቃል የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ አሰናድቶ ነበር፡፡ በዕለቱ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ደግሞ የፊታችን መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ለማከናወን ለታቀደው በጉዳዩ ላይ የሚያተኩር ስብሰባ ግብዓት ለማግኘት በማቀድ መሆኑ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን አዘጋጆቹ የዕለቱ ስብሰባ ዋነኛ ዓላማ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ከታዋቂ ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ መነሻ የሚሆን ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ እንደሆነ ቢገልጹም፣ በዕለቱ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነ በተቃውሞ ጎራው የተለመዱ ግለሰቦች የተገኙበት ስብሰባ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዓብይ አጀንዳው በብሔራዊ መግባባትና በዕርቀ ሰላም ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ ነው ቢባልም፣ ለውይይት መነሻነት የቀረበው ሐሳብ አገሪቱ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን ሁሉ አጭቆ የያዘ በመሆኑ፣ በጉዳዩ ላይ ነጥሮ የወጣ ግብዓት ከማግኘት ይልቅ የተለያዩና ዘርፈ ብዙ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ሲሰነዘሩ ነበር፡፡

በዕለቱ የመድረክ መሪ የነበሩት ታዋቂው የሕግ ምሁርና ፖለቲከኛ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) መድረኩን ለውይይት ከመክፈታቸው በፊት፣ በሕዝቦችና በሕዝብ መካከል ልዩነት ያለ እንደሆነ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚለው አገላለጽ መታረም እንዳለበት በመጠቆም፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነን እንጂ፣ ሕዝቦች አይደለንም፡፡ እኛ አንድ ሕዝብ ነን፡፡ በጉዳዩ ላይ ወደፊት ዕርማት እንደሚደረግ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉት ልዩነቶች ቀላል ከሚመስለው ከዚህ አገላለጽ ጀምሮ የተከማቹና ዘርፈ ብዙ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በመቀጠልም፣ ‹‹ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰቆቃዎች የደረሱ ቢሆንም፣ በግልጽ የይቅርታና ዕርቅ ጉዳይ ትኩረት የተነፈገው ነው፡፡ ዴሞክራሲና ሰላም ከማለታችን በፊት ብሔራዊ ዕርቅን ማስቀደም አለብን፤›› በማለት ከፍተኛ ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያስፈልገው የሚሞግቱበት ምክንያት ደግሞ፣ ባለፉት 40 ዓመታት ለደረሱት ሰቆቃዎች ምንም ዓይነት መፍትሔ ወይም መቋጫ ባለመበጀቱ ነው በማለት እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ቀይ ሽብር ምን እንደሆነ ብዙዎቻችን ዓይተነዋል፡፡ ነጭ ሽብርም እንዲሁ ምን እንደነበር ብዙዎቻችን ዓይተነዋል፡፡ ዕልቂት የተስተናገደበት ዘመን ነበር፡፡ እና ያ ሁሉ ዝም ተብሎ በደፈናው ታፍኖ አለፈ እንጂ በሕዝቡ መካከል ዕርቅ አልወረደም፡፡ እርግጥ ነው የቀይ ሽብር ተዋንያን ደርጎችም ጭምር ፍርድ ቤት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ቅጣታቸውን ተቀብለዋል፡፡ ግን ፍርድ ዕርቅ አያመጣም፡፡ እንዲያውም ዕርቅ ጉዳዩን የበለጠ ሊያከረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ዕርቅ አሁንም እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከሁሉ ነገር አስቀድመን መጀመርያ እርስ በርሳችን መታረቅ ይገባናል፤›› ሲሉም የጉዳዩን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የሕግ ምሁርና በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት የደረሰውን በደል ለመመልከት በተሰየመው ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)፣ በአገሪቱ ባለፉት 40 ዓመታት የደረሱ ብሔራዊ ሰቆቃዎችና ቁርሾዎች በዕርቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ቢገልጹም፣ እሳቸውን ተከትለው የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ግን በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የመነሻ የውይይት ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ፣ በአገሪቱ ያሉ አጠቃላይ ፖለቲካዊ ችግሮችን በመዘርዘር ነበሩ ከተሳታፊዎች በብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ላይ የሚያተኩሩ ግብዓቶች እንዲመላከቱ የጠየቁት፡፡

በዚህም ምክንያት ይመስላል ተሳታፊዎቹ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ታጥረው ግልጽና ጉልህ ሐሳቦችን ከመዘርዘር ይልቅ፣ የተለያዩ ወቅታዊና ዘመን የተሻገሩ የፖለቲካ ልዩነቶችንና ቅራኔዎችን ለማውሳት የተገደዱት፡፡

በአቶ ግርማ በቀለ የቀረበው ባለ አራት ገጽ ጥቅል የውይይት መነሻ ሐሳብ ላይ በመወያየት ለግብዓት የሚሆን ሐሳብ እንዲሰነዘርባቸው ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል ደግሞ ዜግነት፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ፌዴራሊዝምና የመንግሥት አወቃቀር፣ በማዕከልና በፌዴራል መካከል የሚኖረው ግንኙነት፣ የፓርቲዎች አደረጃጀት (ብሔር/ብሔረሰብ፣ ኅብረ ብሔር፣ አካባቢያዊ፣ አገራዊ/ብሔራዊ)፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ አገራዊ እሴቶች፣ የሽግግር መንግሥት፣ ባላደራ መንግሥት፣ የሽግግር ሒደት ወቅት፣ ክልል፣ አስተዳደር፣ አካባቢ፣ ክፍለ አገር፣ ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ከላይ የቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳቦች በአብዛኛው የፖለቲካ ውይይትና ክርክር ወቅት የሚመጡና በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ መጀመርያ ግን በብሐራዊ ዕርቅና መግባባት አጀንዳ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ በተጠራ ስብሰባ ላይ ሲቀርቡ መሠረታዊውን አጀንዳ እንደሚደፈጥጡትና ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ወስደውት በጉዳዩ ላይ የነጠረ፣ የጋራና ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችል ሐሳብ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆን የቅዳሜ ዕለቱ የራስ ሆቴል መድረክ ጥሩ ማሳያ ነበር፡፡

ምክንያቱም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሐሳቦች በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እንኳን መግባባት ያልተደረሰባቸው አጀንዳዎች በመሆናቸው፣ ስለብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ሲወሳ ደግሞ ከፓርቲዎች ግንኙነትና ልዩነት ማዕቀፍ ወጥቶ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ቁርሾ ለማረቅ የሚደረግ የሐሳብ ፍጭት እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ የተለያዩ ጽሑፎች ያመላክታሉ፡፡

ለዚህም ይመስላል የቀድሞው የፓርላማ ተመራጭ አቶ መሐመድ ዓሊ የጽሑፉ ከቀረበ በኋላ፣ የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በማንሳት ጉዳዩ በተወሰነ ማዕቀፍ ውስጥ ቢሆን መልካም እንደነበር ያወሱት፡፡

ከዚህ አንፃር አቶ መሐመድ የሚከተሉትን ጥያቄዎች/ግብዓቶች ለአዘጋጆቹ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹መነሳት ካለባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች የማንግባባባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት በማለት ዘርዝረን እናውቃቸዋለን ወይ? በተለይ የኢትዮጵያን ህልውና ሊፈትኑ የሚችሉ የማንግባባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚባሉት ተነቅሰው መቀመጥ አለባቸው፤› በማለት በዝርዝር ፖለቲካዊ ልዩነቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በብሔራዊ ደረጃ የሚያግባቡና የአገሪቱን ህልውና ሊፈትኑ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ቢሰጥ መልካም እንደሆነ በመግለጽ፣ የማይግባቡትስ እነማን ናቸው? በማለት ጥያቄ አዘል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምክክር መድረኩ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተብሎ በመሰየሙ ምክንያት ባለድርሻዎቹ እነማን ናቸው የሚል ጥያቄ በማቅረብ፣ ‹‹ይህ ስብሰባ የኢትዮጵያን ሥዕል ቢያንስ በጠባቡ ሊያሳየን የሚችል መሆን አልነበረበትም ወይ? በማለት ጠይቀው፣ ‹‹ጠባቡ ኩሬ ውስጥ ከመንቦራጨቅ ወጥተን ባህሩ ውስጥ ገብተን መዋኘት ይኖርብናል፤›› የሚል አተያይ እንዳላቸው  በመግለጽ፣  ‹‹የችግሩን ሥረ መሠረት ማግኘት አለብን፡፡ አለበለዚያ ግን ችግሩን አንፈታውም፤›› የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን አቶ መሐመድም ሆነ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩን በነጠረ መንገድ መመልከትና መወያየት በአገራዊ ዕርቅና መግባባት ላይ የተቸነከሩ ሰንኮፎችን ለመንቀል ወሳኝነት እንዳላቸው የገለጹ ቢሆንም፣ በአቶ ግርማ አማካይነት በዕለቱ ቀርቦ የነበረ የውይይት መነሻ ሐሳብ ግን እጅግ የተለጠጠና የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ እንዲሁም የፖሊሲ ጉዳዮችንም የነካካ ነበር፡፡

ለአብነት ያህልም ከሕገ መንግሥት አንፃር፣ ‹‹የአገርን መሥፈርት የምታሟላ አገር አለችን (ሕዝብ፣ ድንበር፣ መንግሥት፣ ሉዓላዊነት/ነፃነት)? የአገር ባለቤት ማነው? ዜጎች ወይስ ብሔር ብሔረሰቦች? ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ/የሚጋጩ ሕጎች፣ አዋጆች፣ አሠራሮች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ሕገ መንግሥታዊ የሕግ፣ የአዋጅ ደንቦችና አሠራሮች በማንና እንዴት ይሻሻላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ለውይይት መነሻነት ከቀረበው ባለ አራት ገጽ ጽሑፍ ውስጥ ታጭቀው ይገኛሉ፡፡            

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች በመግባት በብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ሐሳብ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ የተጠራው ስብሰባ፣ ‹‹መጪው የ2012 ዓ.ም. ምርጫ በወቅቱ ለማድረግ ከሚጠበቀው የለውጥ ሒደትና ውጤት አንፃር በቂ ጊዜ አለ? በወቅቱ ሊደረግ ይችላል? የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የፈጸሙት በደል እንዴት ይስተናገዳል? ይቅርታ፣ ምሕረት? የነፃ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አወቃቀር፣ አደረጃጀት፣ አመራር፣ ነፃነትና ተዓማኒነት፣ እንዲሁም የተጠያቂነት ጉዳይ እንዴት ይከናወን? ኢሕአዴግ በጀመረው መንገድ በተናጠል ቢያከናውነው ዘላቂና ተዓማኒ ውጤት ሊያመጣ ይችላል? የመከላከያ ኃይል አወቃቀር፣ አደረጃጀት፣ አመራርና በትጥቅ ትግል ያሉ/የነበሩ ድርጅቶች በመከላከያ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? በኢሕአዴግ ዘመን በሙስና የተገኙ በባለሥልጣናት የተያዙ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ጉዳይ፣ ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት ግብዓት ለመሰብሰብ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ግን በአብዛኛው የፖለቲካና የፖሊሲ አጀንዳዎች ከመሆናቸው አንፃር፣ ስለብሔራዊ ዕርቅና መግባባት በተጠራ መድረክ ላይ መነሳታቸው ጉዳዩን ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረግ ራሱ ከፍተኛ ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ሐሳቦች በመተንተን የመፍትሔ ሐሳብ ማስቀመጥና የአገሪቱን ቀጣይ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር መደራደር ወይም መወያየት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስላል ‹አንድ አገር አንድ ሕዝብ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ› የሚባል መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው ድርጅት የመጡት አቶ ነሲቡ ስብሃት፣ ‹‹ምክክርና ውይይት እስከሆነ ድረስ አሁንም ጥረት መደረግ ያለበት በዚህ ሒደት ያልተካተቱ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል መካተት ይኖርባቸዋል፤›› በማለት ያስታወቁት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚንፀባረቀው እኛ ብቻ ነን ተቃዋሚ የሚለውና የአግላይነት ጉዞ እንዳይኖር፣ ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን ጥረት አድርጉ፡፡ አግላይነቱ ካለ አሁንም ወደ ሌላ ቦታ ይወስደናል፤›› ሲሉ አቶ ነሲቡ ማሳሰቢያ ለግሰዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት የምክክር መድረክ ከመፈጠሩ በፊት ፓርቲዎች ራሳቸው መግባትና አንድ መሆን ይገባቸዋል የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ፓርቲዎች በተናጠል የሚያደርጉት እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ምንም ውጤት እንደማያመጣ በብስጭት ተናግረዋል፡፡

‹‹ፓርቲዎች በጋራ ወደ መታገል የማንመጣ ከሆነ እንዲህ ተበጣጥሶ የሚደረገው ነገር የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ይህን ኃይል ከማቀናጀት በፊት እኛ ቁጭ ብለን ልዩነቶቻችንን አጥብበን መምጣት አለብን፤›› ሲሉ በፓርቲዎች በኩል የሚነሱት የተለያዩ ሐሳቦች ከመጀመርያው በተደራጀ መንገድ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በፓርቲዎች መካከል የሰፋ ልዩነት በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት ተሰብስቦ መወያየቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ምንድነው? በማለት የሚጠይቁት አቶ አበበ፣ ‹‹እኛ እኮ ሳንገናኝ ነው ሌላውን ሰው ለማገናኘት የምንሞክረው፡፡ መጀመርያ እኛ ሰብሰብ ብለን ተገናኝተን ነው የሲቪክ ማኅበራትንም ሆነ ሌላውን አካል ማገናኘት የምንችለው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ዝም ብሎ ለይስሙላ የሚደረግ ነገር ነው፤›› ሲሉ ቅድሚያ ለፓርቲዎች አንድነትና የአብሮ መሥራት ባህል መሰጠት እንዳለበት ሞግተዋል፡፡

በቅዳሜው መድረክ ላይ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ምንም እንኳን ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የሚለው አጀንዳ ባለፉት 27 ዓመታት ከፖለቲካው መንደር ጠፍቶ የማያውቅ ቢሆንም አሁንም፣ ግን የትኛው ጉዳይ ቅድሚያ አግኝቶ ዕርቅ ወይም መግባባት ይደረግበት? የሚለው ጉዳይ ራሱ ገና መግባባት ያላገኘ ሐሳብ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በብሔራዊ ዕርቅና መግባባት አጀንዳዎች ላይ ውይይቱና ሙግቱ፣ እንዲሁም ሐሳብ መረጣው አዲስ አበባ በሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ መታጠሩ፣ ጉዳዩ በቅርቡ ብሔራዊ አጀንዳ የመሆን ዕድሉ እየመነመነ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር ከተለያዩ አገሮች የተገኙ ልምዶችን በቀመር በአገሪቱ ማኅበራዊ ግንኙነቶችና ታሪካዊ ስህተቶች ላይ ያሉትን ጽንፍ የያዙና የተቃረኑ ሐሳቦችን መጀመርያ ለመፍታት በሚያመች መንገድ በመግባባት ወደ አንድ መሠረታዊ መግባቢያ መምጣት ካልተቻለ ጉዳዩን ብቻ በማንሳት፣ እንዲሁም ከሌሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በማዳበል ከሚደረገው ጉዞ በመነሳት ብሔራዊ ዕርቅና መግባባትን ማስፈን ከባድ ፈተና እንደሚሆን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -